በጉራጌ ዞን ቸሃ ወረዳ 14 ቀበሌን ማስጠቀም የሚችል የንፁህ መጠጥ ውሀ ፕሮጀክት በሁለት ምዕራፍ ተሰርቶ ተጠናቀቀ።

ህዝቡ ዘንድ ከፍተኛ የመልካም አስተዳደር ችግር ፈጥሮ የነበረው የመገናሴ ሉቄ የንፁህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ተጠናቆ ለአገልግሎት ክፍት ከመደረጉ በፊት ፕሮጀክቱን የሚያስተዳድር ቦርድ መዋቀሩም የጉራጌ ዉሃ ማዕድንና ኢነርጂ መምሪያ አስታወቀ።

የጉራጌ ዞን ውሀ ማዕድንና ኢነርጂ መምሪያ ሀላፊ አቶ ፍሰሀ ዳምጠው እንዳሉት የህብረተሰቡ የንጹህ መጠጥ ዉሃ ችግር ለመቅረፍ በትኩረት እየተሰራ ነዉ።

በ2008 ዓመተ ምህረት በደቡብ ኮሪያ መንግስት በ6 ነጥብ 2 ሚሊዮን ዶላር የበጀት ድጋፍ መገር አዶሼ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክት በተቋራጩ ችግር ምክንያት ግንባታው ዘግይቶ መቆየት ይታወቃል።

ይህንንም ግንባታ ለማከናወን የዞኑ ውሃ ማዕድንና ኢነርጂ መምሪያ ውሉን ከተቋራጩ በመሰረዝ ለፕሮጀክቱ ማጠናቀቂያ 200 ሺህ ዶላር ከኮሪያ መንግስት በተገኘ ድጋፍ ግንባታዉ በሁለት ምዕራፍ በመክፈል ማጠናቀቅ መቻሉን አስረድተዋል።

ይህንንም የዉሃ ፕሮጀክት ለማህበረሰቡ አገልግሎት በተገቢዉ አገልግሎት እንዲሰጡ ማስተዳደር ያለበት ህዝቡ በመሆኑ ፕሮጀክቱን የሚያስተዳድር ቦርድ ማቋቋም አስፈላጊ መሆኑ የገለፁት አቶ ፍሰሀ የተቋቋመው ቦርድም ተግባርና ሀላፊነቱን ወስዶ ፕሮጀክቱን ማስተዳደር እንዳለበት አሳስበዋል።

የቸሃ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሙራድ ከድር በበኩላቸው ይህን ፕሮጀክት እንዲሳካ የዞን ዉሃ ማዕድንና ኢነርጂ መምሪያ ያደረገው አስተዋጽ በማመስገን እንደ ወረዳ መንግስት የአርሶ አደሩን ችግር ለመፍታት በርካታ ተግባራቶች እየተከናወኑ እንደሆነም አብራርተዋል።

አታካች የሆኑ በወቅታዊና በሰው ሰራሽ ችግሮች ፕሮጀክቱ እስካሁን ዘግይቶ መቆየቱን የጠቀሱት አቶ ሙራድ ለፕሮጀክቱ የቦርድ አባላት ችግሩን እንደቀመሰ አካል ተግባርና ሀላፊነታቸውን መወጣት እንዳለባቸው አሳስበዋል።

የወረዳው መንግስትም በጀት ከመመደብ ጀምሮ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ አቶ ሙራድ አስረድተዋል።

የጉራጌ ዞን አስተዳደር አማካሪ አቶ ፈቱ አብዶ በበኩላቸዉ ከአሁን በኋላ ያለው ተግባር የመንግስትና የማህበረሰቡ ቅንጅት ወሳኝ በመሆኑ በባለቤትነት መሰራት ይገባል ብለዋል።

የተገኘውን መልካም አጋጣሚ በመጠቀም ማህበረሰቡን በማንቀሳቀስ ፕሮጀክቱ በፋይናንስ እራሱን እንዲችል መሰራት አለበትም አሳስበዋል።

በአዲሰ መልክ የተዋቀሩት የቦርድ አባላት አንደገለጹት ህብረተሰቡ ተቋማትን የመንከባከብ እና የመጠበቅ ግዴታ እንዳለበት በመግለፅ ሀላፊነታቸውን ለመወጣት መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።

የቦርድ አባላቱ መተዳደሪያ ደንብ በአቶ አብድልፈታ ያሲን የመጠጥ ውሀ አስተዳደርና መሳሪያዎች ጥገና ዋና ስራ ሂደት አስተባባሪ እና የፕሮጀክቱ አጭር ሪፖርት በአቶ ዮሀንስ መለሰ የመምሪያው ም/ሀላፊና የመጠጥ ውሀ ዘርፍ ሀላፊ ቀርቦ ውይይት መደረጉንና የውሃ ማጠራቀሚያ ታንከሮች ተጎብኝተዋል ሲል የዘገበዉ የጉራጌ ዞን የመንግስት ኮሚኒኬሽን መምሪያ ነዉ።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *