በጉንችሬ ከተማና በእኖር ወረዳ ተከስቶ ለነበረው ማህበረሰባዊ ግጭት በጉራጌ የጆካ ሽማግሌ አባቶች ስላም ለማውረድ ሲደረግ የነበረው ጥረት የሰላም ፍሬ አፍርቶ የእርቁ ጅማሮ በአባቶች ተበስሯል።



================
ማህበረሰባችን ማንነቱን የመሠረተበት “እኛ” ብሎ የሚጠራበትን ውብ ማህበራዊ መስተጋብር የመሳሳትና የመሰበር ክስተቶች ሲገጥሙት እሩቅ ቅርብ ሳይሉ ካሉበት በመሠባሰብ፣ አብሮነቱንና ሰላሙን ለመመለስና ማህበራዊ ስብራቱን ለመጠገን ቀን ከሌት በሚተጉ የጃካ አባቶች፣ የቀዬው ተወላጆች ፣ ሙሁራኖች እና ባለሃብቶች እንዲሁ ሰላም ወዳድ በሆኑ አካላት በጉንችሬ በከተማና የእኖር ወረዳ ተከስቶ የነበረው ማህበረሰባዊ ግጭት ለመፍታት ሲደረግ የነበረው ጥረት ተሳክቶ የሰላም ፍሬ እያፈራ ይገኛል።

የጉራጌ ማህበረሰብ ለረጅም ዘመናት የአብሮነት ቋጠሮ ያሰገመደበት ፣ ዕርስ በዕርስ የተሰናሰለበት፣ የአንዱ መኖር ለሌላኛው መኖር ዋስትናው መሆኑን ያረጋገጠበት ፣ ማንነቱንና ስብዕናው የሚቀዳበት በትውልድ ጀረት ሁሉ የሚፀና ውብ የባህል መተዳደሪያ(ቂጫ) ያለው ማህበረሰብ ነው።

ይህንን ውብ እሴት ከትውልድ ትውልድ እንዲሸጋገር ጠብቀው ላቆዩልን የጆካ አባቶች ምስጋና ይድረስና ዛሬም በጉራጌ ዞን ጉንችሬ ከተማና እኖር ወረዳ ተፈጥሮ ለነበረው ወቅታዊ አለመግባባት ችግሩ ከተፈጠረበት ቀን ጀምሮ አካባቢው ወደ ሰላሙ ለመመለስ እና ተጨማሪ ውድመትና ግጭት እንዳይፈጠር “በኸተራት” ከማሰር ጀምሮ በርካታ መድረኮች ፈጥረው ከሁሉም ማህበረሰብ ከተውጣጡ ተወካዮችና በተለይም ግጭት ውስጥ የገቡት የሁለቱ ቤተ እምነት አማኞች ከያንዳንዳቸው 10 እና ከዚያ በላይ ተወካይ እንዲሰጡ በማድረግ ችግሩን ከስሩ ለመፍታት አድካሚና ተደጋጋሚ ውይይት ሲያደርጉ መቆየታቸው ይታወቃል።

ማህበረሰባችንን ወደ ቀደመ ሰላማዊ ኑሮ ለመመለስ ሲደረግ የነበረው ጥረት ተሳክቶ የሰላምና የእርቅ ሂደቱ ጅማሪውን አባቶች አብስረዋል። ለዚህም የከተማችን ማህበረሰብ እንኳን ደስ አላችሁ እያልን ማህበረሰባችን ገብቶበት ከነበረው የመገፋፋትና የመለያየት ውጥረት በመውጣት የቀደመ አብሮነቱን እንዲቀጥል ካለፈው ድርጊቱ ተፀፅቶ ከአጠገብ ካለው ጎረቤቱ ጀምሮ ይርቅታ እንዲያወርድ እና ሀሉም ወገን አሽናፊ መሆን የሚችልበትን የሰላም መንገድ እንዲጀምር አባቶች አሳስበዋል።

የሀይማኖት ተቋማት ፣ሙህራን ፣ወጣቶች ፣ሴቶች ፣ነጋዴ ባለሀብቶ ፣የማህበረሰብ አንቂዎች የመንግስት ስራ ሀላፊዎች እንዲሁም ነዋሪ ማህበረሰባችን ካለፈ ስህተት ተምሮ የሽማግሌዎች የሰላም ሃሳብ ፍሬ እንዲያፈራ ዘላቂ እንዲሆን ሊያግዝ ይገባል። በቀጣይ ጊዜያትም በየአከባቢው ከሚደረጉ የእርቅ ስርአቶችና ውይይቶች ባሻጋር የጋራ ህዝባዊ የእርቅ መድረክ እንደሚዘጋጅም ይጠበቃል።

በመጨረሻም በተለመደው ኢትዮጵያዊ የመተጋገዝና የመተባበር ባህል መሰረት የተጎጂዎች ጉዳት የሁሉ ከሃገር ውስጥና ውጭ ያለ ኢትዮጵያዊ ጉዳት ስለሆነ ሰራተኛው ፣ ነጋዴው፣ የከተማና የገጠር ነዋሪ ከእለት ጉርሳችን በመቀነስ የምንችለውን ሁሉ ድጋፍ በማድረግ ማቋቋም እና ወደ መደበኛ ስራቸው እንዲገቡ በማድረግ ለዘላቂ ሰላም መረጋገጥ የድርሻችን እንድንወጣም ጥሪ ቀርቧል።

መረጃውን ያደረሰን የከተማው መንግስት ኮሚኒኬሽን ነው።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *