በጉራጌ ዞን የሚንቀሳቀሱ ሲቪክ ድርጅቶችና ማህበራት ከ1 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር በላይ በመመደብ ህብረተሰቡ ተጠቃሚ የሚያደርጉ የተለያዩ የልማት ስራዎችን እየሰሩ መሆናቸውን የዞኑ ፋይናንስ መምሪያ አስታወቀ።

የመንግስት፣ የሲቨክ ድርቶችና ማህበራት ዓመታዊ የምክክር ፎረም በቡታጅራ ከተማ ተካሂዷል።

የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ላጫ ጋሩማ በፎረሙ ተገኝተው እንደገለጹት እያደገ የመጣው የህብረተሰቡ የልማት ፍላጎት በመንገስት በጀት ብቻ የሚሸፈን ባለመሆኑ ይህንን ክፍተት ለመሙላት ሲቪክ ድርጀቶችና ማህበራት እያደረጉት ያለው እገዛ ከፍተኛ ነው።

መንግስት በዚህ ዓመት ለዞኑ ከመደበው አጠቃላይ በጀት 28 ከመቶ የሚሆነውን ያክል ከረጂ ድርጅቶች መገኘቱን የተናገሩት ዋና አስተዳዳረው በዚህም ህብረተሰቡ በልማት ተጠቃሚ ለማድረግ የሚያደርጉት አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው ብለዋል።

በዞኑ ትላልቅ የልማት ስራዎችን በትምህርት፣ በጤናና በንጹህ የመጠጥ ውሃ አቅርቦት ላይ የሚሰሩ እንደ ግሊመር ኦፍ ሆፕ እና ወርልድ ቪዥን ያሉ ግብረ ሰናይ ድርጀቶች የአንድን አካባቢ መሰረታዊ ችግር ለመቅረፍ የሚያደርጉት ጥረት አበረታች ቢሆንም በዛው ልክ ጽህፈት ቤት የሌላቸውና የረባ ስራ የማይሰሩ ስላሉ ተገቢውን ክትትልና ድጋፍ ይደረግላቸዋል ብለዋል።

የጉራጌ ዞን ፋይናንስ መምሪያ ኃላፊ አቶ አብዶ ሀሰን በበኩላቸው የህብረተሰቡ አቅም ከረጂ ድርጀቶችና ማህበራት እንዲሁም ከመንግስት ጋር አቀናጅቶ በመስራት የህዝቡን የልማት ጥያቄ በተወሰነ ደረጃም ቢሆን ምላሽ እንዲያገኝ እየተደረገ ይገኛል ብለዋል።

የዞኑ ፋይናንስ መምሪያ ከተሰጠው ኃላፊነት አንዱ ሲቪክ ድርጅቶችና ማህበራት ለሚሰሩዋቸው ተግባራት ምቹ ሁኔታ በመፍጠር የፕሮጀክት ውል ፈጽመው ወደ ስራ እንዲገቡ ማድረግና በውላቸው መሰረት ወደ ተግባር መግባታቸውን ክትትልና ድጋፍ እንደሚያደርግ ተናግረዋል።

በዚህም በዞኑ የሚንቀሳቀሱ 42 ሲቪክ ድርጅቶችና ማህበራት በ72 ፕሮጀክቶች ላይ ከ1 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር በላይ በመመደብ መንግስት ተደራሽ ባልሆነባቸው በህጻናት እርዳታና እንክብካቤ፣ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ያሉ የህብረተሰብ ክፍሎች ኢኮኖሚያዊ፣ አዕምሮአዊና አካላዊ እንክብካቤ ማድረግ፣ በትምህርት፣ በጤናና በንጹህ የመጠጥ ውሃ አቅርቦት ህብረተሰቡ ተጠቃሚ የሚያደርጉ የተለያዩ የልማት ስራዎችን መሰራታቸውን አብራርተዋል።

አንዳንድ የፎረሙ ተሳታፊ ግብረ ሰናይ ድርጅቶችና ማህበራት በሰጡት አስተያየት ከመንግስት ጋር ተቀራርቦ በትብብር በመስራታቸው በርካታ ህብረተሰቡ ተጠቃሚ የሚያደርጉ የልማት ስራዎችን ማከናወናቸውን ተናግረዋል።

የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማህበራት ወደ ዞኑ በሚመጡበት ጊዜ ሁሉም አካባቢ ያማከለና ህብረተሰቡ በፍትሃዊነት ተጠቃሚ እንዲያደርጉ መደረግ አለበት ብለዋል።

በመጨረሻም በ2015 የበጀት አመት የተሻለ አፈጻጸም ያሳዩ የሲቪክ ድርጀቶችና ማህበራት ዋንጫና ሰርተፊኬት ተበርክቶላቸዋል ሲል የዘገበው የጉራጌ ዞን የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ነው።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *