በጉራጌ ዞን ደቡብ ሶዶ ወረዳ በ40 ሚሊዮን ብር ህብረተሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉ የተለያዩ የልማት ስራዎችን እያከናወነ መሆኑም የጉራጌ ልማትና ባህል ማህበር አስታወቀ፡፡

የጉራጌ ልማትና ባህል ማህበር ግሊመር ኦፍ ሆፕና ህብረተሰቡ በማስተባበር በጉራጌ ዞን በደቡብ ሶዶ ወረዳ እያስገነባቸው የሚገኙ የልማት ስራዎች በዞኑ ከፍተኛ አመራሮች ጉብኝት ተካሂዷል፡፡

በጉብኝቱ ወቅት ተገኝተው መልዕክት ያስተላለፉት የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ መሀመድ ጀማል እንደገለጹት የጉራጌ ልማትና ባህል ማህበር ግሊመር ኦፍ ሆፕና ከወረዳው አመራር ተቀናጅቶ ህብረተሰቡ በማስተባበር እያከናወናቸው የሚገኙ የትምህርት፣ የጤናና የንጹህ የመጠጥ ውሃ የልማት ስራዎች የህብረተሰቡን ቁልፍ የልማት ችግር የሚፈቱ ናቸው ብለዋል፡፡

የጉራጌ ልማትና ባህል ማህበር ከግሊመር ኦፍ ሆፕ የጀመራቸውን የልማት ስራዎች አጠናክሮ በማስቀጠል እና ሌሎችም ግብረ-ሰናይ ድርጅቶች ወደ ዞኑ እንዲመጡ በማድረግ የጀመረውን በልማት የመሳተፉ ስራ አጠናክሮ ማስቀጠል አንዳለበት አቶ መሀመድ ተናግረዋል፡፡

በዛሬው እለት ጉብኝት የተካሄደባቸው የልማት ስራዎች ውጤታማ እንዲሁኑ የሚመለከታቸው ሴክተር መስሪያ ቤቶችና የዞኑ አስተዳደር አስፈላጊው እገዛ የሚያደረጉ መሆናቸውን ዋና አስተዳዳሪው ገልጸዋል፡፡

የጉራጌ ልማትና ባህል ማህበር ዋና ዳይሬክተር አቶ ቅባቱ ተሰማ በበኩላቸው የጉራጌ ልማትና ባህል ማህበር ከአባላት፣ ከተለያዩ ረጂ ድርጅቶችና ከተለያዩ ገቢ ከሚያስገኙ ተቋማት ከሚገኘው ገቢ በዞኑ በተለያዩ አካባቢዎች የተለያዩ የልማት ስራዎች እየተሰራ ይገኛል ብለዋል፡፡

በዛሬው ዕለት በጉራጌ ዞን በደቡብ ሶዶ ወረዳ ጉብኝት የተካሄደባቸው የትምህርት፣ የጤናና የንጹህ መጠጥ ውሃ የግንባታ ፕሮጀክቶች ዘጠና ከመቶ የሚሆነው ወጪ ከግሊመር ኦፍ ሆፕ ከተሰኘ ግብረ-ሰናይ ድርጅት በተገኘ ከፍተኛ የገንዘብ ድጋፍ እና ቀሪው አስር ከመቶ በህብረተሰብ ተሳትፎ በማድረግ በመገንባት ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

የጉራጌ ልማትና ባህል ማህበር ከግሊመር ኦፍ ሆፕ ጋር የአንድ ዓመት ውል በመግባት እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር 2021 ለማጠናቀቅ ስምንት የመካከለኛ ጥልቅ ጉድጓድ የንጹህ መጠጥ ውሃ ቁፋሮ ለማድረግ ከተያዘው ውስጥ 6ቱ ተቆፍረው ውሃ ማግኘት የተቻለ ሲሆን በተመሳሳይ አንድ ጥልቅ ጉድጓድ ውሃ ቁፋሮ ተጠናቆ በሰከንድ ከ22 ሊትር በላይ ውሃ መስጠት የሚችል መሆኑን ዋና ዳይሬክተሩ ገልጸዋል፡፡

በተመሳሳይ የጎጊቲ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ግንባታ በ10 ነጥብ 8 ሚሊዮን ብር ወጪ እንዲሁም በቆላ ኑራላ ዘዘሙቴ በሚባል አካባቢ የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ማስፋፊያ የብሎክና የሽንት ቤት ግንባታ በከፍተኛ ፍጥነት በመገንባት ላይ የሚገኙ መሆናቸውን የገለጹት አቶ ቅባቱ ተሰማ በወረዳው በግንባታ ሂደት ላይ የሚገኙ የልማት ስራዎች 40 ሚሊዮን ብር ወጪ የሚደረግባቸው ናቸው ብለዋል፡፡

በደቡብ ሶዶ ወረዳ የግሊመር ኦፍ ሆፕ ፕሮጀክት አስተባባሪ አቶ ፀጋዬ ተሊላ እንደገለጹት ከጉራጌ ልማትና ባህል ማህበር ጋር በገባው ውል መሰረት ከአምስት አመቱ ፕሮግራም ውስጥ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር የ2021 የትምህርት፣ የጤናና የንጹህ መጠጥ ውሃ ግንባታ ፕሮጀክቶች በመከናወን ላይ ናቸው ብለዋል፡፡

አክለውም ግሊመር ኦፍ ሆፕ በመንግስት ሊሸፈኑ ያልቻሉ የልማት ክፍተቶችን በመሙላት ዜጎች ተጠቃሚ በሚያደርጉ የልማት ስራዎች ላይ ከፍተኛ ተሳትፎ በማድረግ ላይ የሚገኝ መሆኑን አቶ ፀጋዬ ተሊላ ገልጸዋል፡፡

የደቡብ ሶዶ ወረዳ የውሃና ማዕድን ኤነርጂ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ታሪኩ በሬሳ በበኩላቸው በወረዳው በሚገኙ 18 ቀበሌዎች ውስጥ ከፍተኛ የውሃ ችግር መኖሩን ጠቁመው በጉራጌ ልማትና ባህል ማህበር አስተባበሪነት በግሊመር ኦፍ ሆፕ ቁፏሮ የተጠናቀቀው ጥልቅ የጉድጓድ ውሃ የኬላ ከተማ ንጹህ የመጠጥ ውሃ እጥረት ችግር ይቀርፋል ብለዋል፡፡

በጉብኝቱ የዞን፣ የጉልባማ፣ የደቡብ ሶደ ወረዳ አመራሮችና የሚመለከታቸው ሴክተር መስሪያ ቤት ባለሙያዎች ተሳታፊ ነበሩ ሲል የዘገበው የጉራጌ ዞን የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ነው፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *