በጉራጌ ዞን ነሀሴ 17 በአንድ ጀንበር ከ1 ሚሊዮን በላይ ችግኞችን ለመትከል አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት መደረጉን የጉራጌ ዞን ግብርና መምሪያ አስታወቀ።


በዞኑ እዣ ወረዳ ኔሸ ቀበሌ ነሀሴ 17 የሚካሄደው የአንድ ጀንበር የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር የቅድመ ዝግጅት ስራዎችን ምልከታ ተደርጓል።

የአንድ ጀንበር የችግኝ ተከላ መርሃ ግብሩ ውጤታማ እንዲሆን ሁሉም የዞኑ ማህበረሰብ በነቂስ በመውጣት አሻራውን ማኖር እንዳለባቸው ተገለጸ።

የጉራጌ ዞን ምክትል አስተዳዳሪና የግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ አበራ ወንድሙ እንዳሉት በዞኑ በ2016 ዓ.ም በአረንጓዴ ልማት አሻራ ስራ 70 ሚሊዮን ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞችን ለመትከል መታቀዱን ገልጸው እስካሁን ከ65 ሚሊዮን በላይ ችግኞችን መትከል ተችላል።

እንደ ሀገር በዞኑ የዘንድሮ የአንድ ጀንበር የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ለየት የሚያደርገው በginous book of record የሚመዘገብ ሲሆን ይህም በቦታ ስፋት፣ በህዝብ ተሳትፎና በችግኝ ተከላ መጠን መሆኑን ገልጸዋል።

በዚህም በዞኑ ነሀሴ 17 በአንድ ጀንበር የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ከአንድ ሚሊዮን በላይ ችግኞችን ለመትከል የታቀደ ሲሆን በዚህም ከ230 ሺህ በላይ የዞኑ ማህበረሰብ እንደሚሳተፍም አስረድተዋል።

የአንድ ጀንበር የችግኝ ተከላው በJinous book of record ለማስመዝገብ በዞኑ ከ20 ሄክታር በላይ ስፋት ያላቸው ወረዳዎች የተመረጡ ሲሆን እነዚህም ምሁር አክሊል 31ነጥብ 5 ሄክታር፣ እዣ 25 ሄክታር፣ ገደባኖ ጉታዘር ወለኔ ወረዳ 36 ሄክታር መሆኑን ተናግረዋል።

የግብርና ምርትና ምርታማነት፣ የገጸና የከርሰ ምድር ውሃ ለማሳደግ የደን ሽፋን ማሳደግ ይገባል ያሉት አቶ አበራ መትከል ብቻ ሳይሆን የተተከሉ ችግሮች የጽድቀት መጠናቸው ከፍ እንዲል ማህበረሰቡ እየሰራቸው ያሉ ስራዎች በማጠናከር መስራት እንዳለበት አመላክተዋል።

እንደ ሀገር በአንድ ጀንበር የሚተከለው የችግኝ ተከላ መርሃ ግብሩ ላይ ሁሉም የዞኑ ማህበረሰብ በመውጣት አሻራቸውን እንዲያኖሩ አሳስበዋል።

በመምሪያው ምክትልና የተፈጥሮ ዘርፍ ኃላፊ አቶ አድማሱ ፍቅሬ በበኩላቸው በአንድ ጀንበር የችግኝ ተከላ መርሃ ግብሩ በዞኑ ከ20 ሄክታር መሬት ስፋት ያላቸው ምሁር አክሊል፣ እዣ ገደባኖና ጉታዘር ወለኔ ወረዳ በሄክታር ስፋት የተመረጡ ሲሆን እንደ ሀገር በginous book of record የሚመዘገቡ መሆናቸውንም አንስተዋል።

ለዚህም የጉድጓድና የተለያዩ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞችን ቅድመ ዝግጅት መደረጉን አመላክተዋል።

ችግኞቹ ከደንነት ባለፈ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞችን ለመትከል ቅድመ ዝግጅት ከማድረግ ባለፈ የጽድቀት መጠናቸው ከፍ እንዲል ቦታው የማጠርና የመከለል ስራ እየተሰራ ነው ብለዋል።

አፈር እንዳይሸረርና የአየር ሁኔታ ለማስተካከል ችግኝ መትከል ፋይዳው ከፍ ያለ ነው ያሉት አቶ አድማሱ ለዚህም ሁሉም በእለቱ እንዲሳተፉ ጠቁመዋል።

የእዣ ወረዳ ግብርና ልማት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ መቻል ተሰማ በወረዳው በ2016 በጀት አመት 9 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞችን ለመትከል በማቀድ እስካሁን 85 በመቶ መትከል የተቻለ ሲሆን የተቀረው ነሀሴ 17 በአንድ ጀንበር ይተከላል።

በዚህም የአንድ ጀንበር የችግኝ ተከላ መርሃ ግብሩ በወረዳው ኔሸ ቀበሌ በ25 ሄክታር መሬት ለመትከል የጉድጓድ፣ የችግኝና ቦታው የመከለል የቅድመ ዝግጅት ስራዎችን መደረጉንም ተናግረዋል።

የወረዳው ማህበረሰብ ችግኝ የመትከል፣ ተንከባክቦ የማጽደቅ ልምድ ያለው መሆኑን ያነሱት ኃላፊው የአንድ ጀንበር የችግኝ ተከላ መርሃ ግብሩ ውጤታማ እንዲሆን ማህበረሰቡ በእለቱ በመውጣት አሻራቸውን እንዲያኖሩም አስገንዝበዋል።

በቀበሌው ቅድመ ዝግጅት ሲያደርጉ አግኝተን ያነጋገርናቸው ነዋሪዎች እንዳሉት የአንድ ጀንበር የችግኝ ተከላ መርሃ ግብሩ አስፈላጊውን የጉድጓድ ቅድመ ዝግጅት ከማድረጋቸውም ባለፈ ቦታው ከእንሰሳና ከሰው ንክኪ ነጻ እንዲሆን የመከለል ስራ እየሰሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በእለቱም ከዚህ ቀደም በችግኝ ተከላ ያላቸው ልምድ በመጠቀም የተለያዩ አደረጃጀቶችን በመጠቀም እቅዱ ውጤታማ እንዲሆን ለመትከል መዘጋጀታቸውም ገልጸዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *