በጤና ተቋማቶች ቀልጣፋና ዉጤታማ አገልግሎት ለመስጠት ከመቼዉም ጊዜ በላይ አጽዕኖት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑም የአበሽጌ ወረዳ ጤና ጽህፈት ቤት አስታወቀ።

ሀምሌ 17/ 2014 ዓ.ም

በጤና ተቋማቶች ቀልጣፋና ዉጤታማ አገልግሎት ለመስጠት ከመቼዉም ጊዜ በላይ አጽዕኖት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑም የአበሽጌ ወረዳ ጤና ጽህፈት ቤት አስታወቀ።

የእናቶችና ህጻናት ሞት ለመቀነስ ባለፈዉ በጀት አመት ከ2 ሺህ 4 መቶ በላይ እናቶች በጤና ተቋም መዉለዳቸዉም ተገልጿል።

በጤና ጣቢያዎች የእናቶች ማረፊያ ማራኪና ምቹ ለማድረግ ባለፉት አመታት ዘርፈ ብዙ ስራዎች እየተሰራ ነዉ።

የአበሽጌ ወረዳ ጤና ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ክበበዉ በስር እንዳሉት በወረዳዉ ሶስት የመንግስትና አንድ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት ጤና ጣቢያዎች ይገኛሉ።

በነዚህም ጤና ጣቢያዎች በሁሉም ዘርፍ አገልግሎት የሚሰጡ ባለሙያተኞች ተመድበዉ ለማህበረሰቡ አገልግሎት እየሰጡ ይገኛሉ ብለዋል።

በወረዳዉ 29 ቀበሌዎች የሚገኙ ሲሆን ከነዚህ መካከል 26 የገጠር ቀበሌዎችና 3 የከተማ ቀበሌዎች ሲሆኑ ለነዚህም 58 ጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያተኞች ተመድበዉ አገልግሎት እየሰጡ ይገኛል ብለዋል።

የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያተኞች በጤና ኬላዎችና ቤት ለቤት በመሄድ የጤና አገልግሎት እየሰጡ እንደሆነም ያስረዱት ኃላፊዉ በየሳምንቱ በሁሉም ቀበሌዎች ከጤና ጣቢያ የተመደቡ ባለሙያተኞች የአገልግሎት አሰጣጡን ወርደዉ እንደሚገመግሙም አስረድተዋል።

በጤና ተቋማቶች ዘርፈ ብዙ አገልግሎቶች ለማህበረሰቡ የሚሰጥ እንደሆነም ተናግረዉ በዚህም የአይን ህክምና ፣ የወሊድ፣ የቅድመ ወሊድና የድህረ ወሊድ እንዲሁም የኤች አይቪ ኤድስ ፣ የወጣቶች የአቻ ለአቻ አገልግሎት የቲቢ ህክምናና በሌሎችም ዘርፎች አገልግሎት እየሰጡ እንደሆነም አብራርተዋል።

በጤና ተቋማቶች ቀልጣፋና ዉጤታማ አገልግሎት እየተሰጠ እንደሆነም ያብራሩት አቶ ክበበዉ ባለፉት ሶስት ወራት ተገልጋዩ ማህበረሰብ የማወያየት ስራ በመስራት የተሻለ ስራ ለመስራት ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ እንደሆነም ጠቁመዋል።

ባለፈዉ በጀት አመት የእናቶችና ህጻናት ሞት ለመቀነስ ትኩረት ተደርጎ እየተሰራ እንደሆነም ተናግረዉ በዚህ 14 ሺህ 140 እናቶች የቤተሰብ ምጣኔ አገልግሎት እንዳገኙና 2 ሺህ 7 መቶ 27 እናቶች የቅድመ ወሊድ ክትትል በጤና ተቋም እንዳደረጉም አስታዉሰዋል።

ክትትል ሲያደርጉ ከነበሩ ነብሰጡር እናቶች መካከል 2 ሺህ 4 መቶ 22 እናቶች በጤና ተቋም የወለዱ ሲሆን እነዚህም እናቶች የኤች አይቪ ኤድስ ምርመራ ያደረጉ እንደሆነም አብራርተዉ ከነዚህም መካከል በ2 እናቶች ላይ ቫይረሱ በደማቸዉ መገኘቱም አስታዉቀዉ እነዚህም ተገቢዉን ህክምና እንዲከታተሉ ተደርጓል ብለዋል።

በወረዳዉ 2 መቶ 24 የህብረተሰብ ክፍሎች የኤች አይቪ ቫይረስ ያለባቸዉ ወገኖች መኖራቸዉም ጠቁመዉ እነዚህም መድሃኒታቸዉ በአግባቡ እንዲወስዱ መደረጉም አስረድተዋል።

ህጻናት የሳንባ ነቀርሳ ፣ የኩፍኝና የጸረ አምስትና ሌሎችም ክትባት ከመስጠት አንጻር መቶ ፐርሰንት የክትባት አገልግሎት እንዲያገኙ መደረጉም አመላክተዋል።

የአገልግሎት አሰጣጡ ፍትሃዊነት በተረጋገጠ መልኩ የጤና ሽፋን 84 ፐርሰንት ማድረስ መቻሉም አስረድተዉ የህጻናት ስርአተ ምግብ በሁሉም ቀበሌዎች እየተሰጠ እንደሆነም አብራርተዋል።

አርሶአደሩን የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን ድርጅት በተሻለ ደረጃ ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑም አስረድተዉ ይህንኑ ለማስፈጸም ከወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ፣ ከዞኑ ቀይ መስቀልና እነዚህም ጨምሮ ከ9 ተቋማት ጋር ዉል ገብተዉ እየሰሩ እንደሆነም ሀላፊዉ አስታዉቀዋል።

በጤና ጣቢያዎች የእናቶች ማረፊያ ማራኪና ምቹ ለማድረግ ባለፉት አመታት ዘርፈ ብዙ ስራዎች መሰራቱም ተናግረዋል።

የሆሌ ጤና ጣቢያ ሀላፊ አቶ ዘኪዩ ሁጅራ በበኩላቸዉ በጤና ጣቢያዉ በ2014 ዓመተ ምህረት 645 እናቶች ክትትል ያደረጉ ሲሆን በዚህም 564 በጤና ጣቢያዉ መዉለዳቸዉም ተናግረዋል።

በጤና ጣቢያዉ የመድሀኒት እጦት እንዳይከሰት ከአጋዥ ድርጅቶችና ከጤና ጽህፈት ቤት ጋር በመተባበር አጽዕኖት ተሰጥቶት እየተሰራ እንደሆነም አስታዉቀዋል።

ማህበረሰቡ በጤና ጣቢያዉ የሚፈልገዉ አገልግሎት አግኝቶ እንዲመለስ ከመቼዉም ጊዜ በላይ በትኩረት እየተሰራ እንደሆነም የተናገሩት አቶ ዘኪዩ በጤና ጣቢያዉ ምቹ የእናቶች ማረፊያ ተገንብቶ አገልግሎት እየሰጠ እንደሆነም ጠቁመዋል።

በሆሌ ጤና ጣቢያ አገልግሎት ሲያገኙ ያነጋገርናቸዉ ወይዘሮ ሀድራ መሀመድ እና ወይዘሮ ዘይነባ ኑርበዛ በሰጡት አስተያየት በጤና ጣቢያዉ በተደጋጋሚ ጊዜ አገልግሎት ለማግኘት የሚመላለሱ እንደሆነም ተናግረዋል።

በጤና ጣቢያዉ ባለሙያተኞች በተገቢዉ ቀልጣፋና ዉጤታማ አገልግሎት እያገኙ እንደሆነም ጠቁመዉ ይህም ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም አስረድተዋል።
መረጃዎቻችበተጨማሪም እነዚህ ሊንኮችን በመጫን ወቅታዊና ትኩስ መረጃዎቻችንን እንድትከታተሉ እንጋብዛለን፡፡
Facebook:- https://www.facebook.com/gurage1Zone
Website:- https://gurage.gov.et
Telegram:- https://t.me/comminuca
Youtub:- https://youtube.com/channel/UCzrcazGvvIO2tG7bQN36CxQ
Twitter:- https://4pvf.short.gy/bTJNNn

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *