የጉራጌ ዞን ትራንስፖርት እና መንገድ ልማት መምሪያ 2016 ዓ.ም እቅድ አፈጻጸም እና የ2017 እቅድ የንቅናቄ መድረክ በወልቂጤ ከተማ አካሂዷል።
የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ላጫ ጋሩማ እንዳሉት በአመቱ በባለሀብቱ እና በህብረተሰቡ የተሰሩ የመንገድ ልማት ስራዎች ህዝብና መንግስት የበለጠ ያስተሳሰረ እና ትልቅ ትርጉም ያለው ሲሆን በዞኑ የትራንስፖርት እና የመንገድ ልማት ስራ ይበልጥ በማጠናከር የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ በትኩረት ይሰራል።
መንገድ ለሌሎች መሰረተ ልማት ስራዎች መስፋፋት ሚናው ከፍተኛ ነው ያሉት አቶ ላጫ የባለሀብቱ እና የህብረተሰቡ አቅም በመጠቀም ገንዘብ በደረሰኝ ሰብስቦ ልማትላይ ማዋል እንዲሁም ደረሰኞች ኦዲት ማድረግ እንደሚገባ አሳስበዋል።
በትራንስፖርት ዘርፉ የሚስተዋሉ ብልሹ አሰራሮች እንዲስተካከል በማድረግ ለህብረተሰቡ ፍትሀዊና ቀልጣፋ አገልግሎት እንዲያገኝ በዘርፉ ያሉ ባለሙያዎች ፣ህብረተሰቡ እና አመራሩ ሊቀናጅ ይገባል ነው ያሉት።
አስፋልት ዳር ላይ መኪኖች ለብዙ ጊዜ ማቆም፣ላቢያጆዎች ባልተገባ ቦታ እየሰሩ መሆኑ፣አስፋልት ዳር ላይ መገበያየት ፣አንድ አንድ አመራር እና የዘርፉ ባለሙያው ስራው በአግባቡ አለመስራት ለአብነት ያነሱ ሲሆን ይህንን በአፋጣኝ ማረም እንደሚገባ አቶ ላጫ አስገንዝበዋል።
በቀጣይ የዞኑ ቀበሌዎች እና ወረዳዎች እርስ በርስ ለማስተሳሰር በትኩረት እንደሚሰራ ተናግረዋል።
የጉራጌ ዞን ትራንስፖርት እና መንገድ ልማት መምሪያ ኃላፊ አቶ ሙራድ ከድር እንደገለፁት በ2016 የተሰሩ የትራንስፖርት እና የመንገድ ልማት ስራዎች በ2017 አጠናክሮ በማስቀጠል የህብረተሰቡ ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ እንደሚሰራ አመላክቷል።
ለአብነትም በ2017 ባለሀብቱ ፣ ማህበረሰቡ እና መንግስት በመቀናጀት 2መቶ 80 ሚሊየን ብር በማሰባሰብ 3መቶ ኪሌ ሜትር የመንገድ ልማት ስራ እንደሚሰራ መታቀዱ ተናግሯል።
የትራንስፖርት አገልግሎት አሰጣጥ ችግር ለመቅረፍ አመራሩ ፣የዘርፉ ባለሙያ፣የጸጥታ አካል እና ህብረተሰቡ ለህገ ወጦች ተባባሪ የመሆን ችግር መቅረፍ ይገባል ያሉት አቶ ሙራድ መናኸርያዎችን ውብና ጹዱ በማድረግ ለተሳፊሪዎች ምቹ እንዲደረጉ አጽንኦት ሰጥተዋል።
አቶ ሙራድ አክለውም ትርፍ መጫን፣ትርፍ ማስከፈል፣ተሳፋሪን ማንገላታት፣ህግን መጣስ፣በስነ ምግባር አለማገልገል የሚስተዋሉ ችግሮች በመሆናቸው ትኩረት እንዲደረግባቸው ጠቁመው ስምሪት የሌለባቸው ከተሞች ስምሪት እንዲኖራቸው ለማድረግ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ይሰራበታል ነው ያሉት።
የማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልል መንገዶች ባለስልጣን ኃላፊ ኢንጅነር ምስጋናው ማቲዮስ በመድረኩ ተገኝተው በጉራጌ ዞን በመንገድ ልማት ዘርፍ የሚሰሩ ስራዎች አበረታች ናቸው።
የተሰሩ የመንገድ ልማት ስራዎች ወቅቱን ጠብቆ መጠገን ፣መንከባከብ እና ተደራሽነትን ይበልጥ ማስፋፋት ያስፈልጋል ያሉት ኢንጅነር ምስጋናው ዞኑ የማይችላቸው እና በክልሉ አቅም የሚሰሩ እንዲሁም ቃል የተገቡ የድልድይ ስራዎች በትኩረት እንደሚሰራባቸው ተናግረዋል።
በውይይቱ የተሳተፉ አካላት በበኩላቸው በአመቱ በህብረተሰቡ እና በባለሀብቱ የተሰሩ የመንገድ ልማት ስራዎች በ2017 የበለጠ አቅዶ መስራት የገባል ብለዋል።
ይሁን እንጂ በትራንስፖርት ዘርፍ የሚስተዋሉ የአገልግሎት አሰጣጥ ችግር ለመቅረፍ የሚደረጉ ጥረቶች አበረታች ቢሆኑም ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ግን ገና ብዙ መስራ ይጠይቃል ሲሉ ገልጸዋል።
ከወልቂጤ እስከ ሁሉም ወረዳ ከተሞች የትራንስፖርት ስምሪት እንዲኖር የጠየቁት ሀሳብ ሰጪዎቹ ይህም ህብረተሰቡ ላልተገባ ወጪና እንግልት የሚዳርግ መሆኑን ተናግረዋል።
በመጨረሻም በአመቱም የተሻለ አፈጻጸም ላሳዩ መዋቅሮትና የመምሪያው ባለሙያዎች እውቅና ተሰጥቷል።
ከእነዚህም ከወረዳዎች 1ኛ እኖር ወረዳ ፣2ኛ እዣ ፣3ኛ ቸሀ ወረዳ በከተማ አስተዳደር ደግሞ ወልቂጤ ከተማ 1ኛ ሲወጣ የገደባኖ ጉታዘር ወለኔ ወረዳ ደግሞ ልዩ ተሸላሚ ሆኗል።