በጉራጌ ዞን ቡታጅራ ከተማ የሚገኘው ጥንታዊና ታሪካዊው የፈትህ መስጊድ ከመንፈሳዊ ፋይዳው በተጨማሪ በህዝቦች መካከል በመቻቻል ላይ የተመሠረተ አንድነት እንዲጎለብትና ወጣቱ በመልካም ስነምግባር እንዲታነፅ ትልቅ አስተዋፅኦ እያበረከተ እንደሚገኝ የእምነቱ አባቶች ተናገሩ።

በመስጊዱ የሚገኙ በጎ እሴቶችን በማጎልበት በውስጡ ያሉ ቅርሶች ለትውልድ ተሻጋሪ እንዲሆኑ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግም የዞኑ ባህልና ቱሪዝም መምሪያ አስታውቋል።

በቡታጅራ ከተማ የሚገኘው ጥንታዊና ታሪካዊው የፈትህ መስጊድ በሼህ ኢሳ ሼህ ሀምዛ አል ቃጥባሪይ እንደመሰረተ ይነገራል።

በመስጊዱ ዙሪያ ማብራሪያ እንዲሰጡን ካነጋገርናቸው የእምነቱ አባቶች መካከል ሀጂ አማን ኬራጎና አቶ ነሥሩ በያን ይገኙበታል።

መስጊዱ ከመንፈሳዊ ፋይዳው በተጨማሪ በህዝቦች መካከል በመቻቻል ላይ የተመሠረተ አንድነት እንዲጎለብትና በተለይም ወጣቱ በመልካም ስነምግባር እንዲታነፅ ትልቅ አስተዋፅኦ እያበረከተ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

ምእመናን ከሌሎች ሀይማኖት ተከታዮች ጋር በመቻቻል ላይ የተመሠረተ አንድነት እንዲኖራቸው መስጊዱ የድርሻውን እየተወጣ እንደሚገኝም አስተያየት ሰጪዎቹ አስረድተዋል።

መስጊዱ በውስጡ የሚገኙ ቅርሶች ተጠብቀው እንዲቆዩና ትውልዱን በዕውቀትና በመልካም ስነ ምግባር በማነፅ እንዲሁም ለቱሪስት ሳቢ በመሆን የድርሻውን መወጣት እንዲችል አሁን ላይ በመስጊዱ ውስጥ የሚገኙ ቅርሶች በመንከባከብ ለቀጣይ ትውልድ ለማስተላለፍ እንዲሁም ወጣቶችን ለማስተማር የሚያስችሉ የሙዚየምና የመማሪያ ክፍሎች ግንባታ ለማከናወን እንቅስቃሴ መጀመሩን የመስጊዱ ኮሚቴ ፀሀፊ አቶ ሳዱዲን መሀመድ ገልጸዋል።

የቡታጅራ ከተማ ባህልና ቱሪዝም ጽህፈት ቤት ሀላፊ ተወካይ አቶ ሠመሩ ስርዋጃ እንደተናገሩት መስጊዱ ጥንታዊና ታሪካዊ መሆኑን ተከትሎ ለከተማውና ለአካባቢው ማህበረሰብ ዘርፈ ብዙ ሀይማኖታዊና ማህበራዊ አገልግሎት እያበረከተ ይገኛል።

ወጣቶች በመልካም ስነምግባር እንዲታነጹ እና የሰላም እሴት እንዲጎለብት በማድረግ ረገድ አይነተኛ ሚና እየተጫወተ እንደሚገኝ ነው ያመላከቱት።

አሁን ላይ በመስጊዱ ውስጥ የሚገኙ የተለያዩ ቅርሶች ለትውልድ ተሻጋሪ እንዲሆኑ ከተማ አስተዳደሩ ድጋፍና ክትትል እያደረገ እንደሚገኝ ነው አቶ ሠመሩ የተናገሩት። ለዚሁ ተግባር ስኬታማነትም ሁሉም ባለድርሻ አካላት የድርሻቸውን ሊወጡ እንደሚገባ አቶ ሰመሩ ጥሪ አቅርበዋል።

የጉራጌ ዞን ባህልና ቱሪዝም መምሪያ ሀላፊ አቶ ተመስገን ገብረመድህን እንደገለፁት የፈትህ መስጊድ በዞኑ ከሚገኙ እድሜ ጠገብ መንፈሳዊ ስፍራዎች አንዱ መሆኑን በማንሳት በተለይም ወጣቶችን በመልካም ስነምግባር ከማነጽ በዘለለ ሀይማኖታዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳው የጎላ ነው።

ከዚህ ጎን ለጎንም በሀይማኖቶች መካከል በመቻቻልና በመደጋገፍ ላይ የተመሠረተ አንድነትና ሰላም እንዲሰፍን መስጊዱ ፋና ወጊ ተግባራት በማከናወን ላይ ይገኛልም ነው ያሉት።

በመስጊዱ ቅጽር ግቢ ችግኝ በየጊዜው እንደሚተከል ተናግረው ይህም ግቢው ነፋሻማ እንዲሆን እድል ከመፍጠሩም ባሻገር የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም እየተደረገ ላለው ጥረት ትልቅ አስተዋጽኦ እያበረከተ እንደሚገኝ አቶ ተመስገን አስረድተዋል።

በመስጊዱ ውስጥ የሚገኙ የተለያዩ ቅርሶች በማልማትና በማስተዋወቅ ለትውልድ ተሻጋሪ እንዲሆኑ በሚደረገው እንቅስቃሴ መምሪያው የድርሻውን እንደሚወጣ የሚናገሩት ሀላፊው ቅርሶቹን ለማልማትና ለማስተዋወቅ እየተደረገ ባለው ጥረት ሁሉም ባለድርሻ አካላት ድጋፍ ሊያደርጉ እንደሚገባ ማሳሰባቸው ከወልቂጤ ኤፍኤም ሬድዮ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *