በጉራጌ ዞን ከ134 ሺህ 3 መቶ ሄክታር በላይ መሬት በተለያዩ ሰብሎች በመኽር እርሻ ለመሸፈን ግብ ተጥሎ እየተሰራ እንደሆነም የጉራጌ ዞን እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት መምሪያ አስታወቀ

May be an image of 2 people, people sitting and indoor

በጉራጌ ዞን ከ134 ሺህ 3 መቶ ሄክታር በላይ መሬት በተለያዩ ሰብሎች በመኽር እርሻ ለመሸፈን ግብ ተጥሎ እየተሰራ እንደሆነም የጉራጌ ዞን እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት መምሪያ አስታወቀ።አርሶአደሩ የተሻሻሉ የግብርና ቴክኖሎጂዎች በማሳቸዉ ላይ ተግባራዊ በማድረግ ምርትና ምርታማነቱን በማሳደግ በሀገሪቱ የተጀመረዉን የብልጽግና ጉዞ ማረጋገጥ እንዳለበትም ተመልክቷል።የ2013/14 አመተ ምህረት የበልግና ስራዎች አፈጻጸም ግምገማ፣የመኽር እቅድ መግባቢያና የዘመኑ አረንጓዴ ልማት ስራ ማጠናከሪያ የንቅናቄ መድረክ በሙህርና አክሊል ወረዳ ሀዋሪያት ከተማ ላይ ተካሄደዋል።የጉራጌ ዞን ብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ሀላፊ አቶ ክፍሌ ለማ እንዳሉት አመራሩ በከተማና በገጠር ስራዎች ላይ በተለይ በገጠሩ የመኽር እርሻ ስኬታማ ለማድረግ ከመቼዉም ጊዜ በላይ ትኩረት ሰጥተዉ ርብርብ ማድረግ አለባቸዉ ብለዋል።በመኽር የግብርና ስራ የታያዘዉን ግብ ለማሳካት አርሶአደሩ እንዲሁም በየደረጃዉ ያለዉን ባለድርሻ አካልና ወጣቱን ማሳተፍ እንደሚገባም አስታዉቀዋል።በበልግ እርሻ ከምርጫው ስራ ጎን ለጎን የተደረገዉ ርብርብ አበረታች የነበረ መሆኑም ያነሱት አቶ ክፍሌ በበልግ እርሻ የታቀደው 93 በመቶ ማሳካት እንደተቻለም አስረድተዋል።የጉራጌ ዞን እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት መምሪያ ሀላፊ አቶ ሸምሱ አማን እንዳሉት የግብርናዉ ሴክተር የዞኑ ብሎም የሀገራችን ኢኮኖሚ በዋናነት የሚያንቀሳቅስ ነዉ።እንደ ዞናችን በበልግ እርሻ ከእቅዱ 93 በመቶ መሳካቱ አስታውሰው የመኽር ተግባራት ላይ የበልጉን ውስንነት ሊሞላ በሚችል ሁኔታ የበለጠ ዉጤታማ ስራ መስራት እንደሚገባም ተናግረዋል።የሙህርና አክሊል ወረዳ በካልም ፕሮግራም በክልሉ አንደኛ በመዉጣቱም ሞዴል እንደሆነም አስረድተዋው እንደዚህ አይነት ስኬት በሌሎች የፕሮግራሙ ተጠቃሚ መዋቅሮቻችንና ብሎም በበልግና መኸሩ በሁሉም መዋቅር ሊደገም ይገባል ብለዋል።በዘንድሮ የበልግ ወቅት የዝናብ እጥረት እንደገጠመም ተናግረዉ በበልጉ ያጣናቸዉ እድሎች በመኽር ማካካሻ እቅድ በማቀድ አርሶአደሩ ተጠቃሚ የሚሆኑበትና ቀጣይ 2014 አመተ ምህረት ህዝባችንን ከኑሮ ውድነቱ የምንታደግበት ማካካሻ ስራ መስራት ይገባል ብለዋል።በዝናብ እጥረት ምክንያት በአንዳንድ አካባቢዎች ላይ ድርቅ ተከስቶ እንደነበረ ተናግረዉ በሙህና አክሊል ወረዳ በአንዳንድ ቀበሌዎች ላይ ከ3 መቶ በላይ ከብቶች መሞታቸዉም አስታዉሰዋል።የጉራጌ ዞን እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት መምሪያ ምክትል ኃላፊ አቶ ክፍለማሪያም መኩሪያ እንዳሉት የግብርናዉ ዘርፍ በሀገሪቱ ኢኮኖሚ እድገት ለማምጣትና ድህነትን በመቀነስ ረገድ ፋይዳዉ የጎላ እንደሆነም ተናግረዋል ።ባለፉት አመታት አጠቃላይ በግብርና ልማት ስራዎች ላይ አበረታች ለውጦች ማስመዝገብ መቻሉም ተናግረዉ ይህንንም ዉጤት የበለጠ አጠናክሮ ለማስቀጠል በሁሉም ሰብሎች ምርትና ምርታማነት ማሳደግ እንደሚገባም አስረድተዋል፡፡ በአየር ንብረት መዛባት ምክንያት ሊመጣ የሚችለውን የምርታማነትና የምርት መቀነስ ችግር ለመቅረፍ እንዲያስችል የበልግ ዕቅድ ተከልሶ ወደ ተግባር የተገባ ቢሆንም የዝናቡ ስርጭትና መጠን በተገቢው መስተካከል ስላልቻለ የቀጣይ 2013/14 ምርት ዘመን የመኽር ዕቅድ በልጉን ሊያካክስ በሚያስችል መልኩ አቅዶ መተግበር አስፈላጊ ነው ብለዋል። በዚህም በዞኑ 1 መቶ 34 ሺህ 3 መቶ 14 ሄክታር በላይ መሬት በተለያዩ ሰብሎች በመኽር እርሻ ለመሸፈን ግብ ተጥሎ እየተሰራ እንደሆነም ተናግረዋል።በመኸር ከሚታረሰው መሬት ውስጥም በተመረጡ ወረዳዎች በገብስ ፣ በስንዴና በጤፍ ሰብሎች 58 ሺህ 5 መቶ 28 ሄክታሩ መሬት በኩታገጠም አስተራረስ ዘዴ የሚሸፈን ይሆናል ብለዋል።ከመኸር ስራችን ጎን ለጎን በዞኑ እየተከናወነ ያለዉን አረንጓዴ ኢኮኖሚ ልማት ስራ ለማሳካት 105 ነጥብ 3 ሚሊየን የደን ችግኝ በሁሉም ወረዳዎች ለመትከል መታቀዱም አቶ ክፍሌ ተናግረዋል።በበልግ ወቅት ልናጣ የምንችለውን የምርት መጠን ማካካስ በሚያስችል መልኩ የመኸር ልዩ የማስፈፀሚያ ዕቅድ ተነድፎ በትኩረት እየተሰራ እንደሆነም አስረድተዋል።በአጠቃላይ በ 2013/14 ምርት ዘመን በልግ 69ሺህ 8 መቶ 33 ሄክታር መሬት በተለያዩ ሰብሎች በመሸፈን 10 ሚሊየን 399 ሺህ 113 ኩ/ል ምርት ለማምረት እየተሰራ እንደሆነም አስታዉቀዋል።የጉራጌ ዞን እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት መምሪያ የተፈጥሮ ሀብት ባለሙያና የካልም ፎካል ፐርሰን አቶ ሀይለየሱስ ይብጌታ በበኩላቸዉ ካልም በአለም ባንክ የመሬት አቀማመጥን መሰረት ያደረገ የአየር ንብረት ለውጥ ትግበራ ፕሮግራም በአለም ባንክ የገንዘብ ድጋፍ በኢትዮጵያ ውስጥ በመተግበር ላይ ይገኛል።የመኖ ልማትን በማስፋፋትና አቅርቦት በማሻሻል ፣ የእንስሳት ሀብት ልማት ውጤታማነትን በማሳደግ፣ የአየር ንብረት ለውጥ የሚቋቋም ኢኮኖሚ መገንባት፣ተጠቃሚዎች የራሳቸዉንና የቤተሰባቸዉን ጉልበትን በተፋሰስ ልማትና በግብርና ምርት ተግባር ላይ በማዋል ገቢውና ኑሮው በቀጣይነት እያደገ እንዲሄድ ማድረግ ይገባል ብለዋል፡፡በመድረኩ የተገኙ አንዳንድ አስተያየት ሰጪዎች እንዳሉት የግብአት አቅርቦት ላይ ያሉትን ማነቆዎችን በመፍታት በመኽር እርሻ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ከመቼዉም ጊዜ በላይ መሰራት እንዳለበትም ተናግረዋል።አርሶአደሩ ከባህላዊ አስተራረስ ዘዴዎችን በማላቀቅ በዘመናዊ መንገድ ለማረስ የትራክተርና ሌሎችም ግብአቶች ላይ ያሉትን ዉስንነቶች በተገቢዉ በመቅረፍ ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ እንደሚገባም አብራርተዋል።በመድረኩ የዞንና የወረዳ ከፍተኛ አመራሮች፣የጉራጌ ዞን እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት መምሪያ ማነጅመንት አካላትና ሌሎችም ባለድርሻ አካላት የተሳተፉ ሲሆን በመጨረሻም የጉራጌ ዞን ብልፅግና ፓርቲ ፅ/ቤት ሀላፊ አቶ ክፍሌ ለማና የመድረኩ ተሳታፊዎች በሙህርና አክሊል ወረዳ ዋና ከተማ ሀዋሪያት ችግኝ በመትከል የአረንጓዴ ልማት አሻራቸው አኑረዋል ሲል የዘገበው የጉራጌ ዞን መንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ነው።

Comments are closed.