በጉራጌ ዞን ቸሀ ወረዳ በክልሉ መንግስት በጀት በ15 ሚሊየን ብር የተገነባው የወዲቶ ከተማ ጤና ጣበያ ተመርቆ አገልግሎት መስጠት ጀመረ።

በምርቃቱ የተገኙት የማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ ኃላፊ አቶ ሽመልስ ዋንጌሮ እንደገለፁት በጤና ጣበያው በተለይ እናቶችና ህጻናት ሞት ለመቀነስ፣በየጊዜው የሚከሰቱ በሽታዎችን በአፋጣኝ መቆጣጠር፣የአካባቢ ንጽህና የመጠበቅና ሌሎችም የጤና ተግባራት አጠናክሮ መስራት ያስፈልጋል ብለዋል።

ማህበራዊ ብልጽግናን ለማረጋገጥ ጤና ጣበያው ከፍተኛ ሚና ይጫወታል ነው ያሉት።

አቶ ሽመልስ አክለውም ክልሉም ለጤና ጣበያው አስፈላጊ ድጋፍ የሚያደርግ ሲሆን የህብረተሰቡ ጤና ለመጠበቅ የጤና አገልግሎት ሰጪ ተቋማት የበለጠ ማጠናከር እንደሚገባ ገልጸዋል።

የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ላጫ ጋሩማ እንደተናገሩት የአካባቢው ማህበረሰብ ለብዙ ጊዜ ከመንግስት ጎን በመሆን በርካታ የመሰረተ ልማት ስራ የሚያከናውን ሲሆን ይህንን በማጠናከር ከተማውንና አካባቢውን ማልማት ይጠበቅበታል።

ማህበረሰባችን ሁል ጊዜ የተረጂነት አስተሳሰብ በመጸየፍ በራስ ጥረት ሰርቶ መለወጥ የሚያምን ሲሆን መንግስት ድህነትን ለማጥፋት በሚያደርገው ትግል ህብረተሰቡ የመደጋገፍ ባህሉ የበለጠ ሊዳብር እንደሚገባ ተናግረዋል።

አቶ ላጫ አክለውም ጤና ጣበያው የሚጠበቅበትን አገልግሎት ለመስጠት ህብረተሰቡ፣መንግስትና ባለሀብቱ አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደርጉለት አሳስበዋል።

የቸሀ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ጥላሁን ሽምንሳ በንግግራቸው ወቅት ማህበረሰቡ ከዚህ በፊት የህክምና አገልግሎት ለማግኘት እስከ 10 ኪሎ ሜትር እርቀት ይጓዝ የነበረ ሲሆን በተለይ በእናቶች ላይ ይደርስ የነበረው እንግልት ቀላል አልነበረም ነው ያሉት።

በመሆኑም ጤና ጣበያው በመሰራቱ የአካባቢው ማህበረሰብ ይደርስበት የነበረው የጤና እክል የሚቀርፍ ሲሆን ከ21 ሺ በላይ የህብረተሰብ ክፍሎች እንደሚያስጠቅም ገልጸዋል።

ጤና ጣበያው ከ15 ሚሊየን ብር በላይ የፈጀ ሲሆን የወረዳው የጤና አገልግሎት ሽፋን ከፍ ያደርገዋል ያሉት አቶ ጥላሁን በቀጣይም የሚያስፈልጉ የህክምና ቁሳቁሶች ለማሟላት ሁሉም እርብርብ ሊያደርግ ይገባል ብለዋል።

የአካባቢው ተወላጅና ኮንተራክተር ኢንጅነር መስፍን ዋልጋ ጤና ጣበያው ከዚህ በፊት በህብረተሰቡ ይደርስ የነበረው ሞትና እንግልት የሚያስቀር ሲሆን በተለይ ባለሀብቱ መንግስት ሳይጠብቅ መሰል አይነት የልማት ስራዎች መስራት ይኖርበታል ሲሉ ተናግረዋል።

በቀጣይም ለጤና ጣበያው አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ እንደሚያደርጉ እና ለጊዜው ለመድሀኒት መግዣ ግማሽ ሚሊየን ብር አበርክተዋል።

የአካባቢው ነዋሪዎች በጋራ በሰጡት ሀሳብ ከዚህ በፊት ጤና ጣበያው ባለመኖሩ በቂ የሆነ የጤና አገልግሎት እንደማያገኙ አብራርተው በቀጣይ ግን ይህንን ችግር በመቅረፍ የተሻለ የጤና አገልግሎት እንድናገኝ ያስችለናል ብለዋል።

በጤና ጣበያውም አስፈላጊው አገልግሎት ለማግኘት አስፈላጊውን ሁሉ እናደርጋለን ሲሉ አስታውቀዋል።

በእለቱም ለጤና ጣበያው ስራ አስተዋጾ ላደረጉ አካላት እውቅናና ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *