በጉራጌ ዞን እኖር ኤነር መገር ወረዳ በኤነር አማኑኤል ገዳም ቅጥር ግቢ የአቮካዶ ችግኞችን ተተክሏል።

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የካልም ፕሮጀክት አስተባባሪና የቢሮ ተወካይ አቶ ስለሺ ደሳለኝ በችግኝ ተከላው ተገኝተው እንዳሉት በክልሉ በአንድ ጀንበር 5ሚሊዮን ችግኞችን ለመትከል የቅድመ ዝግጅት ተደርጓል።

ሁሉም የመንግስትና የግል ተቋማት ከ100 እስከ 10 ሺህ ችግኞችን እንዲተክሉ የተጀመረው ኢንሼቲቭ በክልሉ በሁሉም ተቋማት እየተተከለ መሆኑን የገለጹት አቶ ስለሺ ይህም የአካባቢ ስነምህዳር ከመቀየር ባለፈ የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ ፋይዳው ትልቅ ነው ብለዋል።

ቢሮው ለዘርፉ ትኩረት በመስጠት እየተሰራ እንደሚገኝ ያነሱት ኃላፊው ይህ ተግባር በቀጣይም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።

በጉራጌ ዞን ግብርና መምሪያ ምክትልና የተፈጥሮ ዘርፍ ኃላፊ አቶ አድማሱ ፍቅሬ እንደገለጹት በዞኑ በበጀት አመቱ 70 ሚሊዮን ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞች ለመትከል ታቅዶ እስካሁን 68 ሚሊዮን 7 መቶ ሺህ ችግኞችን መትከል ተችሏል።

ከነዚህም 2ሚሊዮን 4መቶ ሺህ የፍራፍሬ፣ 14 ሚሊዮን የቡናና ሌሎችም የመኖና የጥምር ደን ችግኞች መተከሉንም አንስተዋል።

በክልሉ የወረደው ኢንሼቲቭ በመቀበል በዞኑ በሁሉም መንግስታዊና መንግስታዊ ባልሆኑ ተቋማት በስፋት ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑን ጠቁመው ለዚህም የፍራፍሬ ችግኞችን በመትከል ከጥላና ከውበት ባለፈ ለምግብነት እንዲውሉ በሁሉም ተቋማት በስፋት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

በዞኑ አርሶ አደሩ የ30-40-30 ኢንሼቲቭ ተቀብሎ ተግባራዊ በማድረጋቸው ከምግብ ፍጆታቸው ባለፈ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚ መሆናቸውን ያነሱት አቶ አድማሱ በዞኑ በተቋማት የተጀመረው ስራም ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ተናግረዋል።

በዞኑ ነሀሴ 17 በአንድ ጀንበር 1ሚሊዮን 150ሺህ የተለያዩ ዝርያ ያላቸው ችግኞችን ለመትከል አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት መጠናቀቁን ገልጸው ለዚህም ሁሉም የህብረተሰብ ክፍሎች በእለቱ አሻራቸውን እንዲያኖሩ አስገንዝበዋል።

የእኖር ኤነር መገር ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሸምሱ ሸሀቡ በበኩላቸው በወረዳው ከ1ነጥብ 6 ሚሊዮን በላይ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞችን ለመትከል ታቅዶ እስካሁን ከ80 በመቶ በላይ ችግኞችን ተተክሏል ብለዋል።

በወረዳው በሁሉም ተቋማት የኢኮኖሚ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞችን እንዲተክሉ እየተሰራ እንደሚገኝ የገለጹት አቶ ሸምሱ በዛሬው እለትም በኤነር አማኑኤል ገዳም 5መቶ የአቮካዶ ችግኞችን መትከል መቻሉን አስረድተዋል።

በወረዳው የሚተከሉ ችግኞች ለታለመላቸው አላማ እንዲውሉ በመንከባከብ እንዲጸድቁ ሁሉም የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ አመላክተዋል።

በወረዳው በአንድ ጀንበር ነሀሴ 17 ከ1መቶ 35 ሺህ በላይ ችግኞችን ለመትከል ቅድመ ዝግጅት መደረጉን ያነሱት አስተዳዳሪው ለዚህም ሁሉም የወረዳው ነዋሪዎች በእለቱ በመውጣት እንዲሳተፉ ጠይቀዋል።

የኤነር አማኑኤል ገዳም አበምኔት ቆሞስ አባ ገብረስላሴ ገደፋው እንደገለጹት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ደን በመጠበቅና ጠብቆ ለትውልድ በማስተላለፍ ረገድ ሚናዋ ትልቅ ነው።

በገዳሙ በዛሬው እለት የተተከሉ የአቮካዶ ችግኞችን ከጥላነት ባለፈ ለምግብነትና ለገዳሙ የገቢ ምንጭ የሚውሉ መሆናቸውን የገለጹት አበምኔቱ ችግኞቹም ለታለመላቸው አላማ እንዲውሉ ተንከባክቦ የማጽደቅ ስራ እንደሚሰራም ተናግረዋል።

በችግኝ ተከላ መርሃ ግብሩ የክልል፣ የዞኑ ግብርና መምሪያ የስራ ኃላፊዎች፣ የወረዳው አመራሮችና የማህበረሰብ ክፍሎች ተሳትፈዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *