በጉራጌ ዞን እዣ ወረዳ በባለሀብት፣ በህብረተሰብና በመንግስት ተሳትፎ ከ16 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የተገነቡ 25 ኪሎሜትር መንገዶች ተመርቀው ለትራፊክ ክፍት ሆኑ።


የዞኑ ማህበረሰብ የቆየ የአባቶች ልምድ በመጠቀም ከመንግስት ጋር በመቀናጀት በመንገድ ልማት እየሰራቸው ያሉ ስራዎችን ለማጠናከር የክልሉ መንግስት አስፈላጊውን እገዛ እንደሚያደርግ በርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የመሰረተ ልማት ክላስተር አስተባባሪና የክልሉ ትራንስፖርትና መንገድ ልማት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር መሀመድ ኑሪዬ ገለጹ።

በርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የመሰረተ ልማት ክላስተር አስተባባሪና የክልሉ ትራንስፖርትና መንገድ ልማት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር መሀመድ ኑሪዬ እንዳሉት የጉራጌ ማህበረሰብ ከጥንት ጀምሮ የመንገድ ጥቅም በመገንዘብ በዘርፉ በርካታ ስራዎችን እየሰራ ይገኛል።

በዞኑ ያሉ እምቅ አቅሞችን በተገቢው ለመጠቀም መንገድ ወሳኝ ነው ያሉት ዶክተር መሀመድ ኑሪዬ የክልሉ መንግስትም በዘርፉ ማህበረሰብ በማሳተፍ በርካታ ስራዎችን እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

ህብረተሰቡ በመንገድና በሌሎች መሰረተ ልማቶች የተጠየቀውን ጥያቄዎች በቀጣይ ደረጃ በደረጃ ለመፍታት እንደሚሰራ ተናግረዋል።

የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ላጫ ጋሩማ በመክፈቻ ንግግራቸው የዞኑ ማህበረሰቡ መንገድ የሁሉም ነገር መሰረት መሆኑን በመረዳት የቀድሞ አባቶች ስራ ትውልዱም በማስቀጠል በዘርፉ በትኩረት እየተሰራ ይገኛል።

በዞኑ በመንገድ መሰረተ ልማት ባለሀብትና ህብረተሰብ በማስተባበር በተያዘው በጀት አመት ማሽነሪ፣ የሰው ጉልበትና ሌሎችም ጨምሮ ከግማሽ ቢሊየን ብር በላይ መንገድ መገንባቱንም አንስተዋል።

ባለሀብቶች በትምህርት፣ በንጹህ መጠጥ ውሃና በሌሎችም እየሰሩት ያለው አበረታች ስራ አመስግነው የዞኑ መንግስትም በቀጣይ ሁለት አመታት በዞኑ ያሉ የገጠር ቀበሌዎች ከዋና መንገድ ለማገናኘት ይሰራል ነው ያሉት።

ህብረተሰቡ ከመንግስት ጋር ተቀራርቦ በተሰራው ስራ በሁሉም ዘርፍ አበረታች ውጤቶች እየተመዘገበ መሆኑን ያነሱት አቶ ላጫ በቀጣይም የተጀማሩ የልማት ስራዎችን ለማጠናከር ህብረተሰቡ የጀመረውን ሁለንተናዊ ተሳትፎ እንዲያጎለብትም አስገንዝበዋል።

የጉራጌ ዞን ትራንስፖርትና መንገድ ልማት መምሪያ ኃላፊ አቶ አቶ ሙራድ ከድር መንገድ የመሰረተ ልማቶች ሁሉ አውታር በመሆኑ ህብረተሰቡ በሁሉም ዘርፍ ተሳታፊና ተጠቃሚ ለማድረግ ሚናው የላቀ ነው።

በዚህም በዞኑ በተያዘው በጀት አመት ባለሀብቶችና ማህበረሰቡን በማስተባበር ከ2መቶ 77 ሚሊዮን ብር በላይ በማሰባሰብ ከ2መቶ 43 ኪሎሜትር በላይ መንገድ በማጠናቀቅ ለትራፊክ ክፍት ማድረግ ተችላል ብለዋል።

መንገዶች ለረጅም አመታት አገልግሎት መስጠት እንዲችሉ በተገቢው መጠበቅና መንከባከብ እንደሚገባም ተጠቁመዋል።

የእዣ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዘውዱ ዱላ በወረዳው መንግስት፣ ባለሀብትና ህብረተሰብ በመቀናጀት ከ48 ነጥብ 5 ብር በላይ ወጪ በማድረግ 42 ኪሎሜት አዲስ የጠጠር መንገድ፣ ከ49 ኪሎሜትር በላይ የነባር መንገድ ጥገና እንዲሁም 3 ድልድዮችና 6 እስትራክቸሮች ብሎም ከ18 ነጥብ 7 በላይ የአፈር ስራዎች መከናወኑን ገልጸዋል።

አክለውም መንግስትና ማህብረሰብ በመቀናጀት 16 ሚሊዮን ብር ወጪ በማድረግ ጉ/የስዋ፣ አምባገነትና ያስሁራ 8 ኪሎሜትር አዲስ የጠጠር መንገድ ግንባታ፣ 17 ኪሎሜትር የነባር መንገድ ጥገናና 3 የተለያዩ እስትራክቸሮች በመስራት በዛሬው እለት ማስመረቅ ተችላል ብለዋል።

በወረዳው ማህበረሰቡና ባለሀብቶችን በማስተባበር በመንገድና በትምህርት እየተከናወኑ ያሉ ስራዎችን በቀጣይ በሁሉም ዘርፍ አጠናክረው እንደሚያስቀጥሉ ተናግረዋል።

የአበሩስ የልማት ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ይብልጥ ዳኛቸው እንደገለጹት ባለሀብቱና ህብረተሰቡ በማሳተፍ በባለፈው አመት ከ10 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በላይ በማሰባሰብ መንገዱ ተሰርቶ ለትራፊክ ክፍት በማድረግ ህብረተሰቡ ተጠቃሚ ማድረግ ተችላል።

በመንገድ ችግር ህብረተሰቡ ለዘመናት ሲሰቃይ እንደነበር የጠቆሙት አቶ ይብለጥ የልማት ኮሚቴው 3 ቀበሌዎችን ማለትም ከአምባገነት -የግራሬ- ከዘበዝር ጉየ-ያውሬ እና ከጉየአቦ -ነቄጣር ቀበሌዎችና መንደሮችን በማገናኘት የህብረተሰቡ ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ኮሚቴው መስራቱን ተናግረዋል።

አቶ ብርሃኑ ተሰማና አቶ ደንድር ባባድሪና አግኝተን ያነጋገርናቸው ነዋሪዎች ሲሆኑ ከዚህ ቀደም መንገድ ባለመሰራቱ በሁሉም ዘርፍ ተሳታፊና ተጠቃሚ አንዳልነበሩ አስታውሰዋል።

አሁን ላይ መንገዱ በመሰራቱ ያመረቱት ምርት ወደ ገበያ ለማውጣት፣ እናቶች በጤና ጣቢያ እንዲወልዱና በወረዳው በሁሉም ዘርፍ ተሳታፊና ተጠቃሚ እንዲሆኑ እንዳስቻላቸው ገልጸው መንገዱም ዘላቂ አገልግሎት መስጠት እንዲችል አስፈላጊውን እንክብካቤ እንደሚያደርጉም አመልክተዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *