በጉራጌ ዞን ቸሃ ወረዳ በመኸርና በበልግ እርሻ ልማት የለማው የጤፍና የበቆሎ ማሳዎች የመስክ ምልከታ ተካሄደ።

የጉራጌ ዞን ምክትል አስተዳደሪና የግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ አበራ ወንድሙ እንዳሉት በዞኑ በመኸር እርሻ ልማት በጤፍ ከ21 ሺህ ሄክታር መሬት በላይ በዘር የተሸፈነ ሲሆን ከዚህም ከ16 ሺህ ሄክታር መሬት በላይ በኩታ ገጠም ማልማት ተችሏል።

በዚህም 4ነጥብ 8 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ይጠበቃል ብለዋል።

በበልግ እርሻ ልማት በበቆሎ ከ40 ሺህ ሄክታር መሬት በላይ የለማ ሲሆን ከ35 ሺህ ሄክታር በላይ በኩታ ገጠም ማልማት መቻሉን ያነሱት አቶ አበራ ከዚህም ከ7ነጥብ 1 ሚሊዮን በላይ ኩንታል ምርት እንደሚጠበቅ ገልጸዋል።

አርሶ አደሩ ያመረተውን ምርት ወደ ጎተራ እስኪገባ ድረስ ከማሳቸው ሳይነጠሉ መንከባከብና መከታታተል እንዳለባቸው ጠቅሰው መምሪያውም የአርሶ አደሩ ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የጀመረው ስራ አጠናክሮ እንደሚያስቀጥል ተናግረዋል።

የቸሃ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ጥላሁን ሽምንሳ በበኩላቸው በወረዳው በዘርፉ የአርሶ አደሩ የምግብ ዋስትና ከማረጋገጥ ባለፈ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚ እንዲሆኑ እየተሰራ ያለው ስራ አበረታች ነው ብለዋል።

የመስክ ምልከታው አላማ ምልከታ በተደረገባቸው ቀበሌዎች ያለውን ምርጥ ተሞክሮ ወደ ሌሎች ቀበሌዎች ለማስፋፋት ያለመ መሆኑንም አስረድተዋል።

ሁሉም ቀበሌዎች ያላቸውን ጸጋ በተገቢው በመጠቀም ምርትና ምርታማነት በማሳደግ አሁን ላይ ያለው የገበያ ንረት ከማረጋጋት ባለፈ ከተረጂነት ለመላቀቅ በዘርፉ እየተሰራ ያለው ስራ ይበልጥ ለማጠናከር በትኩረት እንደሚሰራ ተናግረዋል።

በወረዳው የግብርና ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አህመድ መሀሙድ በወረዳው በመኸር እርሻ ልማት በጤፍ ከለማው 4ሺህ 584 ሄክታር መሬት ውስጥ 2ሺህ 160 በኩታገጠም በማልማት በዚህም 82 ሺህ512 ኩንታል ምርት ይጠበቃል ብለዋል።

በበልግ እርሻ ልማት 1ሺህ 25 ሄክታር መሬት በበቆሎ በመሸፈን ከዚህም 1መቶ 13 ሺህ 310 ኩንታል ምርት እንደሚጠበቅ አንስተዋል።

አርሶ አደሩ በዘርፉ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማስቻል የባለሙያ ድጋፍና ክትትል ከማድረግ ባለፈ ግብአት በወቅቱ እንዲያገኙ ስራዎች መሰራታቸው ጠቁመዋል።

በመስክ ምልከታው ወቅት አግኝተን ያነጋጋገርናቸው አርሶ አደሮች እንዳሉት ከማሳ ዝግጅት ጀምሮ የግብርና ባለሙያዎች የሚሰጧቸውን ምክረ ሀሳብ በተገቢው በመጠቀም በሰሩት ስራ ማሳቸው በምርጥ ቁመና ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

በዘርፉ በትኩረት በመስራት ምርትና ምርታማነት ከማሳደግ ባለፈ የገበያ ንረት ለማረጋጋት ተግተው እንደሚሰሩም አንስተዋል።

የመስክ ምልከታው ተሳታፊዎች እንደገለጹት በቀበሌዎቹ ተዟዙረው ያዩትን ምርጥ ተሞክሮ ወደ ቀበሌያቸው ወስደው አስፍተው እንደሚሰሩ ተናግረዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *