በጉራጌ ዞን ጉመር ወረዳ በግብርናው በሁሉም መስኮች እየተከናወኑ ያሉ ስራዎች ውጤታማ በመሆናቸው ይበልጥ አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባ የጉመር ወረዳ አስተዳደር አስታወቀ።


በጉራጌ ዞን ጉመር ወረዳ በግብርናው በሁሉም መስኮች እየተከናወኑ ያሉ ስራዎች ውጤታማ በመሆናቸው ይበልጥ አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባ የጉመር ወረዳ አስተዳደር አስታወቀ።

በወረዳው በግብርና ዘርፍ እየተሰሩ ያሉ የልማት ስራዎች ባለድርሻ አካላት በተገኙበት የመስክ ምልከታ ተካሂዷል።

በመስክ ምልከታው የተገኙት የጉመር ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ደሳለኝ ከድር እንዳሉት የመስክ ምልከታው አላማ በወረዳው በዘርፉ እየተሰሩ ያሉ ስራዎች ላይ ምልከታ በማድረግ አበረታች ተግባራት ለማስቀጠልና ውስንነቶችን ለማረም ያለመ ነው።

በወረዳው በሌማት ትሩፋት የዶሮ መንደር በመመስረት እየተሰሩ ያሉ ስራዎች፣ በበልግ እርሻ ድንች፣ በአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ እና በመኸር እርሻ ቅድመ ዝግጅት እየተከናወኑ ያሉ ስራዎች አበረታች ናቸው ብለዋል።

በግብርናው ዘርፍ እየተሰራ ያለው የተሻለ ስራ በወረዳው በሁሉም ቀበሌዎች በማስፋት የአርሶ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እንደሚሰሩ ተናግረዋል።

የወረዳው ምክትል አስተዳዳሪና የግብርና ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ደገሙ አለሙ በወረዳው በሁሉም ዘርፍ እየተሰሩ ያሉ ስራዎች ውጤታማ ናቸው ብለዋል።

በወረዳው በሌማት ትሩፋት 7 የዶሮ መንደር በመመስረት ለእያንዳንዱ አርሶ አደር 25 ዶሮ መሰጠቱን ገልጸው አርሶ አደሩ የባለሙያ ምክረ ሀሳብ በመቀበል በተገቢው በመስራታቸው ተጠቃሚ ከመሆናቸው ባሻገር ወጣቶችም በዘርፉ ተደራጅተው በመስራት የእንቁላል ምርት በተመጣጣኝ ዋጋ ለማህበረሰቡ እያቀረቡ መሆኑንም ተናግረዋል።

አክለውም በዝርያ ማሻሻል፣ በንብ ማነብ፣ በበግ ማሞከት፣ በአሳ እርባታ እየተሰሩ ያሉ ስራዎች ላይ የህብረተሰቡ ተጠቃሚነት እያረጋገጠ እንደሚገኝ ኃላፊው ገልጸዋል።

ከዚህም ባለፈ በአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ ምርት መስጠት የማይችሉ መሬቶች ምርት እንዲሰጡ ጠረጴዛማ እርከን መሰራቱን ገልጸው እነዚህ መሬቶች በመኸር ወቅት በገብስ ከመሸፈን ጎን ለጎን መኖ መትከልና አሲዳማነቱ በኖራ ለማከም እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።

አያይዘውም በወረዳው 5 ነጥብ 5 ሚሊዮን ችግኝ በመንግስትና በፕሮጀክትና በማህበረሰብ ችግኝ ጣቢያዎች መዘጋጀቱን ገልጸው ለዚህም የወረዳው አግሮኢኮሎጂ የሚሆኑ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞች መዘጋጀቱንም ገልጸዋል።

የመስክ ምልከታው ተሳታፊዎች እንዳሉት በወረዳው በግብርናው ዘርፍ የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየተሰሩ ያሉ ስራዎች ተስፋ ሰጪ መሆናቸውን አንስተው መሰል ስራዎች በቀጣይም ይበልጥ አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባ አመላክተዋል።

በመስክ ምልከታው የወረዳው የስራ ኃላፊዎች፣ የምክር ቤት የኢኮኖሚ ዘርፍ ቋሚ ኮሚቴ፣ የወረዳው የግብርና የማናጅመት አካላትና ሌሎችም ተሳትፈዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *