በጉራጌ ዞን የጥምቀት በዓል ሀይማኖታዊ ስርዓት በመጠበቅ በሰላምና በደማቅ ሁኔታ ተከብሯል።

የጥምቀት በዓል በዩኔስኮ በማይዳሰስ ቅርስነት የተመዘገበ ሀይማኖታዊ በዓል በመሆኑ ይህንን ቅርስ ተንከባክቦ በመጠበቅና ለአለም ይበልጥ በማስተዋወቅ የቱሪዝም ሀብትነቱን ማሳደግ እንደሚገባ የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ መሀመድ ጀማል ገለጹ።

በወልቂጤ ከተማ በጥምቀተ ባህር ተገኝተው ለህዝበ ክርስቲያኑ የበአሉ መልዕክት ያስተላለፉት የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ መሀመድ ጀማል እንደገለጹት የጥምቀት በዓል በዩኔስኮ በማይዳሰስ ቅርስነት የተመዘገበ ሀይማኖታዊ በዓል በመሆኑ ይህንን ቅርስ ተንከባክቦ በመጠበቅና ለአለም ይበልጥ በማስተዋወቅ የቱሪዝም ሀብትነቱን ማሳደግ ይገባል።

እንደ አቶ መሀመድ ገለፃ የዘንድሮ የጥምቀት በዓል ለየት የሚያደርገው የመንግስት ጥሪ ተቀብለው የመጡ በውጭ ሀገር የሚኖሩ ትውልደ ኢትዮጵያውያን በናፈቋት ሀገራቸው ከወገኖቻቸው ጋር በዓሉን የሚያከብሩት በመሆኑ ነው ብለዋል ።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ሀገረ መንግስት ግንባታ ላይ የራሷ ትልቅ አሻራ ያላት እንደመሆኗ መጠን ዛሬ የገጠመንን የህልውና አደጋ ለመቀልበስ እየተደረገ ባለው ትግል ከሌሎች የሀይማኖት ተቋማት ጋር በመሆን ያለፈ ታሪኳ እየደገመች እንደምትገኝም ዋና አስተዳዳሪው ገልጸዋል።

አክለውም በዚህ ታሪካዊና ወሳኝ ወቅት የሀገር ህልውና ለማዳንና ለማፅናት በቀጣይነት በሚደረገው ትግል ቤተክርስቲያኒቱ የጀመረችውን ዓርአያነት ያለው ተግባር በማስቀጠል አሁን ላይ በጠላት ጥቃት የደረሰባቸውን ወገኖች በማቋቋምና የሀገራችን ሠላምና ደህንነት አስተማማኝ ደረጃ ላይ ለማድረስ በሚደረጉ ሀገራዊ ጥሪዎች አንድነታችንን በማጠናከር ከመቼውም በላይ በጋራ መቆም አለብን ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል።

አያይዘውም ህዝበ ክርስቲያኑ በዓሉ ሲያከብር የተቸገሩትን በመርዳት፣ የተራቡትን በማብላት፣ የተጠሙትን በማጠጣት በፈጣሪ ዘንድ የተወደደና ማህበራዊ ግዴታ እየተወጣን ሊሆን እንደሚገባ ገልጸው ህብረተሰቡ በዓሉ በሰላም ተጀምሮ እስኪጠናቀቅ የአከባቢውን ጸጥታ ነቅቶ መጠበቅ አለበት ብለዋል።

የወልቂጤ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ እንዳለ ገብረመስቀል በበኩላቸው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ኢትዮጵያ በቱሪዝም ተመራጭ የሚያደርጓት በርካታ መስህቦች ለሀገር ያበረከተች ባለውለታ መሆንዋን ተናግረዋል።

አሸባሪዎቹ ሕወኃትና ሸኔ ተባብረው በከፈቱብን ጦርነት በሀገሪቷና በህዝቦቿ ላይ ሰብዓዊ፣ ኢኮኖሚ፣ ማህበራዊ እንዲሁም የስነ ልቦና ጫና የደረሰብን ቢሆንም በኢትዮጵያዊያን የተባበረ ክንድ የወራሪዎቹ አከርካሪ በወሳኝ መልኩ ተመተዋል ብለዋል።

ይሁን እንጂ የሀገራችን የግዛት አንድነት ለመነጣጠል በርካታ ሴራዎች እየተሴረብን በመሆኑ ህዝበ ክርስቲያኑ ሀይማኖቱን በመጠበቅና የሌላውም ሀይማኖት በማክበር ክርስቲያናዊ በሆነ ስነ ምግባር የመረዳዳትና የመከባበር ባህላዊ እሴቶቹን ሊያጎለብት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

አክለውም ህዝበ ክርስቲያኑ በዓሉ ሲያከብር በሰሜንና በምስራቅ ኢትዮጵያ በዓሉ ለማክበር ያልታደሉትን እህት ወንድሞቻችን በማቋቋም አለኝነታችን በተግባር በማረጋገጥ ክርስቲያናዊ ግዴታችንን መወጣት አለብን ብለዋል።

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የጉራጌ ሀገረ ስብከት ዋና ስራ አስኪያጅ መጋቢ ስብሃት ሳህሉ ተሰማ እንዳሉት የበዓሉ ዋና አላማ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ከገሊላ ተነስቶ ወደ ዮርዳኖስ በመውረድ በቅዱስ ዮሐንስ እጅ በመጠመቅ የአዳም ልጆች የእዳ ደብዳቤያቸውን የቀደደበትና ህዝበ ክርስቲያኑ የመንፈስ ቅዱስ ልጅነት ያገኙበት በአል ነው ብለዋል።

አክለውም ህዝበ ክርስቲያኑ ጽድቅ ሊፈጽምና በጽድቅ ሊመላለስ ይገባል ብለዋል።

የጥምቀት በዓል ሲያከብሩ አግኝተን ያነጋገርናቸው አንዳንድ የበዓሉ ታዳሚዎች በሰጡት አስተያየት የዘንድሮ በዓል ለየት ባለና በደመቀ መልኩ መከበሩን ገልፀው ወጣቶች ከፀጥታ አካላት ጎን በመሆን ያለምንም የፀጥታ ችግር በሰላም ማክበራቸውንም ገልጸዋል።

አስተያየት ሰጪዎቹ አክለውም ህዝበ ክርስትያኑ በዓሉ ሲያክብር የተቸገሩትን በመርዳት ሀይማኖታዊ ግዴታችን በመወጣት ሊሆን ይገባል ብለዋል ሲል የዘገበው የጉራጌ ዞን የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ነው።

= ኢትዮጵያን እናልማ!
= የፈረሰውን እንገንባ!
= ለፈተና እንዘጋጅ!

በተጨማሪም እነዚህ ሊንኮችን በመጫን ወቅታዊና ትኩስ መረጃዎቻችንን እንድትከታተሉ እንጋብዛለን፡፡

Facebook:- https://www.facebook.com/gurage1Zone
Website:- https://gurage.gov.et
Telegram:- https://t.me/comminuca
Youtub: -https://www.youtube.com/channel/UCzrcazGvvIO2tG7bQN36Cx

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *