በጉራጌ ዞን ወልቂጤ ከተማ የመስቀል በዓል ፌስቲቫል በጉብርየ ክፍለ ከተማ ኤዋንና ጭቋራ ቀበሌ በተለያዩ ዝግጅቶች በድምቀት ተከበረ።️

በጉራጌ ብሔር ዘንድ በድምቀት ከሚከበሩ አበይት በዓላት መካከከል የመስቀል በዓል አንዱ ነው።

በዓሉም በጉራጌ ብሔር ዘንድ ያለው ማህበራዊ ፋይዳ ከፍተኛ ሲሆን በስራ ምክንያት አመቱን ሙሉ ተለያይተው የኖሩ ቤተሠቦችና ዘመድ አዝማዶች የሚገናኙበትና የሚጠያየቁበት፣ ማህበራዊ ችግሮቻቸውን የሚፈቱበት፣ ወጣቶች የሚተጫጩበት፣ ስለ አካባቢ ልማት የሚመከርበት መሆኑን ይታወቃል።

ከዚህም ባለፈ በጋብቻ የተሳሰሩ ቤተሠቦች የሚጠያየቁበት፣ በጥል የተለያዩ ባልና ሚስቶች እንዲሁም የተጣሉ ሰዎች የሚታረቁበት፣ እዳ የሚሠረዝበትና በዳይና ተበዳይ ይቅር የሚባባሉበት ታላቅ በዓል ነው ፡፡

ይህንን አኩሪና ድንቅ እሴት ተጠብቆ ወደ ተተኪው ትውልድ ለማሸጋገር የወልቂጤ ከተማ አስተዳደር የበኩሉን ሚና እየተወጣ ይገኛል።

የከተማው ከንቲባ አቶ እንዳለ ስጦታው እንዳሉት የመስቀል በዓል በጉራጌ ማህበረሰብ ዘንድ ሀይማኖታዊና ቱባ ባህላዊ ይዘቱን ሳይለቅ ከማስቀጠል ባለፈ ማህበራዊ መስተጋብሮቹን የበለጠ እንዲጎለብቱ የከተማው መንግስት እየሰራ ይገኛል።

የመስቀል በዓል ተከትሎ በርካታ እንግዶች ከሀገር ውስጥና ከውጭ ሀገር ወደ ጉራጌ ዞን እንደሚመጡ የገለጹት አቶ እንዳለ በዚህም የማህበረሰቡን እሴት ለሌሎች ከማስተዋወቅ ባለፈ የከተማው በጎ ገጽታ ለመገንባትና የቱሪስት ፍሰቱ እንዲጨምር ሚናው ከፍተኛ ነው ብለዋል።

አቶ እንዳለ አክለውም ከተማ ለኢንቨስትመንት ምቹና ተመራጭ መሆኗን ተከትሎ ኢንቨስት ለማድረግ ለሚሹ ባለሀብቶች የከተማው መንግስት ያለምንም እንግልት ተቀብሎ ለማስተናገድ ዝግጁ መሆኑን ገልጸዋል።

የወልቂጤ ከተማ ባህልና ቱሪዝም ጽህፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሮ ንግስት ገብሬ በበኩላቸው የመስቀል በዓል ለጉራጌ ብሔር ተወላጆች ልዩ ትርጉም ያለው በመሆኑ በየዓመቱ በድምቀት የሚከበር ተናፋቂ በዓል መሆኑን ገልጸዋል።

በዚህም የተጣላ የሚታረቅበት፣ ወጣቶች የሚተጫጩበትና በመተባበርና በአንድነት በፍቅር የሚከበር በዓል ነው ብለዋል።

ወይዘሮ ንግስት አክለውም ጽህፈት ቤቱ የጉራጌ ቱባ ባህሎችን ከማልማትና ከማስተዋወቅ ባሻገር የመስቀል በዓል ሃይማኖታዊና ባህላዊ ይዘቱን ሳይለቅ በማስቀጠል ወደ ጉራጌ ዞን የሚመጡ ቱሪስቶች ቁጥር ለማሳደግ የሚሰራ ሲሆን በከተማዋ ደረጃቸው የጠበቁ የቱሪስት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት (ሆቴሎች)፣ ባንኮች፣ እና ሌሎች ጥንታዊ መስህባት በመኖራቸው ተመራጭ እንዲሆን በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝ አስገንዝበዋል።

የ2017 የመስቀል በዓል በከተማው መከበሩ በዓሉ ቱባ ባህሉን ሳይለቅ ለተተኪው ትውልድ ለማስተላለፍ እና አካባቢው ለማስተዋወቅ ጉልህ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት ወ/ሮ ንግስት ገልጸዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *