በጉራጌ ዞን የሚገኙ ሁለገብ የገበሬዎች ህብረት ስራ ዩኒየኖች የግብርናውን ዘርፍ ከማዘመን ጎን ለጎን የዋጋ ንረትን ለመከላከል የግብርና ውጤቶች በተመጣጣኝ ዋጋ ለማቅረብ መሰራት እንደሚጠበቅባቸው የዞኑ ህብረት ስራ ልማት ጽህፈት ቤት አስታወቀ ።

ምርትና ምርታማነትን የሚያሻሽሉ የተለያዩ የቴክኖሎጂ ውጤቶች በማቅረብ አርሶአደሮች ተጠቃሚ ለማድረግ እየሰሩ እንደሚገኙ በጉራጌ ዞን የሚገኙ የሁለገብ የገበሬዎች ህብረት ስራ ዩኒየኖች ገለፁ፡፡

የጽህፈት ቤቱ የማኔጅመንት አባላት የዩኒየኖቹን የስራ እንቅስቃሴ ጎብኝተዋል።

በጉራጌ ዞን የግብርና ግብዓትና የሰብል ምርቶችን በማቅረብ የዋጋ ንረት በመከላከል ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያደረጉ ከሚገኙ ዩኒየኖች መካከል “ዋልታ ሁለገብ የገበሬዎች ህብረት ስራ ዩኒየን” እና “እድገት የዘር ብዜትና ግብይት ህብረት ስራ ዩኒየን” ተጠቃሾች ናቸው፡፡

የጉራጌ ዞን ህብረት ስራ ልማት ጽህፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሮ ትብለጥ እስጢፋኖስ እንደገለጹት እድገት ምርጥ ዘር ብዜትና ግብይት ህብረት ስራ ዩኒየን ምርታማነታቸው እና ጥራታቸው የተረጋገጠ የስንዴ፣ የጤፍ፣የባቄላ እና የመሳሰሉትን ምርጥ ዘሮችን በማባዛት ለአርሶ አደሩ በተመጣጣኝ ዋጋ እያቀረበ ይገኛል ብለዋል፡፡

ዩኒየኑ በሀገሪቱ እየተስተዋለ ያለው የምርጥ ዘር አቅርቦት እጥረት ችግር ለመቅረፍ እየሰራ ሲሆን ለክልሉ አርሶአደሮች በማቅረብ አርአያነት ያለው ተግባር እያከናወነ እንደሚገኝ ገልጸዋል ።

ሌላው ዋልታ ሁለገብ የገበሬዎች ህብረት ስራ ዩኒየን የግብርና ግብዓትና የሰብል ምርቶችን በማቅረብ የዋጋ ንረት ለመከላከል እየሰራ ይገኛል ያሉት ኃላፊዋ
ዩኒየኑ ከምርጥ ዘር፣ ከእንስሳት መኖ አቅርቦት ባሻገር ምርትና ምርታማነትን ሊያሳድጉ የሚችሉ የተለያዩ የአፈር ማዳበሪያዎችና ኬሚካሎችን እንደሚያቀርብ ገልፀዋል፡፡

ዩኒየኑ አርሶ አደሮች ምርት በሚሰበስቡበት ወቅት በተመጣጣኝ ዋጋ በመግዛት ለተቋማትና ለሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች በተመጣጣኝ ዋጋ እያቀረበ እንደሚገኝ ነው ወይዘሮ ትብለጥ የተናገሩት፡፡

ዩኒየኖቹ ለበርካታ ዜጎች የስራ እድል በመፍጠር ዜጎች ተጠቃሚ እንዲሆኑ ከማስቻል በተጨማሪ በዞኑ ወላጅ አጥ ለሆኑ ህጻናትና ሌሎች ድጋፍ የሚሹ የህብረተሰብ ክፍሎች በመርዳት ማህበራዊ አገልግሎት እየሰጡ እንፈሚገኙ አብራርተዋል።

በመሆኑም ዩኒየኖቹ በቀጣይ አድማሳቸውን በማስፋት ማህበረሰቡን በስፋት ተጠቃሚ እንዲያደርጉ በቅንጅት መስራት ያስፈልጋል ብለዋል ።

የእድገት የዘር ብዜትና ግብይት ህብረት ስራ ዩኒየን ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ተሰማ አለማየሁ እንደተናገሩት ዩኒየኑ ከ2003 ጀምሮ የአርሶ አደሩ የምርጥ ዘር አቅርቦት ችግር ለመቅረፍ እየሰራ ይገኛል፡፡

በተጨማሪም ዩኒየኑ ዘር አባዥ ለሆኑ አባል መሰረታዊ ህብረት ስራ ማህበራት አርሶ አደሮች ለዘር ብዜት የሚሆን ገንዘብ ብድር የማመቻቸት፣ ሙያዊ እና ሌሎች አስፈላጊ የሆኑ የድጋፍና ክትትል ስራዎች ይሰራሉ ብለዋል፡፡

ባለፉት ዓመታት ዩኒየኑ መነሻ ዘሮችን ለማገኘት ይቸገር እንደነበር የተናገሩት አቶ ተሰማ አለማየሁ አሁን 85 በመቶ የሚሆነውን መነሻ ዘር ለሌሎች አርሶ አደሮች እንደሚያቀርቡ አስረድተዋል ።

በአከባቢው ያለው አርሶ አደር የሚፈልገው ዘር ብቻ በመለየት መነሻ ዘሮችን በማባዛት እንዲጠቀሙ ማድረጋቸውን የገለጹት ዋና ስራ አስኪያጁ ለዘንድሮ መኸር 6ሺህ ኩንታል የጤፍ ፣ የስንዴ እና የባቄላ ምርጥ ዘር በተመሠከረለት የጥራት ደረጃ ተመርቶና ተረጋግጦ ለአርሶ አደሩ ለማቅረበ ተዘጋጅቷል ብለዋል።

ዋልታ የገበሬዎች ህብረት ስራ ዩኒየን ምክትል ስራ አስኪያጅ አቶ ያሲን ሀሰን በበኩላቸው ዩኒየኑ ምርጥ ዘር፣ የአፈር ማዳበሪያ፣የከብቶች ማድለብ ፣ የወተት ላም፣ የእንቁላል ጣይ እና ለሌሎችም የሚሆን ምጥን መኖ አዘጋጅቶ እንደሚያቀርብ ተናግረዋል ።

እንደ ምክትል ስራ አስኪያጁ ገለፃ የዋጋ ግሽበት ለማረጋጋት አባል ማህበራት በሰብል ግብይት እንዲሰማሩ እየተደረገ ሲሆን ማህበረቱ የሰብል ውጤቶች ዋጋ በሚንርበት ወቅት ለገበያ በማቅረብ ገበያን የማርጋጋት ስራ እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።

በ2015 በጀት ዓመት ለሸማቹ የህብረተሰብ ክፍሎች 4መቶ ኩንታል ጤፍና ለ110 ኩ/ል በላይ በቆሎ በተመጣጣኝ ዋጋ ማቅረቡን የገለጹት አቶ ያሲን አሁን ገበያ ላይ ከሚሸጥበት በጤፍ 1ሺህ ብር እንዲሁም በበቆሎ 3 መቶ ብር ቅናሽ ማቅረብ ተችሏል ብለዋል።

በዩኒየኖቹ የስራ እድል ተፈጥሮላቸው ሲሰሩ ያገኘናቸው ተጠቃሚዎች እንደገለፁት የገበሬዎች ህብረት ስራ ዩኒየኖች በሰለጠኑበት የትምህርት ዝግጅትና እውቀት እንዲሰሩ እድል በመፍጠራቸው ተጠቃሚ አድርጓቸዋል፡፡

በቀጣይም ያላቸው እውቀትና ልምድ በመጠቀም የተሸለ ስራ በመስራት ለዩኒየኖቹ ውጤታማነት ተግተን እንሰራለን ብለዋል ሲል የዘገበው የጉራጌ ዞን የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ነው።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *