በጉራጌ ዞን ከትምህርት ገበታቸዉ የራቁ 38 ሺህ 960 ተማሪዎች ወደ ትምህርታቸዉ እንዲመለሱ በማድረግ ረገድ አመራሩ ፣ የትምህርት ባለድርሻ አካላቶችና ማህበረሰቡ በቅንጅት መስራት እንዳለባቸዉ የዞኑ ትምህርት መምሪያ አስታወቀ።

የተማሪ ቅበላ አፈጻጸም ግምገማና የንቅናቄ መድረክ እንዲሁም የ12ኛ ክፍል ፈተና አሰጣጥ ኦረንቴሽን የዞን ፣የወረዳና ከተማ አስተዳደር አመራሮች፣ የፀጥታና በዘርፉ ባለሙያዎችና የሚመለከታቸዉ ባለድርሻ አካላቶች በተገኙበት በወልቂጤ ከተማ ተካሄዷል።

የሀገራችን የትምህርትና ስልጠና ፖሊሲ ትኩረት ከሰጣቸው ዋና ዋና ሥልቶች መካከል “የትምህርት ምዘናና ፈተና” አንዱ ነው።

በየደረጃው የሚገኙ አካላቶች ከጥቅምት 29 እስከ ህዳር 2 ቀን 2014 ዓ.ም የ2013 ዓ/ም የሀገር አቀፍ ፈተና ደህንነት ተጠብቆ በስርዓቱ እንዲመራ የተቀናጀ አሰራርን ከመፍጠር አንጻር የባለድርሻ አካላት የነቃ ተሳትፎ ወሳኝ ነዉ።

በመድረኩ የተገኙት የጉራጌ ዞን የመንግስት ዋና ተጠሪ አቶ ክፍሌ ለማ እንዳሉት የጉራጌ ዞን ማህበረሰብ ለትምህርት ልዩ ትኩረት የሚሰጥ እንደሆነም ተናግረዉ የ2014 ዓመተ ምህረት የተማሪዎች ቅበላ አቅም ማሳካት ላይ ዉስንነት የሚስተዋልባቸዉ አካባቢዎች ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ተቀናጅተው በመስራት ከትምህርት ገበታቸዉ የራቁ ተማሪዎችን እንዲመለሱ ርብርብ ማደረግ እንዳለባቸው አሳስበዋል።

ከትምህርት ገበታቸዉ የራቁ ከ38 ሺህ በላይ ህጻናት ተማሪዎች ወደ ትምህርታቸዉ እንዲመለሱ በማድረግ ረገድ የትምህርት ዘርፉ ባለድርሻ አካላቶች ከሌሎች የሚመለከታቸዉ ባለድርሻ አካላት ጋር ቅንጅታዊ አሰራርን በመፍጠር ዉጤታ ስራ ሊሰሩ እንደሚገባም ተናግረዋል።

ወደ ትምህርት ቤት ገብቶ የሚማረዉ የደሃ ልጅ ነገ ሀገር የሚረከብና እናትና አባቱን የሚጦር ተማሪ ሰፈር ላይ ማስቀረት የለብን ያሉት አቶ ክፍሌ ይህም ከሀላፊነት አንጻርና ከህሊናም አንጻር የሚያስጠይቅ እንደሆነም አስታዉቀዉ እነዚህ ተማሪዎች በየአካባቢዉ ወደ ሚገኙ ትምህርት ቤቶች ተቀላቅለው እንዲማሩ ማድረግ እንደሚገባም አሳስበዋል።

ከስርአተ ትምህርት አንጻር እንደ ሀገር የትምህርት ተደራሽነት ላይ በተሰራዉ ልክ የትምህርት ጥራት ላይ እንዳልተሰራም አስረድተዉ የትምህርት ፖሊሲና ስርዓተ ትምህርት ላይ ማሻሻያ የተደረገ መሆኑም ገልፀዋል።

አክለውም አቶ ክፍሌ በክልሉ በርካታ ዞኖች መፅሃፍቶቻቸዉ አዘጋጅተዉ ማሳተማቸዉም አመላክተዉ በዞኑ የቀቤናና የማረቆ ቋንቋዎች ላይ የሚሰራዉ የትምህርት ስራ በመደገፍ ከቤተ ጉራጌ አንጻር የተጀመሩ ስራዎች ላይ መምሪያዉ ከሌሎች አካላቶች ጋር በመሆን በተመረጡ ትምህርት ቤቶች ላይ የሙከራ ትግበራ ሊጀምር እንደሚገባም አሳስበዋል።

የጉራጌ ዞን ትምህርት መምሪያ ሀላፊ አቶ አስከብር ወልዴ እንዳስታወቁት በአዲሱ ምዕራፍ ስለ ሀገራችንና ህዝቦቿ አዲስ ተስፍና ብልጽግና ለማረጋገጥ የትምህርቱ ሴክተር ትልቁን ድርሻ አለዉ።

የዞኑ ህዝብ በዚያ በጨለማዉ ዘመን ልክ እነደ አሁኑ ዘመናዊ ትምህርት ሳይስፋፋ ትምህርት የሁሉም ነገሮች መሰረት እንደሆነ በመረዳት እንደ አባ ፍራንሷ ባሉ ታላላቅ አባቶቻችንና ህዝቡ እምድብር አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃና አበሩስና እና ሌሎች መሰል ትቤቶች በማስገንባትና ትውልድ በማፍራት ታሪክ የማይረሳው አሻራ ጥለው አልፈዋል ብለዋል።

በዞናችን በሁሉም የክፍል ደረጃዎች ከ113,356 በላይ ህጻናትና ተማሪዎች በ2013 አመተ ምህረት ትምህርታቸዉን ሲከታተሉ ከነበሩት ዉስጥ ከ 38 ሺህ 960 በላይ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ዉጪ ሆነዉ በየመንደሩ እንደሚገኙም አስታዉቀዋል።

እነዚህ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ገበታቸዉ እንዲመለሱ የዘርፉ አካላቶች ከሚመለከታቸዉ ባለድርሻ ጋር በመሆንና በየቀበሌዉ ህዝቡን በማወያየት እንደሚለሱ ማድረግ እንደሚገባም አስረድተዋል።

ከ10 ሺህ በላይ ልዩ ፍላጎት ያላቸዉ እንዲሁም በርካታ ቅድመ አንደኛ መግባት የነበረባቸዉ ተማሪዎች በየመንደሩ እርዳታችን በመጠባበቅ ላይ መሆናቸዉም አመላክተዋል።

ከጥቅምት 29 እስከ ህዳር 2 የሚሰጡዉ የ2013 ዓመተ ምህረት ሀገር አቀፍ የ12ኛ ክፍል ፈተና ተገቢዉን ድጋፍና ክትትል በማድረግ የተሳካ እንዲሆን ሁሉም የድርሻዉን እንዲወጣ አቶ አስከብር አሳስበዋል።

በመድረኩ የተገኙ አንዳንድ ባለ ድርሻ አካላት በሰጡት አስተያየት ወደ ትምህርት ቤት ያልገቡ ተማሪዎች ወደ ትምህርት እንዲመለሱ ለማድረግ በቀበሌ ደረጃ ከህዝብ ጋር ዉይይት በማድረግ እንደ ክልል በተቀመጠው ጊዜ ገደብ ወደ ትምህርትቤት እንዲገቡ መደረግ አለበት ብለዋል።

ፈተና በሚሰጥባቸዉ አካባቢዎች ከጸጥታ ችግር ነጻ መሆን እንዳለባቸዉና የፈተና አሰጣጥና ስርጭት በሚደረግበት ጊዜ በተገቢዉ በመምራትና በሰላም እንዲጠናቀቅ የሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ከጸጥታዉ መዋቅር ጋር ቅንጅታዊ አሰራር ማጠናከር እንደሚገባም አመላክተዋል።

የትምህርት ልማቱ ስራ ስኬታማ ለማድረግ የቅበላ አቅም በማሳደግና በተለያዩ ምክንያቶች ያቋረጡ ተማሪዎችን ወደ ትምህርት እንዲመለሱ በማድረግና በዞኑ ከሁሉም አካባቢዎች ትምህርት ቤት ያልገቡ ተማሪዎች በአጭር ጊዜ ዉስጥ ወደ ትምህርት ገበታቸዉ እንዲመለሱ ቅንጅታዊ አሰራርን ማጠናከር ይገባል ብለዋል።

በመድረኩ የጉራጌ ዞን ምክር ቤት ዋና አፈጉባኤ ክብርት ወ/ሮ አርሽያ አህመድ፣የዞኑ የመንግስት ዋና ተጠሪ አቶ ክፍሌ ለማ ጨምሮ የዞንና የወረዳ ከፍተኛ አመራሮች፣የፀጥታ አካላት፣ የዘርፉ ባለሙያዎችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል ሲል የዘገበዉ የጉራጌ ዞን የመንግስት ኮሚኒኬሽን መምሪያ ነዉ።

በተጨማሪም እነዚህ ሊንኮችን በመጫን ወቅታዊና ትኩስ መረጃዎቻችንን እንድትከታተሉ እንጋብዛለን፡፡
Facebook:- https://www.facebook.com/gurage1Zone
Website:- https://gurage.gov.et
Telegram:- https://t.me/comminuca
Youtub: -https://www.youtube.com/channel/UCzrcazGvvIO2tG7bQN36Cx

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *