በግብርና ዘርፍ እየተመዘገቡ ያሉ ምርጥ ተሞክሮዎች ለማስፋት የአርሶአደሮች የመስክ ጉብኝት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት የቸሀ ወረዳ አስተዳደር አስታወቀ።

መጋ

በግብርና ዘርፍ እየተመዘገቡ ያሉ ምርጥ ተሞክሮዎች ለማስፋት የአርሶአደሮች የመስክ ጉብኝት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት የቸሀ ወረዳ አስተዳደር አስታወቀ።

በወረዳው በመደበኛ መስኖና በበጋ መስኖ ስንዴ በለሙ ማሳዎች የመስክ ጉብኝት ተካሄደ።

በጉራጌ ዞን መደበኛና የበጋ መስኖ ስንዴ በስፋት ከሚመረትባቸው ወረዳዎች አንዱ ቸሃ ወረዳ ሲሆን በዘርፉ የተገኙ ልምዶች ለማስፋት በየጊዜው የአርሶ አደሮች የመስክ ጉብኝት ይካሄዳል።

የጉራጌ ዞን ግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ አበራ ወንድሙ እንደተናገሩት በየአመቱ የሚከናወኑ የአርሶአደሮች የመስክ ጉብኝት አርሶአደሮች፣ ባለሙያዎችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ከፍተኛ ልምድ ያስገኝላቸዋል።

በዞኑ በተለያዩ አካባቢዎች መደበኛ እና የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት እየተከናወነ ሲሆን ለዘርፉ ውጤታማነት መንግስት አስፈላጊውን ድጋፍ እያደረገ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

በቸሃ ወረዳ በመደበኛ መስኖ እና በበጋ መስኖ ስንዴ የለሙ ማሳዎች አበረታች ሲሆኑ በዞኑ በሚገኙ በሁሉም ቀበሌዎች መሰል ስራዎች በማጠናከር የግብር ምርቶች በብዛት ለገበያ በማቀረብ የዋጋ ግሽበት ለመቆጣጠር መስራት ይገባል ብለዋል።

በዞኑ በሁሉም ወረዳዎች የመሬትአቅርቦት እጥረት ባለመኖሩ ወጣቶች፣ ሴቶች እና አርሶአደሮች በግብርናው ዘርፍ መሰማራት ይጠበቅባቸዋል። ለዚህ ደግሞ ዞኑ አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን አቶ አበራ ገልጸዋል።

የቸሀ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ጥላሁን ሽምንሳ የወረዳው አርሶአደሮች የምግብ ዋስትናው ከማረጋገጥ ባለፈ ለገበያ በማቅረብ ተጨማሪ ገቢ እንዲያገኝ እየተሰራ ነው ብለዋል።

በ2015 ዓ.ም 210 ሄክታር መሬት በበጋ መስኖ ስንዴ የለማ ሲሆን ከ3 ሺህ 500 በላይ ሄክታር መሬት በመደበኛ መስኖ እየለማ እንደሚገኝ አቶ ጥላሁን ገልጸዋል።

እንደ ዋና አስተዳዳሪው ገለፃ ወጣቶች ከስራ ጠባቂነት ተላቀው በመስኖ ስራ እንዲደራጁ ግንዛቤ ከመፍጠር ጎን ለጎን የብድር አገልግሎት፣ የመሬት አቅርቦትና የባለሙያ ድጋፍ እንደሚደረግላቸው አስረድተዋል።

የወረዳው ግብርና ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ዮሴፍ ይልማ በበኩላቸው በሞዴል አርሶ አደሮች የለሙ ማሳዎች ተሞክሮ ወደ ሌሎች አካባቢዎች ለማስፋት በየአመቱ የአርሶአደሮች የመስክ ጉብኝት ይካሄዳል ብለዋል።

አርሶአደሮች ከዝናብ ጥገኝነት ተላቀው በአመት እስከ ሶስት ጊዜ በማምረት የምግብ ዋስትናቸውን እንዲያረጋግጡ የመስኖ ልማት ስራዎች ማጠናከር እንደሚጠበቅባቸው ገልጸዋል።

አርሶአደሮች በገበያ ተፈላጊ የሆኑ የመስኖ ውጤቶች መመልከታቸው የግብርና ዘርፍ የአርሶ አደሩ የገቢ አቅም ከማሳደግ ባለፈ ገበያን ለማረጋጋት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት ያላቸው ግንዛቤ ያሳድግላቸዋል ብለዋል።

በወረዳው እስካሁን በመስኖ ከለማ ከ3ሺህ 500 በላይ ሄክታር ማሳ ከ350 ሺህ በላይ ኩንታል ምርት የተሰበሰበ ሲሆን ምርቱ የገበያ ክፍተት በሚስተዋልባቸው አካባቢዎች ለሽያጭ እንደሚቀርብ አቶ ዮሴፍ አስረድተዋል።

በዘንድሮው የአርሶአደሮች የመስክ ጉብኝት አግኝተን ያነጋገርናቸው አጋዝ ትዛዙ ናማጋ እና አቶ ስራጅ ተሰማ በ2015 ዓ.ም በወረዳው በመደበኛ እና በበጋ መስኖ ስንዴ የተሰሩ ስራዎች አበረታች በመሆናቸው በቀጣይ ተሞክሮውን እንዲሰፋ እንሰራለን ብለዋል።

እንደ ተሳታፊዎቹ ገለጻ ከዚህ ቀደም ጥቅም ላይ ያልዋሉ ሰፋፊ መሬቶች በአትክልትና በበጋ መስኖ ስንዴ በመሸፈን እየተመዘገቡ ያሉ ውጤቶች ቁጭት የሚፈጥሩ መሆናቸው ተናግረዋል።

እንደ ተሳታፊዎቹ ገለጻ በሀገሪቱ የሚታዩ የድህነት፣ የስራ ጠባቂነትና የኑሮ ውድነት ጫናዎች ለመቋቋም ወጣቶች፣ ሴቶችና አርሶአደሮች ያላቸውን እምቅ አቅም መጠቀም ይጠበቅባቸዋል።

ወጣቶች ጊዜያቸው በአልባሌ ቦታ በማዋል ለደባል ሱስ እንዳይዳረጉ ከማድረግ ባሻገር ራሳቸው ከኢኮኖሚ ጥገኝነት ተላቀው የገቢ አቅም መፍጠር እንዲችሉ ግንዛቤ የፈጠረላቸው ይገባል። ለዚህ ደግሞ በአርሶ አደሮች የመስክ ጉብኝት የተሳተፉ ባለድርሻ አካላት የላቀ አስተዋጽኦ ማበርከት እንደሚጠበቅባቸው ገልጸዋል።

በእለቱ ከተጎበኙ ማሳዎች በያሚኒ የወጣቶች ማህበር የለማው የመስኖ ማሳ ተጠቃሽ ሲሆን 25 ሄክታር በተለያዩ አትክልቶች በመሸፈን አርአያነት ያለው ተግባር እያከናወነ ይገኛል።

የማህበሩ ሰብሳቢ በወጣት ዳንኤልን ሺፈታ እንደገለጸው ወጣቶች ከስራ ጠባቂነት ተላቀው በግብርና ስራ ቢሰማሩ ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ወጣት ዳንኤል ገልጿል ።

መንግስት በግብርና ዘርፍ ለሚሰማሩ ወጣቶች እያደረገ ያለው ተግባር አበረታች በመሆኑ በየአካባቢው የሚገኙ ወጣቶች ተግተው መስራት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።

ወጣቶች የወጣትነት ጊዜያቸው በአግባቡ በመጠቀም ከተቀጣሪነት ወደ ቀጣሪነት የሚሸጋገሩበት እድል ይፈጥርላቸዋል ብለዋል።

ያሚኒ የወጣቶች ማህበር ከ40 እስከ 100 ሰራተኞች በጊዜያዊነትና በቋሚነት ቀጥሮ የሚያሰራ ሲሆን እስከ 10ሺህ ብር ደሞዝ ይከፍላል። በመሆኑም ወጣቶች የማህበሩን ተሞክሮ በመቀመር ተግባራዊ ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው መልዕክት አስተላልፏል ሲል የዘገበው የጉራጌ ዞን የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ዘግቧል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *