በጉራጌ ዞን ገደባኖ ጉታዘር ወለኔ ወረዳ የትምህርት ቤት ቁሳቁስ ጨምሮ በ6.5 ሚሊየን ብር የተገነባው የገደባኖ፣ የተበተባንና የኢንጌ ሁለተኛ ደረጃና መሰናዶ ትምህርት ቤቶች ተመርቀው ለአገልግሎት ክፍት ሆኑ።

በወረዳው ትምህርት ቤቶቹ ተገንብቶ በመመረቃቸው ደስተኛ መሆናቸውን የአከባቢው ነዋሪዎች ተናገሩ።

በምረቃ ስነ ስርዓቱ ላይ የተገኙት የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳደር አቶ መሀመድ ጀማል እንደገለጹት ባለፉት አመታት መንግስት ህብረተሰቡን በማስተባበር ከአጋር ድርጅቶች ጋር በመሆን ትላልቅ ፕሮጀክቶችን መሰራታቸውን ጠቁመው ለህብረተሰቡ ትምህርት ተደራሽ እንዲሆን እያደረገው ያለው እገዛ ሰፊ መሆኑና በቀጣይም ጠናክሮ እንዲቀጥል ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል።

እንደ አስተዳዳሪው ገለጻ ሚዛን የሰላምና የልማት ማህበር በትምህርት ማስፋፊያ ፕሮጀክት ላይ ከሙስሊም ኤድ ዩኤስኤ ባገኘው የገንዘብ ድጋፍ በወረዳው የተሰራው ስራ የሚበረታታ መሆኑና በቀጣይም በዞኑ ያሉ የመሰረተ ልማት ችግሮችን ለመቅረፍ ሌሎችንም በማስተባበር እንደሚሰራም እምነታቸው የላቀ መሆኑና በዚህም የዞኑ መንግስት እገዛ እንደሚያደርግ ገልፀዋል ።

በወረዳው በርካታ የመሰረተ ልማት ችግሮች መኖራቸውን ያስታወቁት ዋና አስተዳዳሪው ህብረተሰቡ በምርጫ ወቅት ያነሳቸው የልማት ጥያቄዎችን ለመቅረፍ ህብረተሰቡና ባለሃብቱ በማስተባበር በትኩረት እንደሚሰራም ተናግረዋል።

የጉራጌ ዞን ትምህርት መምሪያ ኃላፊ አቶ ተሾመ ንዳ በበኩላቸው በዞኑ የትምህርት ተደራሽነት ለማስፋፋት የዞኑ ማህበረሰብ፣ ባለሀብቶች፣ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችና መንግስት በመቀናጀት በጋራ እየተሰራ ያለው ተግባር አበረታች ነው ብለዋል።

አክለውም ሚዛን የሰላምና የልማት ማህበር እየሰራው ያለው በጎ ተግባር በሌሎችም የዞናችን ክፍሎች ትውልድ የመታደግ ስራ በሰፊው እንዲሰሩና የበኩላቸውን እንዲወጡና ጠይቀው ለዚህም የዞኑ ትምህርት መምሪያ ከጎናቸው እንደሚሆንም ጠቁመዋል።

የገደባኖ ጉታዘር ወለኔ ወረዳ ዋና አስተዳደሪ አቶ ሙራድ ረሻድ እንደተናገሩት የልማት ማህበሩ የትምህርት ቤት ግንባታ በተጨማሪ ለተገነቡ ትምህርት ቤቶች ቁሳቁስን ጨምሮ 6 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር ወጪ ማድረጉንም አስረድተዋል።

በወረዳው የሚስተዋለውን የትምህርት ተደራሽነት ለመቅረፍ የወረዳው መንግስት ህብረተሰቡን በማስተባበርና ሚዛን የሰላምና የልማት ማህበር ጋር በመቀናጀት ከፍተኛ ርብርብ መደረጉን ያነሱት አቶ ሙራድ ለትምህርት ቤቶቹ ግንባታና ለውስጥ ግብአቶች መሟላት አስተዋጽኦ ላበረከቱ አካላት አመስግነዋል።

የሚዛን ሰላምና የልማት ማህበር ጠቅላላ ጉባኤ ሰብሳቢ አቶ ሶፊያን ሰይፉ ማህበሩ የአስቾካይ ሰብአዊ ድጋፍ ስራዎችን ጨምሮ በንፁህ መጠጥ ዉሃ አቅርቦት፣ በጤና ተቋማት ግንባታና አቅም ማጎልበት እንዲሁም በትምህርትና በሌሎች የስራ ዘርፎች ላይ በትኩረት እንደሚሰራም አመላክተዋል።

ማህበሩም በዛሬው እለት በገደባኖ ጉታዘር ወለኔ ወረዳ 3 የሁለተኛና መሰናዶ ትምህርት ቤቶች ማስፋፊያ ፕሮጀክቶችን አጠናቆ ማስመረቁን ገልጸዋል።

ለፕሮጀክቶቹ በስኬት መጠናቀቅ አስተዋጽኦ ላበረከቱ ለሙስሊም ኤይድ ዩኤስኤ፣ ለጉራጌ ዞን ፋይናንስ መምሪያ፣ ለወረዳው ፋይናንስና ኢኮኖሚ ልማት ፅ/ቤት፣ ለወረዳው ትምህርት ፅ/ቤትና ሌሎችም እገዛ ላደረጉ አካላት አመስግነዋል።

አቶ ሰይድና ከድር የገደባኖ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች ሲሆኑ ከዚህ በፊት በትምህርት ቤት ጥበትና በኮቪድ ወረርሽኝ ምክንያት ተጨናንቀው ይማሩ እንደነበር ጠቁመው አሁን ላይ ችግሩ በመቀረፉ መደሰታቸውን ገልፀዋል።

አቶ ጀማል ሙዘይድ የአከባቢው ነዋሪ ሲሆኑ ትምህርት ቤቱ በመገንባቱ ደስተኛ መሆናቸውንና በቀጣይም የተገነባውን ትምህርት ቤት የአከባቢው ማህበረሰብ በአግባቡ በመያዝ ለቀጣይ ትውልድ ማስተላለፍ አለብን ብለዋ።

በምረቃ ስነ ስርዓቱም ላይ የዞና የወረዳ ከፍተኛ አመራሮች፣ የአከባቢው ነዋሪዎችና ሌሎችም ባለድርሻ አካላት ተገኝቷል ሲል የዘገበው የጉራጌ ዞን የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ነው።

በተጨማሪም እነዚህ ሊንኮችን በመጫን ወቅታዊና ትኩስ መረጃዎቻችንን እንድትከታተሉ እንጋብዛለን፡፡
Facebook:- https://www.facebook.com/gurage1Zone
Website:- https://gurage.gov.et
Telegram:- https://t.me/comminuca
Youtub: -https://www.youtube.com/channel/UCzrcazGvvIO2tG7bQN36Cx

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *