በጉራጌ ዞን የተጀማመሩ የካፒታል ፕሮጀክት ስራዎች በወቅቱ ተጠናቀው ለህብረተሰቡ አገልግሎት እንዲሰጡ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በትኩረት እንደሚሰራ የማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ፕላንና ልማት ቢሮ አስታወቀ።


የህብረተሰቡ የልማትና የመልካም አስተዳደር ችግር ለመቅረፍ በካፒታል ፕሮጀክቶች ላይ አስፈላጊውን ቁጥጥርና ድጋፍ እያደረገ መሆኑ የጉራጌ ዞን ፕላንና ኢኮኖሚ ልማት መምሪያ ገለጸ።

የማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ፕላንና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ፣የጉራጌ ዞን ፕላንና ኢኮኖሚ ልማት መምሪያና የሚመለከታቸው አካላት በጉራጌ ዞን የሚከናወነው የካፒታል ፕሮጀክቶች በበጀትና በተግባር አፈጻጸም ያሉበት ሁኔታ አስመልክቶ የመስክ ምልከታ አድርገዋል።

የማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ፕላንና ልማት ቢሮ የልማት ፕሮጀክቶች ዳይሬክተር አቶ ብርሀኑ ፋንታ እንደገለፁት በመጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶች፣ በመስኖ ልማት ፕሮጀክቶች ፣በጤናና እና በኢንድስትሪ ፓርኮችና ላይ የመስክ ምልከታ ማድረጋቸው ተናግሯል።

የወልቂጤ ሆስፒታል በጥራትና በፍጥነት አሁን እየተሰራ ያለው ስራ ጥሩ በሆንም ከኤሌክትሮ ሜካኒካል እና ከሳይት ወርክ ዲዛይን መጀመርያ በጫረታ ውሉ ላይ አለመካተቱ ተግዳሮት እንደሆና ችግሩ እንዲፈታ ከሚመለከተው አካል ጋር መግባባት መቻሉ ገልጸዋል።

አቶ ብርሀኑ አያይዘውም በሌሎች መዋቅሮችም የጤና ጣቢያ፣የፋርማሲ፣የቀዶ ጥገና ማእከላት ግንባታ ቀሪ ስራዎች ያሉ ሲሆን የሀዋርያት ሆስፒታልም ሙሉ ግብአቶች ተሟልቶለት አገልግሎት እንዲሰጥ በትኩረ መስራት ይጠይቃል ነው ያሉት።

በክልሉ የመጠጥ ውሃና የመስኖ ፕሮጀክት ስራዎች ጨምሮ በርካታ ፕሮጀክቶች ቢኖሩም በመዋቅር አደረጃጀት ምክንያት መስተጓጎል መግጠሙ የገለጹት አቶ ብርሀኑ ለአብነትም በሙህር አክሊል ወረዳ የከሬብ መስኖ በቸሀ ወረዳ የመጌች መስኖና በሌሎች ወረዳዎችም በርካታ ፕሮጀክቶች የዚህ ችግር ተቋዳሽ መሆናቸው አብራርተዋል።

ይሁን እንጂ በአፈጻጸም እና በጥራት በጥሩ ሁኔታ ያሉና በአጭር ጊዜ ውስጥ ህብረተሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ፕሮጀክቶች መኖራቸው ገልጸው በዘንድሮ አመት የሚጠናቀቁና በጥራትና በሌሎች ጉዳዮች ወደ ቀጣይ አመት የሚሸጋገሩ ግዙፍ ፕሮጀክቶች የትኞቹ እንደሆኑ የመለየት ስራ መሰራቱ ገልጸዋል።

በጉራጌ ዞን በሚከናወኑ የካፒታል ፕሮጀክቶች በጥራትና በፍጥነት ከመስራት አንጻር አበረታች ናቸው ያሉ ሲሆን ሌሎች የተጀማመሩ የካፒታል ፕሮጀክት ስራዎች በወቅቱ ተጠናቀው ለህብረተሰቡ አገልግሎት እንዲሰጡ ከክልል እና ከፌደራል ከሚመለከታቸው ተቋሟት ጋር በትኩረት እንደሚሰራ አቶ ብርሀኑ አስታውቀዋል።

የክልሉ የግብርናና የገጠር ልማት ቋሚ ኮሚቴና የፌደሬሽን ምክር ቤት አባል ወ/ሮ አሰለፈች ሀይሌ በመስክ ምልከታው እንዳሉት በፋይናስና በግብዓት አቅርቦት ችግር እየተጓተቱ ያሉ ፕሮጀክቶች እንዲጠናቀቁ እና ህብረተሰቡ የፕሮጀክቶቹ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ባለድርሻ አካላት ተቀናጅተው ሊሰሩ ይገባል ብለዋል።

ወጣቶች የኢኮኖሚ ተጠቃሚ ለማደረግ ተደራጅተው ወደ ተግበራው በሚገቡበት ወቅት የሚያጋጥማቸው የመብራት ችግር ሊፈታላቸው እንደሚገባና እና የገበያ ትስስር ሊፈጠርላቸው ይገባል ብለዋል።

የጉራጌ ዞን ፕላንና ልማት መምሪያ ኃላፊ አቶ ከበደ ኃይሌ እንደተናገሩት በዞኑ በክልል እና በፌደራል ደረጃ በጥራትና በፍጥነት እየተከናወኑ ያሉ በዙ የካፒታል ፕሮጀክቶች ያሉ ሲሆን በተያዘላቸው ጊዜ ግን አለመጠናቀቃቸው የህብረተሰቡ የመልካም አስተዳደር ችግር እየሆኑ ይገኛሉ።

እነዚህ በተለያዩ ዘርፎች ያሉ ግዙፍ ፕሮጀክቶች ቢጠናቀቁ የህብረተሰቡ የልማትና የመልካም አስተዳደር ችግር በቀላሉ መቅረፍ የሚችሉ በመሆናቸው መምሪያውም በካፒታል ፕሮጀክቶች ላይ አስፈላጊውን ቁጥጥርና ድጋፍ እያደረገ ይገኛል ብለዋል።

በዘንድሮ አመትም ከሚመለከታቸው ሴክተር ተቋማትና ጋር በመሆን 39 ፕሮጀክቶች ያሉበት ደረጃ መመልከታቸው አስታውሰዋል።

ለአብነትም የከሬብ መስኖ ፕሮጀክት ሲጠናቀቅ 1ሺ 2መቶ ሄክታር መሬት የሚያለማ ሲሆን የመጌች መስኖ ፕሮጀክት በፌዝ አንድ 1ሺ 3መቶ 47 በፌዝ ሁለት ደግሞ 1ሺ 200 ሄክታር መሬት ማልማት የሚችሉና ለበርካታ ህብረተሰብ አገልግሎት የሚሰጡ ብሎም ለሀገር ኢኮኖሚ እድገት ጉልህ ሚና ያላቸው መሆናቸው አብራርተዋል።

አቶ ከበደ አክለውም የወልቂጤ እና የሀዋርያት ሆስፒታሎች በአሁን ሰአት በጥራት እና በፍጥነት እየተሰሩ ያሉ ስራዎች ጥሩ ቢሆኑም መሟላት ያለባቸው ቁሳቁሶችና በቀሪ ተግባራት ላይ ከሚመለከተው አካል ጋር በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝ ተናግሯል።

የጋዜቦ የውሃ ፕሮጀክትም በክልሉ መንግስት ጫረታ ወጥቶ ስራው እየተሰራ የነበረ ቢሆንም አሁን ግን ድጋሚ ጫረታ ወጥቶ ስራ መጀመሩ አመላክተዋል።

በእንደጋኝ ወረዳ የደብረ ጽጌ እና በጉመር ወረዳ የጀንቦሮ ጤና ጣበያ OR ብሎኮች ግንባታ እንዲጠናቀቁ ምልከታ በመደረጉ ምላሽ እንዲያገኙ በአጽንኦት ይሰራል ብለዋል አቶ ከበደ ሀይሌ።

የእነዚህ ፕሮጀክቶች መጓተት ምክንያት የክልሉ መዋቅር መበታተን፣ የበጀት እጥረት፣የገበያ ንረት፣በአንድ አንድ አካባቢዎች የሰላም እጦት እና ሌሎችም መንስኤዎቹ ናቸው ያሉት ኃላፊው ፕሮጀክቶች በጊዜ እና በጥራት እንዲጠናቀቁ ቲም ተዋቅሮ በበጀት እንዲደገፉ በትኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *