በጉራጌ ዞን እዣ ወረዳ ከ35 ሚሊየን ብር በላይ በሆነ ወጪ የተገነባው የአገና የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ተመርቆ ለአገልግሎት ክፍት ሆነ።

ሆስፒታሉም 1መቶ 20 ሺ የህብረተሰብ ክፍሎች ተጠቃሚ እንደሚያደርግም ተገልፃል።

ሆስፒታሉ በአቅራቢያቸው ተገንብቶ አገልግሎት መስጠት በመጀመሩ ህክምና ለማግኘት ከሚያባክኑት ጊዜ፣ ጉልበትና ወጪ እንደሚያድናቸውና ጤናማና አምራች ትውልድ በመገንባቱ ረገድ ሚናው የላቀ መሆኑን የአከባቢው ነዋሪዎች ተናግረዋል።

የደቡብ ክልል ጤና ቢሮ ኃላፊ አቶ እንዳሻው ሽብሩ እንደገለፁት በክልሉ በባለፉት አስርት አመታት የአገና ሆስፒታልን ጨምሮ 45 የመጀመሪያ ሆስፒታሎችን በመገንባት አገልግሎት እየሰጡ ይገኛሉ።

የክልሉ መንግስት ለአገና ሆስፒታል 29 ሚሊየን ብር ወጪ ማድረጉን ገልፀው በቀጣይ 4መቶ ሺህ ብርና የተለያዩ ድጋፎችን እንደሚያደርግም ተናግረዋል።

የእስካሁኑ ድጋፍ በቂ አለመሆኑ የገለፁት አቶ እንዳሻው በቀጣይም ከክልል መንግስት ጋር በጋራ በመሆን ሆስፒታሉ ያለበትን የግብአት እጥረት ለመቅረፍ እንደሚሰሩም አመላክተዋል።

የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ መሀመድ ጀማል የተመረቀው ሆስፒታል በዞኑ የሚገኙ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታሎች ቁጥር ወደ 9 ከፍ እንደሚያደርገውና በህብረተሰቡ በተደጋጋሚ ሲነሳ የነበረው የጤና አገልግሎት ሽፋንና ተደራሽነት ጥያቄ በተወሰነ መልኩ ከመመለሱም በላይ የአገልግሎት ጥራቱን በማሳደግ ረገድ የራሱ ሚና ይጫወታል።

በዞኑ የሚገኙ ሆስፒታሎች የማቴሪያል ድጋፍ ይደረጋል ያሉት አቶ መሀመድ በባለፉት አመታት አሜሪካ የሚገኙ የአከባቢ ተወላጆችን በማስተባበር በ40 ሚሊየን ብር ወጪ 2መቶ አልጋዎች ድጋፍ መደረጉን አስታውሰው ለአገና ሆስፒታልም 15 አልጋዎች ድጋፍ መደረጉንም ገልፀዋል።

ሆስፒታል መገንባት ብቻ ግብ አይደለም ያሉት አቶ መሀመድ ሆስፒታሉ በሰው ሀይልና ቁሳቁስ ማደራጀትና ተገቢውን አገልግሎት በጥራትና በፍትሃዊነት ለህብረተሰቡ ተደራሽ ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል።

እንደ አቶ መሀመድ ገለፃ በቀጣይ በዞኑ የሚገኙ ሆስፒታሎች ያሉባቸውን ችግር ለመቅረፍ ከክልልና ከፌደራል ጤና ቢሮ ጋር በመቀራረብ እንደሚሰራም አመላክተዋል።

የእዣ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ክብሩ ፈቀደ በጤናው ዘርፍ የህብረተሰቡን ተሳታፊነትና ተጠቃሚነትን ይበልጥ ለማጠናከርና የአገልግሎት አሰጣጡ ከማዘመንና ከማቀላጠፍ ባለፈ የጤና ተቋማት ተደራሽነት ላይ እየተሰራ ነው ብለዋል።

ሆስፒታሉ በአቅራቢያ መገንባቱ ከዚህ በፊት ህብረተሰቡ በሆስፒታል ርቀት ምክንያት ይስተዋል የነበረውን እንግልትና አላስፈላጊ ወጪ ከማዳን ባለፈ ጤንነቱን የተረጋገጠ አምራች ዜጋ ለማፍራት ድርሻው የላቀ ነው ብለዋል።

የወረዳው መንግስት 7ሚሊየን ብር ወጪ በማድረግ የውስጥ ቁሳቁስ ለማሟላት ጥረት መደረጉን ገልፀው አሁንም የቀዶ ጥገና፣ የጨቅላ ህፃናት ፅኑ ህሙማን፣ የራጅ ክፍልና ሌሎችም ችግሮች መኖራቸው ጠቁመዋል።

በመሆኑም ህብረተሰቡ በሆስፒታሉ ይበልጥ ተጠቃሚና ተገቢውን አገልግሎት እንዲያገኝ ሆስፒታሉ ያለበትን የህክምና ግብአት እጥረት ለማሟላት በሚደረገው ጥረት ሁሉም ከመንግስት ጎን በመቆም የበኩሉን አስተዋጽኦ እንዲያደርግም ጠይቀዋል።

አቶ ግዛቸው ብዛኒ፣ ወይዘሮ ዙፋን ሽኩርና ትዕግስት መንግስቱ የአከባቢው ነዋሪዎች ናቸው። በጋራ በሰጡት አስተያየት ሆስፒታሉ በአቅራቢያቸው መገንባቱ ለማህበረሰቡ የተሻለ አገልግሎት ከመስጠቱም ባለፈ ጤናማ፣ አምራች ትውልድ በመገንባቱ ረገድ ሚናው ከፍተኛ ነው ብለዋል።

ከዚህ በፊት ሆስፒታል በአቅራቢያቸው ባለመኖሩ ምክንያት ከፍተኛ እንግልትና ላላስፈላጊ ወጪ ይዳረጉ እንደነበር አስታውሰው የሆስፒታሉ መገንባት ከእነዚህና መሰል ችግሮች እንደሚታደጋቸው ተናግረዋል።

በተለይም በእናቶችና በህፃናት ላይ ይደርስ የነበረውን ሞትና እንግልት ከመቀነሱም ባለፈ ጤናን በማጎልበቱ ረገድ ሆስፒታሉ ትልቅ ሚና ይኖረዋል ብለዋል ሲል የዘገበው የጉራጌ ዞን የመንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ነው።

በመረጃ ምንጭነት ገፃችን ምርጫዎ ስላደረጉ እናመሰግናለን!
= ኢትዮጵያን እናልማ!
= የፈረሰውን እንገንባ!
= ለፈተና እንዘጋጅ!
በተጨማሪም እነዚህ ሊንኮችን በመጫን ወቅታዊና ትኩስ መረጃዎቻችንን እንድትከታተሉ እንጋብዛለን፡፡
Facebook:- https://www.facebook.com/gurage1Zone
Website:- https://gurage.gov.et
Telegram:- https://t.me/comminuca
Youtub:- https://youtube.com/channel/UCzrcazGvvIO2tG7bQN36CxQ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *