ጥር 15/2015
በጉራጌ ዞን ቸሀ ወረዳ የግራርሰነ የንጹህ መጠጥ፣ የግልና የአካባቢ ንጽህና አጠባበቅ ፕሮጀክት ማብሰሪያ ፕሮግራም ተካሂዷል ።
በኢትዮጵያ ካቶሊክዊት ቤተክርስቲያን የእምድብር ሀገረ ስብከት የመንግስትን የልማት ክፍተት በመሙላት ህብረተሰቡን ተጠቃሚ በሚያደርጉ የልማት ስራዎች እየተሳተፈች መሆኗን የጉራጌ ዞን አስተዳደር ገለፀ።
ፕሮጀክቱ ከጀርመን የካቶሊክ ጳጳሳት ጉባኤ በተገኘ ከ48 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ የሚገነባ እንደሆነና ከ15 ሺህ በላይ የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ሊያደር እንደሚችል ተመልክቷል ።
የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ላጫ ጋሩማ እንዳሉት የህብረተሰቡ የረጅም ጊዜ የንፁህ መጠጥ ውኃ ችግር ሊቀርፍ የሚችል የግራርሰነ የንጹህ መጠጥ ውኃ፣ የግልና የአካባቢ ንጽህና አጠባበቅ ፕሮጀክት መሠረተ ድንጋይ መጣል በመቻላቸው ከፍተኛ ደስታ እንደተሠማቸው ገልፀዋል ።
የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ከመንፈሳዊ አገልግሎቶች ባሻገር በንፁህ መጠጥ ውሃ ፣በግብርና ፣ በትምህርትና በሌሎችም የልማት ስራዎች በዞኑ በተለያዩ ወረዳዎች በማከናወን የህብረተሰቡን ችግር እየቀረፉ እንደሆነ ገልጸዋል ።
ቤተክርስቲያኗ ፕሮጀክቶችን ከመጀመር ባሻገር በጥራት በተባለው ጊዜ በመጨረስ ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግና የመንግስት የልማትን ክፍተት ለመሙላት እያከናወነች ያለዉ ተግባር ከፍተኛ መሆኑን አቶ ለጫ ጋሩማ ተናግረዋል ።
ፕሮጀክቱ በታለመለት ጊዜና በጥራት ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት እንዲችል የዞኑ መንግስት አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን ገልጸዋል።
የቸሀ ወረዳ ዋና አሰተዳደር አቶ ጥላሁን ሽምንሳ በበኩላቸው ከኢትዮጵያ ካቶሊክዊት ቤተክርስቲያን የእምድብር ሀገረ ስብከት በወረዳው በተለያዩ ቀበሌዎች በውሀ፣ በጤና ፣በትምህርት የሚስተዋሉ ችግሮችን በመቅረፍ ከ 15 ዓመት በላይ ህብረተሰባችንን ተጠቃሚ አያደረጉ መሆኑን ተናግረዋል ።
የግራርሰነ የንጹህ መጠጥ ውኃ ፣ የግልና የአካባቢ ንጽህና አጠባበቅ ፕሮጀክት 48 ሚሊየን 456 ሺ 81ብር የሚገነባ እንደሆነ አቶ ጥላሁን ሽምንሳ ገልጸዋል ።
ፕሮጀክቱ በአራት ቀበሌዎች ለሚኖሩ ከ15 ሺህ በላይ ለሚሆኑ የህብረተብ ክፍሎች የንፁህ መጠጥ ውኃ ችግር እንደሚቀርፍ አመላክተዋል ።
በኢትዮጵያ ካቶሊክዊት ቤተክርስቲያን የእምድብር ሀገረ ስብከት ጳጳስ አቡነ ሙሴ እንደገለጹት ውሃ የሠው ልጅ ጤናማ ህይወት እንዲኖር እጅግ አስፈላጊ በመሆኑ ቤተክርስቲያኗ ዘር፣ ቀለም ፣ሀይማኖት ሳትለይ ሁለም ዜጋ በጋራና በፍቅር የሚጠቀሙባቸውን የልማት ስራዎች እየሰራች ነው ብለዋል ።
ይህን ልማት ተግባር መስራት የተቻለው አሁን ላይ በተገኘው ሰላም ምክንያት በመሆኑ ሁሉም ህብረተሰብ ለሰላም ዘብ መቆም እንዳለበት የተናገሩት ጳጳስ አቡነ ሙሴ ፕሮጀክቱ ተጀምሮ እንዲጠናቀቅ ሁሉም የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል ።
ፕሮጀክቱ ተጠቃሚ ከሚያደርጋቸው የህብረተሰብ ክፍሎች መካከል ወ/ሮ ዘነበች ብዛኒ ፣ወ/ሮ አዳነች ስፍር እና ቄስ ትዳሩ ተክሌ በሰጡት አስተያየት በአካባቢያቸው የነበረውን የንጹህ መጠጥ ውሃ ችግር ለመቅረፍ የመሠተ ድንጋይ በመጣሉ መደሰታቸውን ተናግረዋል።
ፕሮጀክቱ አውን እንዲሆን በጉልበትም ሆነ በብር የሚጠበቅባቸውን ሁሉ ለማድረግ መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።
ፕሮጀክቱ በአራት ቀበሌዎች ለሚገኙ ከ15ሺ 2መቶ በላይ የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ሊያደርግ እንደሚችልና ለ3 ዓመት ያህል ጊዜ እንደሚቆይ በየኢትዮጵያ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን የእምድብር ሀገረ ስብከት ጠቅላይ ፅህፈት መረጃ እንደሚያመላክት የዘገበው ጉራጌ ዞን የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ነው።
እነዚህ ሊንኮችን በመጫን ወቅታዊና ትኩስ መረጃዎቻችንን እንድትከታተሉ እንጋብዛለን፡፡
Facebook:- https://www.facebook.com/gurage1Zone
Website:- https://gurage.gov.et
Telegram:- https://t.me/comminuca
Youtub: -https://www.youtube.com/channel/UCzrcazGvvIO2tG7bQN
ቲዊተር- https://4pvf.short.gy/bTJNNn