የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ላጫ ጋሩማ በዚህ ወቅት እንዳሉት የጉራጌ ማህበረሰብ ከጥንትም ከአባ ፍራንሷ ማርቆስ ጀምሮ የትምህርት ትርጉም አስቀድሞ የተረዳ ማህበረሰብ ነው።
ለዚህም በ2016 በተደረገው የትምህርት ንቅናቄ ባለሀብቱ ፣የተማሪ ወላጅ ፣በጎ አድራጊ ድርጅቶች እና ሌሎችም በጋራ በተሰሩ ስራዎች ከግማሽ ቢሊየን ብር በላይ ማሰባሰብ መቻሉ እንዲሁም የትምህርት ቁሳቁስ ማሟላት መቻሉ ገልጸዋል።
ለአብነትም የትምህርት ቤት ግንባታ እና ጥገና፣የመጽሀፍት ህትመትና ስርጭት፣የኮምፒውተር፣የወንበር እና ሌሎች ስራዎች መሰራታቸው ጠቅሰዋል።
በዚህም በሀገርና በክልላችን ግምባር ቀደም በመሆን ለሌሎች ሞዴል መሆን ተችሏል ነው ያሉት ዋና አስተዳዳሪው።
የትውልዱ የቀጣይ እጣ ፈንታ ለማረጋገጥ የትምህርት ስራችን ድርድር የለውም ያሉ ሲሆን በመሆኑ የዞናችን ተማሪዎች በወቅቱ ወደ ትምህርት የማይገቡበትና ገብተው ደግሞ የሚያቋርጡበት ምክንያት ምን እንደሆነ ማጥናት እና የሚመለከተው አካል ሁሉ ለዚህ ችግር የመፍትሄ አካል መሆን እንዳለበት አስታውቀዋል።
በዞኑ የትምህርት ተደራሽነትን እንዲኖር የተጀመረው ተግባር ይበልጥ ማጠናከር እና ለትምህርት የደረሰ ማንኛውሞ ተማሪ ትምህርቱን ትኩረት አድርጎ ሊከታተል እንደሚገባ አቶ ላጫ ገልጸዋል።
የወልቂጤ ከተማ ከንቲባ አቶ እንዳለ ስጦታው በበኩላቸው ልዩነቶቻችን በማጥበብ አንድነታችን በማጠናከር ለልማት እና ለሰላም በጋራ ልንቆም ይገባል ብለዋል።
ትምህርት የአንድ ማህበረሰብ እድገትና ብልጽግና የሚረጋገጥበት ትልቅ መሳረያ ነው ያሉት አቶ እንዳለ ይህንን የተረዳ ማህበረሰባችን መንግስት ብቻ ሳይጠብቅ ለትምህርት ልማት ስራ እያደረገ ያለው ንቁ ተሳትፎ የሚበረታታ ነው ብለዋል።
በህዝብ ተሳትፎ ሊገነባ የታሰበው የጉብርየ 1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እና ሌሎች በከተማው እየተሰሩ ያሉ ትምህርት ቤቶች የትምህርት ተደራሽነትና ጥራት እንዲኖር ሚናቸው ከፍተኛ መሆኑን አቶ እንዳለ አብራርተዋል።
በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን የእምድብር ሀገረ ስብከት ገዳም ጳጳስ አቡነ ሉቃስ በዚህ ወቅት እንደገለፁት በስነ ምግባር የታነጸ ትውልድ እንዲኖር ብሎም ሀይማኖታዊ ፣ፖለቲካዊ ፣ማህበራዊ ጉዳዮች በጥራት ለማከናወን ትምህርት ግንባር ቅደም መሆኑን አስረድተዋል።
ቤተ ክርስቲያኗ ከዚህ በፊት ለትምህርት ቤቱ እድሳት በማድረግ ፣ቁሳቁስ በማቅረብና ሌሎች ድጋፎች ያደረገች ሲሆን ይህንን አሻራዋ በቀጣይም አጠናክራ እንደምትቀጥል አቡነ ሉቃስ አስታውቀዋል።
በፕሮግራሙ አግኝተን ያነጋገርናቸው የህብረተሰብ ክፍሎ፦የጉብርየ የአባ ፍራንሷ ሙሉ 1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በአባ ፍራንሷ ማርቆስ ተነሳሽነት በ1934 ዓ.ም ተቋቁሞ ለዚህ የበቃ ሲሆን አሁን ያለው ትውልድ ከአባታችን የወረሰው አሻራ ተቀብሎ ለቀጣይ ትውልድ ማስተላለፍ ይጠበቅበታል።
ትምህርት ቤቱ ለሀገር ባለውለታ የሆኑ በርካታ ምሁራን እንዳፈራ የተናገሩት ሀሳብ ሰጪዎቹ ይህንን ተግባር እንዳይቋረጥ በግንባታውም ሆነ በማንኛውም እንቅስቃሴ የበኩላቸው ድርሻ እንደሚወጡ ተናግረዋል።