በ2014 ዓመተ ምህረት በልግ ወቅት ከ82 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በተለያዩ ሰብሎች እንደሚለማ የጉራጌ ዞን ግብርና መምሪያ አስታወቀ።

መምሪያው የ2014 የበልግ፣የፍራፍሬና የመኖ ልማት የንቅናቄ መድረክ በወልቂጤ ከተማ ዛሬ አካሄደ።

በመድረኩ የተገኙት የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ መሀመድ ጀማል እንዳሉት አመራሩ፣ባለሙያውና አርሶ አደሩ በመደበኛ መስኖና በበጋ የመስኖ ስንዴ ተግባር ላይ ያሳየው ቁርጠኝነትና ውጤታማነት በበልግና በሌሎችም የግብርና ስራዎች መድገም አለበት።

የበልግ ወቅት የግብርና ስራችን ውጤታማ እንዲሆን አመራራችን ከማይጠቅሙ አጀንዳዎች ወጥቶ ባለሙያው በማገዝ ሊያጋጥሙ የሚችሉ የግብአትና ሌሎችም ችግሮች እየፈታ በጥንቃቄ መምራት አለበት ብለዋል።

በዞናችን በፍራፍሬው ዘርፍ ያለው አቅም ለመጠቀምና የአርሶ አደሩን ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ የፍራፍሬ የችግኝ ጣቢያዎችን በማስፋፋት ለአርሶአደሩ በሚፈልገው አይነትና መጠን ማሰራጨት መሰረታዊ ጉዳይ መሆኑ አመላክተዋል።

አስተዳዳሪው አክለውም የፍራፍሬ ምርትን በአርሶአደር፣ በእምነት ተቋማት እና በትምህርት ቤት ማሳዎች ላይ ማስፋት ያስፈልጋል ሲሉም ጠቁመዋል።

የጉራጌ ዞን ምክትል አስተዳዳሪ እና የግብርና መምሪያ ሀላፊ አቶ አበራ ወንድሙ እንደገለፁት የንቅናቄው አላማ ከሰብል ልማት ፣ ከፍራፍሬ እና ከመኖ ልማት አኳያ ከአመራሩና ከሌሎችም ባለድርሻ አካላት ጋር በመወያየት በቀጣይ የአርሶአደሩን ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ ወሳኝ በመሆኑ ነው።

በዞናችን የበልግ እቅድ ለማሳካት ሁሉም መሬቶች በተገቢ ለይቶ ከአርሶ አደሩ በመግባባትና በተገቢ በማቀድ ወደ ተግባር መግባት ያስፈልጋል ብለው ለዚህም አመራሩና ባለሙያው ቁርጠኛ መሆን አለበት ብለዋል።

የምርጥ ዘር ማባዣ ማእከላት በመገንባት የአርሶአደሩን የግብአት ችግሮች ለመቅረፍ መሰራት ይገባል የሚሉት አቶ አበራ ለየትኛው ሰብል የትኛውን ማዳበሪያ መጠቀም እንደሚገባ ለአርሶ አደሩ ለማስገንዘብ የግብርና ባለሙያዎች ከወዲሁ መስራት ይገባቸዋል ብለዋል።

የእንስሳት ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ በተሰራው ስራ በ2009 አመተ ምህረት ከነበረው 64 ነጥብ 6 በመቶ በ2014 አመተምህረት ወደ 85 ነጥብ 5 በመቶ መሳደግ ተችሏል ብለው የበለጠ ውጤታማ ለመሆን የመኖ ልማት ስራዎች በሁሉም አማራጮች መጠናከር አለበት ብለዋል።

የመምሪያው ምክትል ሀላፊና የእርሻ ዘርፍ ሀላፊ አቶ አክሊሉ ካሳ የበልግና የፍራፍሬ ልማት ንቅናቄ እቅዱ ባቀረቡበት ወቅት እንደገለፁት በ2014 ዓመተ ምህረት በልግ ከ350 ሺህ በላይ አርሶ አደሮች በማሳተፍ ከ82 ሺህ በላይ መሬት በበልግ ሰብሎች ይለማል።

አክለውም አቶ አክሊሉ የክልሉ መንግስት የቀጣይ 3 አመታት 30፣40፣30 የፍራፍሬ ልማት አዲስ እቅድ ይፋ ማድረጉ ገልፀው እንደ ዞናችን ወረዳዎች ባላቸው ምቹ ሁኔታ በ4 የፍራፍሬ ክላስተር በማደራጀት በቀጣይ 3 አመታት 1ሚሊየን 600 ሺ የፍራፍሬ ዛፎች እንዲሁም በ2014 ዓመተ ምህረት 480 ሺ የፍራፍሬ ዛፎች ልማት ስራ ይሰራል ብለዋለ።

ኩታገጠም እርሻ ካለው ጠቀሜታ አንፃር በበልግ ከሚለማው ማሳ 75 ከመቶው በኩታ ገጠም አስተራስ ዘዴ ማሳካት እንደሚገባም በእቅዳቸው አመላክተዋል።

የመምሪያው ምክትል ሀላፊና የእንስሳት ዘርፍ ሀላፊ አቶ መሀመድ ሙደሲር የመኖ ንቅናቄ እቅድ ባቀረቡበት ወቅት እንደገለፁት የእንስሳት ሀብት ልማት ያለ መኖ ልማት ውጤታማ ሊሆን አይችልም ብለው የመኖ ልማት በዞናችን በርካታ አርሶ አደሮች አምርተው በመሸጥ ከፍተኛ ገቢ እያገኙ ይገኛል።

እንደ አቶ መሀመድ ገለፃ በዞኑ የእንስሳት ሀብት ከ9 ሚሊዮን በላይ መድረሱ ገልፀው በቀጣይ ወራት የእንስሳት ሀብት ልማቱ ውጤታማ ለማድረግ 10 ሺህ 670 ሄክታር መሬት በተለያዩ የመኖ ዝርያዎች ይለማል።

የመድረኩ ተሳታፊዎች በበኩላቸው እንደ ሀገር ከገጠመን ፈተና ለመሻገር ከአርሶ አደሩ ጋር በቀጣይ በበልግና በሌሎችም ወቅቶች የሚሰሩ የግብርና ስራዎች ላይ መግባት ይገባል ብለዋል።

የግብርና ምርትና ምርታማነት ሲጨምር የዋጋ ንረት ይቀንሳል የሚሉት ተሳታፊዎች የአርሶ አደሩን የማምረትና የእርሻ አቅም በማወቅ ከምርጥ ዘር፣ከማዳበሪያና ከሌሎችም ግብአት አቅርቦት ጋር ተገቢ ዝግጅት ማድረግ እንደሚገባ ተናግረዋል።

አክለውም አስተያየት ሰጪዎቹ የመኖ ልማት ለእንስሳት ዘርፉ ወሳኝ በመሆኑ ከአርሶ አደሩ ባሻገር ወጣቶችንና ሴቶችን በማደራጀት የወል መሬት ላይ ቢተገበር አዋጭ መሆኑን ገልፀው በከተሞች ዘመናዊ የግብርና ስራዎች ማስፋትና መደገፍ ይገባል ብለዋል ።

የዞኑ የበልግ ሰብሎችና የፍራፍሬ እንዲሁም የመኖ ልማት ንቅናቄ እቅዶች በዘርፉ አመራሮች በዝርዝር ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል ሲል በመድረኩየዘገበው የጉራጌ ዞን የመንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ነው።

= ኢትዮጵያን እናልማ፣ የፈረሰውን እንገንባ፣ለፈተና እንዘጋጅ!

በመረጃ ምንጭነት ምርጫችሁ ስላደረጋችሁን እናመሰግናለን

በተጨማሪም እነዚህ ሊንኮችን በመጫን ወቅታዊና ትኩስ መረጃዎቻችንን እንድትከታተሉ እንጋብዛለን፡፡
Facebook:- https://www.facebook.com/gurage1Zone
Website:- https://gurage.gov.et
Telegram:- https://t.me/comminuca
Youtub: -https://www.youtube.com/channel/UCzrcazGvvIO2tG7bQN36Cx

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *