በጉራጌ ዞን እዣ ወረዳ ከ15 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ በአካባቢው ህብረተሰብ እና ባለሀብቶች የተገነቡ የመንገድ ፕሮጀክቶች አገልግሎት መስጠት ጀመሩ።

የአካባቢው ማህበረሰብ የልማት ተጠቃሚነቱን ለማሳደግ ተቀናጅተው እንደሚሰሩ የወረዳው ባለሀብቶች ተናግረዋል።

የእዣ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዘውዱ ዱላ በመንገዶቹ ምረቃት ስነስርዓት ላይ ተገኝተው ባደረጉት ንግግር የጉራጌ ማህበረሰብ የራሱን አቅም፣ እውቀትና ገንዘብ በመጠቀም መንገድ የመገንባት የካበተ ልምድ ባለቤት ሲሆን በትውልድ ቅብብሎሽ በተለያዩ አካባቢዎች እየተተገበረ ይገኛል ብለዋል።

በእዣ ወረዳ በተለያዩ ቀበሌዎች በህብረተሰብና በአካባቢው ባለሀብቶች ተሳትፎ የመንገድ መሰረተ ልማት በማስፋፋት ህብረተሰቡ ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።

ለምርቃት የበቃው የቦነጋራ-አዘር የቅርበራ የጠጠር መንገድ ፕሮጀክት፣ ድልድዮችና ስትራክቸሮች ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ እንዳላቸው የገለጹት አቶ ዘውዱ ፕሮጀክቶቹ ዘላቂ አገልግሎት መስጠት እንዲችሉ ማህበረሰቡ አስፈላጊውን ክብካቤ ሊያደርግላቸው እንደሚገባ አስረድተዋል።

በ2015 ዓ ም በመንግስትና በማህበረሰብ ተሳትፎ 19 ነጥብ 4 ኪሎሜትር አዳዲስ መንገዶች የተገነቡ ሲሆን 39 ነጥብ 3 ኪሎሜትር የመንገድ ጥገና እና ከ10 በላይ ስትራክቸሮች መስራት መቻሉን አቶ ዘውዱ ገልጸዋል።

በመንገድ ፕሮጀክቶቹ አስተዋጽኦ ካበረከቱ የአካባቢው ባለሀብቶች መካከል አቶ ተስፋዬ ገብረህይወት ተጠቃሽ ሲሆኑ የቀደሙ አባቶች አካባቢን የማልማት እና መሰረተ ልማትን የማስፋፋት ልምድ ለተተኪው ትውልድ ማስተላለፋቸው በአካባቢ ልማት ላይ በንቃት እንዲሳተፉ አስችሏቸዋል።

እንደ አቶ ተስፋዬ ገለጻ በአዘርና ቅርበራ ተወላጆች ተገንብተው ለምረቃ የበቁ የ2 ነጥብ 5 ኪሎሜትር የጠጠር መንገድ፣ የ2 ድልድዮች እና ስትራክቸር ስራዎች ከ15 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ተደርጎላቸዋል።

በቀጣይ በአካባቢው የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት፣ የመብራትና ሌሎች የመሰረተ ልማት ስራዎች በማስፋፋት ህብረተሰቡ ተጠቃሚ ለማድረግ ከሌሎች ባለሀብቶችና ተወላጆች ጋር ተቀናጅተው እንደሚሰሩ አቶ ተስፋዬ ገልጸዋል።

አቶ አበራ ሀሰን እና ሃጅ አብዶ ሁሴን ከዚህ ቀደም በአካባቢው የነበረው ከፍተኛ የመንገድ ችግር ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጫና እንዳሳደረባቸው ገልጸዋል።

ይህን የመንገድ ችግር ለመቅረፍ የአካባቢው ማህበረሰብና ባለሀብቶች ደረጃውን የጠበቀ የጠጠር መንገድ መገንባት በመቻላቸው ኑሯቸው እንደሚያቀልላቸው ነዋሪዎቹ ገልጸዋል።

ወይዘሮ ወርቅነሽ መንጂየ በበኩላቸው በአካባቢው የተስተካከለ መንገድ ባለመኖሩ ለከፋ የጤና ችግር ይዳረጉ እንደነበር ተናግረዋል።

እንደ ወይዘሮዋ ገለጻ ህሙማንና ነፍሰጡር እናቶች በወቅቱ ወደ ጤና ተቋም በመሄድ የህክምና አገልሎት ለማግኘት ይቸገሩ ነበር። ይህ መንገድ የዘመናት ችግር የሚቀርፍና የእለተ ተዕለት እንቅስቃሴያቸው ለማቀላጠፍ የሚያግዛቸው በመሆኑ መንገዱ በጎርፍ እንዳይጎዳ አስፈላጊውን ክብካቤ እንደሚያደርጉ ገልጸዋል።

አክለውም ነዋሪዎቹ ባለሀብቶች እና የአካባቢው ነዋሪዎች የሚያከናውኗቸው ተግባራት ለማጠናከር መንግስት አስፈላጊውን ድጋፍ ማድረግ እንደሚጠበቅ ተናግረዋል ሲል የጉራጌ ዞን የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ዘግቧል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *