በጉራጌ ዞን ወልቂጤ ከተማ አስተዳደር WWW.Wolkitecityadministration.gov.et የተሰኘ ዌብሳይት ተመርቆ አገልግሎት መስጠት ጀምሯል።

የዌብሳቱ መበልጸግ በከተማው ያሉ እምቅ አቅሞችንና የህብረተሰቡን መልካም እሴቶችን ብሎም በከተማው የሚሰሩ የልማትና የመልካም አስተዳደር ስራዎችን ለማስተዋወቅ ሚናው ከፍተኛ መሆኑን ተገለጸ።

የጉራጌ ዞን ሳይንስና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ መምሪያ ኃላፊ አቶ ደምስ ገብሬ በምረቃው ወቅት እንዳሉት በአሁን ወቅት ስራዎችን በዘልማዳዊ አሰራር ከመስራት በመውጣት በቴክኖሎጂና በሲስተም በመታገዝ መስራት ይገባል ያሉት አቶ ደምስ ለዚህም አመራሩና ባለሙያዎች ቴክኖሎጂን በተገቢው በመጠቀም መስራት ይኖርባቸዋል ብለዋል።

በዛሬው እለት የበለጸገው ዌብሳት ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ እንዳለው ያነሱት አቶ ደምስ ማበልጸግ ብቻ ግብ እንደማይሆን አንስተው ይህም ሁሉም ተቋማት በአግባቡ በመጠቀም በከተማዋ የሚሰሩ የልማትና የመልካም አስተዳደር ስራዎችን ብሎም የቱሪስት መስህቦችና ሌሎችም የማህበረሰቡ እሴቶችን ለአለም ህዝብ ማስተዋወቅ ይገባል።

ዌብሳይቱ በደንብ ሲተዋወቅ የገቢ ምንጭ ጭምር መሆኑን አንስተው ይህ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያለው ድረገጹ ሁሉም በአግባቡ መረጃ መመገብና ማስተዳደር ላይ በትኩረት መስራት እንደሚገባም አመላክተዋል።

ዌብሳይቱ ላበለጸገው ለአቶ ኢዘዲንና በማበልጸጉ ሂደት አስተዋጽኦ ላበረከቱ ባለድርሻ አካላት አመስግነው በቀጣይም የዞኑ ማህበረሰብ ተጠቃሚ ለማድረግ በሚደረጉ ጥረቶች እገዛው አጠናክሮ እንዲቀልም ጠይቀዋል።

የወልቂጤ ከተማ አስተዳደር ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ግርማ ንቅበሸዋ እንዳሉት ቴክኖሎጂ ልማትና የመረጃ ቋት እንደሆነ አንስተው ለዚህም በከተማው የሚሰሩ የልማትና የመልካም አስተዳደር ስራዎችንና ያለው እምቅ አቅም ብሎም የህብረተሰቡን እሴቶችን ዌብሳይቱን በመጠቀም ለአለም ህዝብ ለማስተዋወቅ በትኩረት መስራት እንደሚገባ ገልጸዋል።

አሁን ባለንበት ዘመን ቴክኖሎጂ መጠቀም የግድ የሚልበት ዘመን ላይ ደርሰናል ያሉት ኃላፊው ለዚህም አለም የደረሰበት ደረጃ ለመድረስ ቴክኖሎጂን በተገቢው መጠቀም ያስፈልጋል ያሉት ኃላፊው ሁሉም የከተማው ሴክተር መስሪያ ቤቶች መረጃን በአግባቡ በመመገቡ ስራ የበኩላቸውን መወጣት ይኖርባቸዋል ብለዋል።

አቶ ኢዘድን ማህበረሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ ዌብሳይት ያለ ምንም ክፍያ በማበልጸጉ ምስጋና አቅርበው ሌሎችም የፈጠራ ባለቤቶች፣ ባለሀብቶችና አርቲስቶችና ሌሎችም ተሞክሮ በመውሰድ እንዲሰሩም ጠይቀዋል።

የወልቂጤ ከተማ ሳይንስና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ሀምዱ ካሚል በበኩላቸው ዌብሳይቱ በአቶ ኢዘዲን ያለምንም ክፍያ መበልጸጉን ገልጸው ይህም በመጠቀም በከተማው በቱሪዝም፣ በኢንቨስትመንትና በሌሎችም ዘርፎች ያሉ ስራዎች ለአለም ህዝብ ለማስተዋወቅ እየሰራን ነው ብለዋል።

ሴክተር መስሪያ ቤቶች የሚሰሯቸው የልማትና የመልካም አስተዳደር ተግባራቶችን ዌብሳይቱ በመጠቀም በማስተዋዋቅ ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ መስራት ያስፈልጋል ያሉት ኃላፊው ተቋሙ በቴክኖሎጂ ዘርፍ የሚሰራቸው ስራዎችን በቀጣይም አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ተናግረዋል።

የሄክስ ላብስ ምክትል ስራ አስፈጻሚ፣ የአይቤክስ ዋና ስራ አስፈጻሚና የፈጠራ ስራ ባለሙያ አቶ ኢዘዲን ካሚል በበኩላቸው የወጣሁበትን ማህበረሰብ ተጠቃሚ ለማድረግ በማሰብ ከከተማው ሳይንስና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ጽህፈት ቤት ጋር በመሆን www.wolkitecityadministration.gov.et የሚል የወልቂጤ ከተማ ዌብሳይት ማበልጸግ ችያለሁ ብለዋል።

እንደ አቶ ኢዘዲን ካሚል ገለጻ ከ1መቶ በላይ ዌብሳይቶችን በማበልጸግ ያላቸውን እውቀትና ልምድ በመጠቀም የተሻለ ዌብሳይት ማበልጸጋቸውን ጠቁመው ይህ ዌብሳይት በአግባቡ በመጠቀም የአለም ህዝብ ስለ ወልቂጤ ከተማ እንዲያውቁ፣ ለጥናትና ምርምር ትክክለኛና ታአማኒ መረጃዎችና ጫረታ ጨምሮ ሌሎችም በቀላሉ እንዲያገኙ ታስቦ መሰራቱና ደህንነቱ የተጠበቀ መሆኑንም አንስተዋል።

ዌብሳይቱ በከተማው አስተዳደር ውስጥ የሚሰሩ ስራዎችን፣ ያሉ እምቅ አቅሞችንና የህብረተሰቡን እሴቶችን ዌብሳይቱ ላይ በመጫን ለከተማው የገቢ ምንጭ ጭምር እንደሚሆን ጠቅሰው ለዚህም ሁሉም የበኩሉን ድርሻውን ሊወጣ ይገባል ብለዋል።

በዌብሳይቱ ምረቃ ላይ የተገኙት ተሳታፊዎች እንዳሉት የዌብሳይቱ መበልጸግ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ እንዳለው አንስተው የከተማው ሴክተር መስሪያ ቤቶችን በከተማው ያሉ እምቅ አቅሞችንና በከተማው የሚሰሩ ስራዎችን ለህብረተሰቡና ለአለም ህዝብ ለማስተዋወቅ በትኩረት መስራት ይገባል ብለዋል።

ዌብሳይቱ እንዲበለጽግ ላደረጉና አስተዋጽኦ ላበረከቱ አካላት አመስግነዋል ሲል የዘገበው የጉራጌ ዞን የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን መምሪያ ነው።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *