በጉራጌ ዞን ባለፉት አመታት ያጋጠመውን የተማሪዎች ውጤት ስብራት ለማሻሻል የሚያስችል ተጨማሪ የማጠናከሪያ ትምህርት ለመስጠት እየሰራ መሆኑን የዞኑ ትምህርት መምሪያ አስታወቀ፡፡

የጉራጌ ዞን ትምህርት መምሪያ ከወልቂጤ ዩኒቨርስቲ ጋር በመተባበር በዞኑ በሚገኙ 12 የሁለተኛ ደረጃ ት/ቤቶች ላይ የማጠናከሪያ ትምህርት ለመስጠት የሚያስችል ኦረንቴሽን ለባለድርሻ አካላት በወልቂጤ ከተማ መስጠቱን ተጠቁሟል፡፡

የጉራጌ ዞን ትምህርት መምሪያ ኃላፊ አቶ መብራቴ ወ/ማሪያም በኦረንቴሽን መድረኩ ላይ እንዳሉት ዞኑ ያለውን ውስን ሀብትና መምህራን በመጠቀም የመማር ማስተማር ስራ በማጠናከር ባለፉት አመታት ያጋጠመውን የተማሪዎች ውጤት ስብራት ለመጠገን ከመቼውም ጊዜ በላይ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ይገኛል፡፡

በዚህም ከአቅም በላይ በሆኑ ምክንያቶች የባከኑ የትምህርት ክፍለ ጊዜዎች የማካካሻ ትምህርት በመስጠት የትምህርት ብክነት መከላከል፣ በት/ቤቶቹ በቅዳሜ እንዲሁም በተቃራኒ ፈረቃ መደበኛ የማጠናከሪያ ትምህርት እየተሰጠ ይገኛል፡፡

በተያያዘ በዞኑ በሚገኙ 12 የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ላይ ከ10ኛ እስከ 12ኛ ክፍል ላሉ የተፈጥሮ ሳይንስ ተማሪዎች ከወልቂጤ ዩኒቨርስቲ ጋር በመተባበር በዩኒቨርስቲው የተሻለ ልምድና እውቀት ባላቸው መምህራኖች ከየካቲት 30/2016 ዓመተ ምህረት ጀምሮ ልዩ የማጠናከሪያ ትምህርት በየሳምንቱ ቅዳሜ ለተከታታይ 18 ሳምንታት ለመስጠት የሚያስችል ኦረንቴሽን ለባለድርሻ አካላት ዛሬ መሰጠቱን ኃላፊው ገልጸዋል፡፡

በመሆኑም የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች ለሀገር አቀፍ የሁለተኛ ደረጃ መልቀቂያ ፈተና በጥሩ ሁኔታ ለመዘጋጀት እንደሚረዳቸውም ጠቁመዋል፡፡

የወልቂጤ ዩኒቨርስቲ ለዞኑ የትምህርት ስራ በርካታ ድጋፎች እያደረገ ይገኛል፡፡ እነዚህም የጉራጊኛ ቋንቋ ልማት ውጤታማ ለማድረግ ለመምህራን ስልጠና በመስጠት እና በመጽሐፍ ዝግጅት እንዲሁም በተፈጥሮ ሳይንስ ዘርፍ በኮንፒውተር፣ በአርተፊሻል ኢንተሊጀንስና በቤተ-ሙከራ አጠቃቀም ላይ ለተማሪዎች ስልጠና መስጠቱን የተናገሩት አቶ መብራቴ ለዩኒቨርስቲውም ከፍተኛ ምስጋና አቅርበዋል፡፡

ዘንድሮ ለሚሰጠው የማጠናከሪያ ትምህርት የወልቂጤ ዩኒቨርስቲ ለመምህራን ማትጊያ፣ ለነዳጅና ለተለያዩ ወጪዎች የሚሆን 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ማድረጉን ገልጸዋል።

ከዚህ ቀደም የማጠናከሪያ ትምህርት በሚሰጥበት ወቅት የተወሰኑ ተማሪዎች በወቅቱ ተገኝተው የሚሰጠው ትምህርት ያለመከታተል ክፍተት እንደነበረና ዘንድሮ ይህንን ክፍተት ለመቅረፍ ተማሪዎችና የተማሪ ወላጆች የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ሊያደርጉ እንደሚገባ አቶ መብራቴ አሳስበዋል።

የማጠናከሪያ ትምህርቱ የተማሪዎች ውጤት ሊያሻሽል በሚችል መልኩ እንዲሰጥ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት አስፈላጊውን እገዛ ሊያደርጉ እንደሚገባም አክለዋል፡፡

የኦረንቴሽን መድረኩ ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያየት በዞኑ ያጋጠመውን የተማሪዎች ውጤት ስብራት ለመጠገን ልዩ የማጠናከሪያ ትምህርት በዩኒቨርስቲ መምህራን መሰጠቱ ተማሪዎች በዚህ ዓመት ጥሩ ዝግጅት በማድረግ የተሻለ ውጤት ለማምጣት እንደሚያስችላቸው ገልጸው ለውጤታማነቱ ከትምህርት ባለድርሻ አከላት ጋር ተቀናጅተው እንደሚሰሩ ተናግረዋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *