የዞኑ ፍትህ መምሪያ የ3 ዓመት የፍትህ ዘርፍ ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ላይ ትኩረት ያደረገ ውይይት ከባለ ድርሻ አካላት ጋር በወልቂጤ ከተማ ተካሂዷል።
የጉራጌ ዞን ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ ክብርት ወ/ሮ ልክነሽ ስርገማ በመድረኩ ላይ እንዳሉት በሀገሪቱ የሚሰሩ ልማቶች ህብረተሰቡ ተጠቃሚ ለማድረግ የፍትህ ተቋማት ሚና ከፍተኛ ነው።
በፍትህ ተቋማት የሚስተዋሉ ብልሹ አሰራሮችን በመቅረፍ የአገልግሎት አሰጣጡ ቀልጣፋ፣ ፍትሃዊና ውጤታማ ለማድረግ በትኩረት ሊሰራ ይገባል።
በፍትህ ተቋማት በሚሰጡት አገልግሎቶች ላይ ህብረተሰቡ እንደማይረካና እምነቱ እየሸረሸረ መምጣቱን በመገንዘብ ይህንን ለመቀየር የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ተቀናጅተው ሊሰሩ እንደሚገባ ክብርት አፈ ጉባኤዋ አስገንዝበዋል።
የጉራጌ ዞን ፍትህ መምሪያ ኃላፊ አቶ ኤሊያስ ሰብለጋ በበኩላቸው ፍትህ በገንዘብ ይሰጣል የሚል ቅሬታ ህብረተሰቡ ዘንድ እንደሚነሳ ገልጸው በቀጣይ ፍትህ ያለ ምንም አድሎ ለዜጐች ለመስጠት የሚያስችሉ የፍትህ ማሻሻያዎችን ተግባራዊ እንደሚደረጉ አብራርተዋል።
የፍትህ እሴቶች እውቀት፣ ውጤታማነት፣ ነጻነት፣ ተጠያቂነት፣ ግልጽነት፣ ታማኝነት፣ እኩልነትና ተደራሽነት ተግባራዊ በማድረግ ህብረተሰቡ በፍትህ ተቋማት ያለውን እምነት ማሳደግ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
እንደ አቶ ኤሊያስ ገለጻ በቀጣይ የፍትህ ዘርፍ ለማሻሻል ባህላዊ የሽምግልና ስርዓት ማጠናከር፣ የኢንፎርሜሽን ኮሚዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ አጠቃቀም ማሳደግ፣ ለህብረተሰቡ የንቃተ ህግ ትምህርት መስጠት፣ አማራጭ የሙግት መፍቻ ስርዓት መዘርጋት እንዲሁም የፍትህ ተቋማት ተደራሽነት ማስፋት ላይ ትኩረት ተደርጎ ይሰራል።
የውይይቱ ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያየት ከፌዴራል ተቋማት ጀምሮ በፍትህ ዘርፍ የሚስተዋሉ ችግሮች ለመቅረፍ የሚደረጉ ጥረቶች አነስተኛ በመሆናቸው ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ብለዋል።
በዞኑ መርማሪ ፓሊስ በሰው ሀይል የማጠናከር እና ከማረሚያ ተቋማት የሚደረጉ የእስረኛ ዝውውሮች ላይ የሚስተዋሉ የግልጸኝነት ችግሮች መፍትሔ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል።
አክለውም ህብረተሰቡ በፍትህ ተቋማት ያለውን አመኔታ ለማሻሻል አጥፊ ባለሙያዎች በህግ ተጠያቂ የሚሆኑበት እንዲሁም በጥሩ ስነ ምግባር የተሻለ የሚፈጽሙት የሚበረታቱበት ስርዓት ሊዘረጋ እንደሚገባ ተናግረዋል።