በጉራጌ ዞን የ2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች የዘማች ቤተሰቦችና የመከላከያ ሰራዊት የድጋፍ ጥሪ ዘመቻ ጀምረዋል።

ለሀገራችን የህልዉናዉ ጦርነት በግንባር ተገኝተዉ እየተዋደቁ ለሚገኙ የዘማች ቤተሰቦች ወጣቶች ፣ተማሪዎችና ሌሎችም የህብረተሰብ ክፍሎች ሰብል የማንሳትና ሀብት የማሰባሰብ ስራ እየተሰራ እንደሆነም የጉራጌ ዞን ብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት አስታወቀ።

የያበሩስ አጠቃላይ ሁለተኛደረጃና መሰናዶ ትምህርት ቤት ተማሪዎች ፣ መምህራን፣ የአስተዳደር ሰራተኞችና ሌሎችም ባለድርሻ አካላቶች በቀቤና ወረዳ ጫንጮ ዉጥኝ ቀበሌ የዘማች ቤተሰብ ሰብል የማሰባሰብ ስራ ተሰርተዋል።

የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ለሰብል አሰባሰብና ለዘማች ቤተሰቦች ድጋፍ ለማድረግ የተደረገ ሀገራዊ ጥሪ ተከትሎ የተለያዩ የድጋፍ መርሃግብሮች ተዘጋጅተው እየተከናወኑ ሲሆን ሰብል መሰብስብ፣ ድጋፍ ማሰባሰብ፣ የዘማች ቤተሰቦችን ማገዝ እና ደም የመለገስ መርሀ ግብር እየተከናወነ ይገኛል።

በአጨዳዉ ወቅት የተገኙት የጉራጌ ዞን የመንግስት ረዳት ተጠሪ አቶ አለማየሁ ገብረመስቀል እንዳሉት በቀቤና ወረዳ ጫንጮ ዉጥኝ ቀበሌ የአንድ ዘማች ቤተሰብ በመኸር ወቅት ያለማዉን የጤፍ ማሳ እሱ በግንባር እየተዋደቀ ሲሆን የያበሩስ ሁለተኛና መሰናዶ ትምህርት ቤት ተማሪዎች ፣ መምህራን ፣ የዞንና የወረዳዉ አመራር ፣የወጣቶችና የሴት አደረጃጀቶች በተገኙበት ሰብል የማሰባሰብ ስራ ተሰርቷል።

የጠቅላይ ሚኒስትሩ ሀገራዊ ጥሪ በመቀበል በጉራጌ ዞን በሁለም አካባቢዎች የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ለአንድ ሳምንት በመዝጋት ተማሪዎች መምህራን አንድ ላይ በመሆን ሰብል የማሰባሰቡ ስራ እየተሰራ እንደሆነም አስረድተዋል።

በተለይም ለሀገራችን የህልዉናዉ ጦርነት በግንባር ተገኝተዉ እየተዋደቁ ለሚገኙ የዘማች ቤተሰበች እንዳይባዝኑና ባይተዋርነት እንዳይሰማቸዉ ወጣቶች ፣ተማሪዎችና ሌሎችም የህብረተሰብ ክፍሎች ሰብል የማንሳትና ሀብት የማሰባሰብ ስራ እየተሰራ እንደሆነም ተናግረዋል።

የጉራጌ ዞን ትምህርት መምሪያ ኃላፊ አቶ አስከብር ወልዴ እንዳሉት በሀገራችን እየተካሄደ ባለዉ የህልዉና ዘመቻ በኢኮኖሚ ለመደገፍ በዞኑ የሚገኙ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ለአንድ ሳምንት የሚቆይ ለዘማች ቤተሰቦች እህል የማሰባሰብ ፣ ገንዘብ በማሰባሰብ ለመከላከያ ድጋፍ የማድረግ እንቅስቃሴ ላይ እንገኘለን ብለዋል።

እያንዳዱ ተማሪ ከቤተሰብ ለምግብ ከሚያገኘዉ ገቢ መከላከያዉ ለመደገፍ በተደረገዉ እንቅስቃሴ ከ2 ነጥብ 2 ሚሊየን ብር በላይ ከተማሪዎች የማሰባሰብ ስራም መሰራቱም አብራርተዋል።

በዚህ ሳምንት በዞኑ የገቢ አሰባሰቡ ስራ አጠናክሮ በማስቀጠል ከ 7 ሚሊየን ብር በላይ ከተማሪዎች ብቻ ለማሰባሰብ መታቀዱም አስታዉቀዉ እያንዳንዱ መምህራን ከዚህ በፊት ከደሞዛቸዉ 20 ፐርሰንት በመወሰን የሰጡ መሆኑም ይታወቃል ብለዉ የህልዉናዉ ዘመቻ ለማጠናከር መምህራኖች ከደሞዛቸዉ ተቀናሽ በማድረግ ለመከላከያ ሰራዊት ገቢ እንዲደረግ ጥረት እየተደረገ እንደሆነም አብራርተዋል።

በአንደኛ ደረጃም ትምህርት ቤት የሚገኙም መምህራኖች እንደዚሁ ከደሞዛች ለሀገር መከላከያ ሰራዊት ድጋፉ እንዲያደርጉ እየተደረገ እንደሆነም አመላክተዉ በዞኑግን በተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ ተማሪዎች እና መምህራን ሰብል የመሰብሰብ፣ ደም የመለገስ እና ሌሎች ማህበራዊ አገልግሎቶችን ላይ በስፋት እየተሰራበት እንደሆነም አስረድተዋል።

በአጨዳ ፕሮግራሙ ላይ ያነጋገርናቸዉ አንዳንድ ያአበሩስ ሁለተኛና መሰናዶ ትምህርት ቤት ተማሪዎች በሰጡት አስተያየት በጎ ስራ መስራት ለራስ ነዉ ብለዉ ሁሉም ሰዉ በሀገራችንም ጉዳይ ላይ ተሳትፎአችን ማሳየት አለብን ብለዋል።

ሀገርን ለማዳን የዘመቱ ቤተሰቦች ምርት የማሰባሰብ ስራዉ ማገዝ ግዴታችንም ጭምር ነዉ የሚሉት ተማሪዎቹ በመተባበር በዘር በሀይማኖት ሳንለያይ አንድ በመሆን አገራችን ከዉስጥና ከዉጭ የተቃጣባትን አደጋ በመከላከል የሀገራችን ልማት ማስቀጠል እንደሚገባም ተናግረዋል።

በጫንጮ ዉጥኝ ቀበሌ ምርት የተሰበሰባላቸዉ የዘማች ቤተሰብ ወላጅ አባት አርሶአደር በሻ አልያ እና ወላጅ እናት አንበዛች ሰይድ በሰጡት አስተያየት ልጃቸዉ ሀገራዊዉ ጥሪዉን ተቀብሎ ግንባር በመዝመት ሀገርን ለማፈራረስ የተነሳዉን አሸባሪዉን የህወሃት ቡድን ዋጋዉን ለመስጠት የድርሻዉን እየተወጣ ይገኛል ብለዋል።

ልጃቸዉ ሰራዊቱን ሳይቀላቀል በፊት በጣም ያግዛቸዉ እንደነበረና ለምርት አሰባሰቡ ብዙ ጊዜና ጉልበት ያባክኑ እንደነበረም ጠቅሰዉ ዛሬ በተማሪዎችና በሌሎችም ተሳታፊዎች የተደረገላቸዉ የሰብል አጨዳ ስራ ይህንኑም እንዳስቀረላቸዉም ተናግረዉ ለዚህም ልዩ ምስጋናም አቅርበዋል ሲል የዘገበዉ የጉራጌ ዞን መንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ነዉ።

-አካባቢህን ጠብቅ !

  • ወደ ግንባር ዝመት !
  • መከላከያን ደግፍ !

በተጨማሪም እነዚህ ሊንኮችን በመጫን ወቅታዊና ትኩስ መረጃዎቻችንን እንድትከታተሉ እንጋብዛለን፡፡
Facebook:- https://www.facebook.com/gurage1Zone
Website:- https://gurage.gov.et
Telegram:- https://t.me/comminuca
Youtub: -https://www.youtube.com/channel/UCzrcazGvvIO2tG7bQN36Cx

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *