በጉራጌ ዞን አረንጓዴ አሻራችን ለትውልዳችን በሚል መሪ ቃል በአንድ ጀንበር ከ19 ሚሊዮን በላይ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞችን መተከሉን የጉራጌ ዞን አስተዳደር አስታወቀ።

ይህ የተናገሩት በጉራጌ ዞን እዣ ወረዳ ዞን አቀፍ የአንድ ጀንበር የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር በስራይ ቀበሌ በይፋ በተጀመረበት ወቅት ላይ ነው።

ከችግኝ ተከላ ጎን ለጎን የመኸር ስራዎችንም አጠናክሮ በማስቀጠል ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ እንደሚገባ የደቡብ ክልል ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ተስፋዬ ብላቱ ገለጹ።

የጉራጌ ዞን ምክትል አስተዳዳሪና የግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ አበራ ወንድሙ በዞኑ በአንድ ጀንበር ከ19 ነጥብ 9 ሚሊዮን ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞችን መተከሉን ገልፀው በዚህም በሁሉም ወረዳና ከተማ አስተዳደር የሚገኙ ከ4 መቶ ሺ በላይ የህብረተሰብ ክፍሎች መሳተፋቸውንም ተናግረዋል።

የአርሶ አደሩን የምግብ ዋስትናን ሊያረጋግጡ የሚችሉና የኢኮኖሚ ችግር መፍታት የሚያስችሉ የ30_40_30 የፍራፍሬ ፕሮጀክት መጀመሩን የዘንድሮው የአረንጓዴ ልማት ለየት እንደሚያደርገው ገልፀው ከ9መቶ በላይ በአጭር ጊዜ የሚደርሱ የአቮካዶ፣ የፓፓያ፣ የአፕል ችግኞችና የሙዝ ፍራፍሬ ዝርያዎችን ወደ ዞኑ በማስገባት ለአርሶ አደሩ ተደራሽ ማድረግ ተችሏል ብለዋል።

በዘንድሮ አመት ከ70ሺ በላይ የሙዝ ተክሎችን ወደ ዞን በማስገባት ለአርሶ አደሩ ተደራሽ መደረጉን የገለፁት አቶ አበራ አርሶ አደሩ ለእንክብካቤ፣ ለበሽታ ቁጥጥርና ለገበያ በተሻለ መንገድ ለማቅረብ እንዲያመቸው በመንደር መተከሉና በዚህም የተሻለ ስራ መሰራቱንም ተናግረዋል።

ከአቮካዶ አንፃር በዞኑ በተለይም መስቃን አከባቢ የአቮካዶ ምርት በማምረት ወደ ውጪ መላክ መጀመራቸውን ጠቁመው በዚህም ተግባር ወጣቱና ባለሀብቱ በመደራጀት ኢንቨስት እያደረጉ መሆኑና ተግባሩም በቀጣይ በሁሉም የገጠር ወረዳዎች ላይ ለማስፋት እንደሚሰራም አመላክተዋል።

የዞኑ ማህበረሰብ ችግኝ የመትከልና የመንከባከብ ስራው ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱን ገልፀው በበጋ ወቅት ውሃ በማጠጣት፣ በመኮትኮት በኔነት ስሜት እያደረጉት ያለው ተግባር በቀጣይም የበለጠ እንዲያድግ እንደሚሰራም ተናግረዋል።

የደቡብ ክልል ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ተስፋዬ ብላቱ በበኩላቸው በክልሉ በአንድ ጀንበር 1መቶ ሚሊዮን ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞችን መተከሉን ገልፀው በዞኑም 19 ነጥብ 9 ችግኞችን መተከላቸውን አመላክተዋል።

በዚህም የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ላይ ህፃናት፣ ወጣቶች፣ ሴቶች፣ የአከባቢ ሽማግሌዎ፣ የሀይማኖት አባቶች፣ ሙህራን፣ ፓለቲከኞችና የመንግስት ሰራተኞችና ሌሎችም መሳተፋቸውን ተናግረዋል።

ችግኝ መትከል ካለው ዘርፈ ጠቀሜታ አንፃር በተለይም የአከባቢ ስነ ምህር ከመጠበቅና ምርትና ምርታማነትን በማሳደጉ ረገድ ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለው በመረዳት የአንድ ጊዜ ተግባር ብቻ ሳይሆን የሁል ጊዜ ተግባር በማድረግ አጠናክሮ ማስቀጠል ያስፈልጋል ብለዋል።

ከችግኝ ተከላው ጎን ለጎን የመኸር ስራዎችን መስራት እንደሚገባ የገለጹት ኃላፊው ምርትና ምርታማነትን ሊያሳድጉ የሚችሉ የተሻሻሉ ዝሪያዎችና ቴክኖሎጂዎችን እንዲሁም የኩታ ገጠም የአስተራረስ ዘዴ መጠቀም ያስፈልጋል።

እንደ አቶ ተስፋዬ ገለፃ በበጋ የመስኖ ስራ ላይ የነበረው ቅንጅት በመኸርም አጠናክሮ በማስቀጠል ምርትና ምርታማነት ማሳደግ እንደሚገባ አውስተው በበልግ ወቅት ያጋጠሙ ማነቆዎችን በመፍታት በመኸር ስራ ለማካካስ በትኩረት መስራት እንደሚገባም አመላክተዋል።

በዞኑ የተጀመሩ የክረምንት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ስራዎች ይበልጥ በማጠናከር አቅመ ደካሞችና አረጋውያን በመደገፍ፣ ቤት በመጠገንና በመስራት፣ ችግኝ በመትከል፣ ደም በመለገስና በሌሎችም ስራዎች ላይ ወጣቶች የበለጠ እንዲሳተፉም አሳስበዋል።

በመረጃ ምንጭነት ገፃችን ምርጫዎ ስላደረጉ እናመሰግናለን!
= ኢትዮጵያን እናልማ!
= የፈረሰውን እንገንባ!
= ለፈተና እንዘጋጅ!
በተጨማሪም እነዚህ ሊንኮችን በመጫን ወቅታዊና ትኩስ መረጃዎቻችንን እንድትከታተሉ እንጋብዛለን፡፡
Facebook:- https://www.facebook.com/gurage1Zone
Website:- https://gurage.gov.et
Telegram:- https://t.me/comminuca
Youtub:- https://youtube.com/channel/UCzrcazGvvIO2tG7bQN36CxQ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *