በጉራጌ ዞን ጌታ ወረዳ ዛራ ቀበሌ በግንባታ ላይ የነበረው የጎንደራ ዘመናዊ መስኖ ፕሮጀክት ተጠናቆ ርክክብ ተፈፀመ፡፡

ግንባታውን ከገነባው መስፍን አስረስ የውሃ ስራና አጠቃላይ የኮንስትራክሽን ስራ ተቋራጭ ጋር ርክክቡን የፈፀሙት የጌታ ወረዳ ውሃ ማዕድንና ኢነርጂ ጽ/ቤት ሀላፊ አቶ ሚፍታ ሸሪፍ እንደገለፁት ፕሮጀክቱ በአጠቃላይ የፈጀው 3 ሚሊየን 692 ሺ 43 ብር AGP-2(Agricultural Growth Program ወይም የግብርና እድገት ፕሮግራም) በተባለ ግብረሰናይ ድርጅት የተሸፈነ ሲሆን ገንብቶ ለማጠናቀቅም ሰባት ወራትን ፈጅቷል ብለዋል፡፡

አቶ ሚፍታ አክለውም ለፕሮጀክቱ መሳካት በተለያየ መልኩ አስተዋፆ ላበረከቱ አካላት ምስጋና አቅርበው የመስኖ ግንባታው ሙሉ ለሙሉ ሲጠናቀቅ ከ 30 ሄ/ር በላይ በአካባቢው ለሚገኙ አርሶ አደሮች ለመስኖ ልማት ስራ ማስጠቀም የሚችል ሲሆን በቀጣይም ውስን ማስፋፊያ በመስራት በሁሉም አርሶ አደር ጓሮ ካናል የማስፋት፣ የከብቶች ውሃ ማጠጫና ልብስ ማጠቢያ ማስጠቀም እንዲችል ይደረጋል ብለዋል፡፡

የዚህ ታላቅ ፕሮጀክት ተጠቃሚ የሆኑት የአካባቢው አርሶ አደሮችም ግንባታውን በባለቤትነት በመጠበቅና በአመት ሶስት ጊዜ በማምረት ራሳቸውንና ቤተሰባቸውን ከመለወጥ ባሻገርም አሁን ላይ እየተስተዋለ የሚገኘውን የኑሮ ውድነት ከማረጋጋትም አንፃርም ከፍተኛ ሚና ልትጫወቱ ይገባል ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

በፕሮግራሙ ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የጌታ ወረዳ ትምህርት ጽ/ቤት ሀላፊና የወረዳው ዋና አስተዳዳሪ ተወካይ አቶ ሃብቱ ወ/የሱስ በበኩላቸው AGP-2(የግብርና እድገት ፕሮግራም) የተባለው ግብረሰናይ ድርጅት ከዚህ ቀደምም በፉቻሬና ወርከ ቀበሌዎች ላይ በተመሳሳይ የዘመናዊ መስኖ ገንብቶ አርሶ አደሩን እያስጠቀመ ያለ ፕሮጀክት መሆኑን አውስተው በግብርናው ዘርፍ እያደረገ ላለውን ዘርፈብዙ ድጋፍም አመስግነዋል፡፡

ይህ ግንባታ በተለይ መንግስት እንደ ሀገር አርሶ አደሩ በአመት ሁለት ጊዜ ብቻ ከማምረት ተላቆ ቢያንስ ሶስት ጊዜ በማምረት ሀገራችንን ከስንዴ ልመና ለማላቀቅ እየሰራ ባለበት በዚህ ወቅት መገንባቱና ከፍተኛ ውጤት ያስገኘልንን የዘንድሮ የበጋ መስኖ ስንዴ በቀጣይ በስፋት ለማምረት ለምናደርገው ጥረት ጉልህ አስተዋፆ የሚያበረክት ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡

አቶ ፈለቀ ፍቃዱ በጌታ ወረዳ ግብርና ጽ/ቤት የሰብል ኤክስቴንሽን ልማት ዘርፍ አስተባባሪና የጽ/ቤቱ ምክትል ሀላፊ ሲሆኑ በእለቱ በተናገሩት ንግግር በዘንድሮ የበጋ መስኖ ስንዴ በፉቻሬና ወርከ ቀበሌ ዘመናዊ መስኖዎች ከወረዳ አልፎ ለዞን ተሞክሮ የሚሆን ምርጥ ስራ መሰራቱን ጠቁመው የዚህ ግንባታ መጠናቀቅ የዛራ ቀበሌ አርሶ አደሮችም በቀጣይ የዚሁ እድል ተጠቃሚ እንዲሆን እድል የሰጠ በመሆኑ ንብረቱን በመጠበቅ በአመት ቢያንስ ሶስቴ በማልማት በምግብ ሰብል ራሳቸውን መቻል ይጠበቅባቸዋል ብለዋል፡፡

የቀበሌው አስተዳዳሪ አቶ ምስጋናው ተፈሪና በፕሮግራሙ ላይ የታደሙ አንዳንድ የአካባቢው አርሶ አደሮች በሰጡት አስተያየት ፕሮጀክቱ ተጠናቆ ለአገልግሎት ዝግጁ በመሆኑ መደሰታቸውን ገልፀው በቀጣይም ግንባታውን ከአደጋ በመጠበቅ በበልግና በመኸር ከሚያመርቱት ምርት በተጨማሪ በመስኖ በማልማት ከራሳቸው ባለፈ ለገበያ የሚሆን ምርት እናመርታለን ሲሉ ቃል ገብተዋል፡፡

በእለቱም በርክክብ ፕሮግራሙ ላይ የወረዳ አመራሮች፣ የAGP-2 ፕሮጀክት ፎካሎች፣ የፕሮጀክቱ ተጠቃሚ አርሶ-አደሮችና ሌሎች ጉዳዩ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ተሳታፊ ነበሩ ሲል ያደረሰን የወረዳው መንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ነው፡፡

በመረጃ ምንጭነት ገፃችን ምርጫዎ ስላደረጉ እናመሰግናለን!

= ኢትዮጵያን እናልማ!
= የፈረሰውን እንገንባ!
= ለፈተና እንዘጋጅ!
በተጨማሪም እነዚህ ሊንኮችን በመጫን ወቅታዊና ትኩስ መረጃዎቻችንን እንድትከታተሉ እንጋብዛለን፡፡
Facebook:- https://www.facebook.com/gurage1Zone
Website:- https://gurage.gov.et
Telegram:- https://t.me/comminuca
Youtub: -https://www.youtube.com/channel/UCzrcazGvvIO2tG7bQN

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *