በጉራጌ ዞን አበሽጌ ወረዳ ባለፉት ስድስት ወራት በድህነት ቀናሽ ተቋማትና በህብረተሰብ ተሳትፎ የተከናወኑ ተግባራት አፈጻጸም በባለድርሻ አካላት ተጎብኝተዋል።

በጉብኝቱ ወቅት የተገኙ መልካም ተሞክሮዎች ቀምሮ በሁሉም ቀበሌዎች በማስፋት ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ እንደሚሰራ የወረዳው አስተዳደር ገለጸ።

የመንግሰት ተቋማት ህብረተሰቡን በልማት ስራዎች ተጠቃሚ ስለማድረጋቸው ከሚያረጋግጥበት መንገድ አንዱ ወቅቱን የጠበቀ ሪፖርት መቀበል ሲሆን የሪፖርቱ ተዓማኒነት ለማረጋገጥ ደግሞ የመስክ ምልከታ ይደረጋል።

የአበሽጌ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ መላኩ ብርሃነለ በጉብኝቱ ወቅት እንደተናገሩት ባለፉት ስድስት ወራት በድህነት ቀናሽ ተቋማት እቅድ አፈጻጸም ሪፖርት መሰረት ተግባራቱ የሚገኙበት ደረጃ ለማወቅ ከወረዳው ፕላን ጽህፈት ቤት ጋር በመተባበር በተለያዩ ቀበሌዎች የመስክ ምልከታ ተደርጓል።

የመስክ ምልከታ ከተደረገባቸው ፕሮጀክቶች መካከል የመስኖ ስራ አንዱ ሲሆን በወረዳው በመደበኛ፣ በጠብታና በበጋ ስንዴ መስኖ ስራዎች የታዩ ውጤቶች አበረታች እንደሆኑ ዋና አስተዳዳሪው ገልጸዋል።

ይሁን እንጂ የመስኖ ስራው ይበልጥ ውጤታማና በአርሶ አደሩ ኑሮ ላይ መሰረታዊ ለውጥ እንዲያመጣ በትኩረት ቢሰራም አርሶ አደሮች በአሁን ወቅት እየተቸገሩበት ያለው የነዳጅ እጥረት ችግር እንዲቀረፍላቸው ወረዳው፣ ዞኑና ክልሉ እንዲሁም ባለድርሻ አካላት በቅንጅት ሊሰሩ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

የህብረተሰቡን ተሳትፎ በልማት ስራዎች ውጤታማነትና ተደራሽነት ላይ ያለው ፋይዳ ከፍተኛ በመሆኑ በተያዘው በጀት አመት በጀጀባ፣ በአቡኮ፣በቁሊት2፣በሁዳድ ሰባትና በሌሎች ቀበሌዎች የተጀመሩ የመንገድ ስራዎች በአርአያነት ይጠቀሳሉ ብለዋል።

በወረዳው በተለያዩ ቀበሌዎች የሚስተዋለው የውሃ እጥረት ችግር ደረጃ በደረጃ ለመቅረፍ በትኩረት እንደሚሰራ የገለፁት አስተዳዳሪው የዞኑ አስተዳደር ባደረገው ድጋፍ የዋልጋ ንጹሕ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ቁፋሮ ስራ እየተከናወነ እንደሚገኝ አብራርተዋል።

በተቋማቱ የእቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ላይ ተግባራት በተጨባጭ ስለመኖራቸው በጉብኝቱ ወቅት ማረጋገጥ የተቻለ በመሆኑ በጉብኝቱ ወቅት የተገኙ መልካም ተሞክሮዎች በመቀመር በሌሎች ቀበሌዎች ተግባራዊ ለማድረግና ጉድለቶችን ለመሙላት በትኩረት ይሰራል። ይህ ደግሞ የውሸት ሪፖርት ለመከላከል ያስችላል ብለዋል።

ዜጎች በልማት ስራዎች ተጠቃሚ እንዲሆኑ አንድነታቸው በማጠናከር የአካባቢያቸውን ሰላም መጠበቅ እንዳለባቸው አሳስበዋል።

የወረዳው ፕላንና ልማት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሺመልስ አይተንፍሱ በበኩላቸው የመስክ ምልከታው ተቋማት ከዘልማዳዊ አሰራር ተላቀው አሰራራቸውን በማዘመን ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ ያስችላል ብለዋል።

የተቋማቱ የስድስት ወራት እቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ከተገመገመ ወዲህ በሪፖርቱ የሰፈሩት አፈጻጸሞች ለመከታተል በተደረገው የመስክ ምልከታ ጠንካራና ደካማ አፈጻጸም ያላቸው ፕሮጀክቶች ለመለየት እንዳስቻላቸው ገልጸዋል።

የተቋማቱ አፈጻጸም በማሳደግ ህብረተሰቡ በልማትና በመልካም አስተዳደር ስራዎች ተጠቃሚ ለማድረግ ድጋፍና ክትትል ሲሆን አፈጻጸማቸው መሰረት ያደረገ ግብረ መልስ እንደሚሰጥ አስረድተዋል ።

የማህበረሰብ አቅም እንደ ካፒታል አቅም በመጠቀም ህዝቡ የሚጠይቃቸው የልማት ጥያቄዎች ምላሽ እንዲያገኙ ማስቻሉን አቶ ሺመልስ ገልጸዋል።

የወረዳው የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ብዛኒ ግርማ የወረዳው ህብረተሰብ መንግስት በልማትና በመልካም አስተዳደር ስራዎች ተጠቃሚ ለማድረግ አየተሰሩ ያሉ መልካም ስራዎች ህብረተሰቡ እንዲያውቃቸው መረጃ እንዲኖረው እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል።

ተማሪዎች ብቁ ተወዳዳሪና በራሳቸው የሚተማመኑ ሀገር ተረካቢ ዜጋ እንዲሆኑ በቴክኖሎጂው ዘርፍ እየተሰሩ ያሉ ስራዎች አበረታች እንደሆኑ ገልጸዋል። በመሆኑም የትምህርት ተቋማት አቅም ለማጎልበትና ተተኪ ትውልድ ለማፍራት አስፈላጊውን ድጋፍ ሊደረግላቸው እንደሚገባ ተናግረዋል።

የመስክ ምልከታውን በርካታ ልምዶች የተገኙበት በመሆኑ በጥንካሬ የተለዩ አፈጻጸሞች ለማስቀጠል እና በድክመት የተለዩ አፈጻጸሞች ለማረም ልምድ አግኝተንበታል ብለዋል።

= ኢትዮጵያን እናልማ!
= የፈረሰውን እንገንባ!
= ለፈተና እንዘጋጅ!

በተጨማሪም እነዚህ ሊንኮችን በመጫን ወቅታዊና ትኩስ መረጃዎቻችንን እንድትከታተሉ እንጋብዛለን፡፡

Facebook:- https://www.facebook.com/gurage1Zone
Website:- https://gurage.gov.et
Telegram:- https://t.me/comminuca
Youtub: -https://www.youtube.com/channel/UCzrcazGv

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *