በጉራጌ ዞን በ2015 ዓ.ም በበጋ ወራት የበጎ ፍቃድ አገልግሎት የተሰሩ ቤቶች ለተጠቃሚዎች የቁልፍ እርክክብና የአዲስ ቤት ግንባታ ማስጀመሪያ ፕሮግራም ተካሄደ።


የዞኑ ህብረተሰብ የመቻቻልና የመደጋገፍ ባህሉ አጠናክሮ በማስቀጠል በየአካባቢው ያሉ አቅመ ደካማ ወገኖች ሊረዱ እንደሚገባ የጉራጌ ዞን አስተዳደር አስታወቀ።

በ2015 ዓ.ም በአረቅጥ እና በቆሼ ከተሞች በበጋ ወራት የበጎ ፍቃድ አገልግሎት የተሰሩ ቤቶች የቁልፍ እርክክብ የተደረገ ሲሆን በእንሴኖ ከተማ ደግም አዲስ ቤት ለመስራት የቤት ፈረሳ ተካሂዷል።

የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ላጫ ጋሩማ በዚህ ወቅት እንዳሉት ምንም እንኳን ሀገራችን ድሀ ብትሆንም ሀብታም እና ድሀ ህዝቦቿ ግን በአብሮነት፣ በመቻቻልና በመደጋገፍ መኖር የሚችሉ አኩሪ ባህል ያላቸው ናቸው።

በመሆኑም ህብረተሰቡ ይህንን የመቻቻልና የመደጋገፍ ባህሉ አጠናክሮ በማስቀጠል በየአካባቢው ያሉ አቅመ ደካማ ወገኖች ሊረዱ እንደሚገባ አቶ ላጫ ጋሩማ አሳስበዋል።

የበጎ አድራጎት ስራ እንደ ሀገርም መንግስት አምኖበት በትኩረት የሚሰራት ዘርፍ ሲሆን በተለይም ወጣቶች ጉልበታቸውና እውቀታቸው ተጠቅመው የበለጠ ሊሰሩበት ይገባል ያሉ ሲሆን የዞኑ መንግስትም አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ተናግረዋል ።

የጉራጌ ዞን ወጣቶችና ስፖርት መምሪያ ኃላፊ አቶ አወል ጅሟቶ እንደተናገሩት በ2015 ዓ.ም በበጋ ወራት በጎ ፍቃድ አገልግሎት የዞኑ፣ የወረዳ መንግስትና የከተማ አስተዳደሮች ፣ባለሀብት፣ በጎ አድራጊ ድርጅቶች፣ የዞኑ ቀይ መስቀል፣ ወጣቶችና የህብረተሰብ ክፍሎች በማስተባበር 4 መቶ 29 ቤቶች በአዲስና በጥገና መልኩ መሰራታቸው ገልጸዋል።

አክለውም የበጎ አድራጎት ተግባር በዞኑ ማህበረብ ባህል የነበረ ቢሆንም ይህን ተግባር ተጠናክሮ እየተሰራ በመሆኑ የብዙዎች ህይወት እየቀየረ ይገኛል ብለዋል።

በመሆኑም ሁሉም ማህበረሰብ ቤቱ ውስጥ ካለው ልብስ ጀምሮ አቅሙ በፈቀደው ልክ የተቸገሩ ወገኖች መርዳት እንደሚያስፈልግ የተናገሩት አቶ አወል ለዚህ ስራ አስተዋጽኦ ላደረጉ አካላት ሁሉ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

የጉራጌ ዞን ወጣቶችና ስፖርት መምሪያ ምክትል ኃላፊና የወጣት ዘርፍ አስተባባሪ አቶ አብዶ ድንቁ በበኩላቸው በዞኑ በማህበረሰቡ ውስጥ ደጋፊና ጠዋሪ የሌላቸው ወጎኖች በመኖራቸው በክረምትና በበጋ ወራት በተለያዩ አገልግሎቶች ሲረዱ እንደነበር አስታውሰዋል።

ከዚህ በፊት ክረምት በዝናብ በጋ በጸሀይና በውርጭ እየተሰቃዩ የነበሩ ግለሰቦች ቤታቸው ፈርሶ እንደነበር የገለጹት አቶ አብዶ በእለቱም በጉመር ወረዳ 4መቶ ሺህ ብር ፤በቆሼ ከተማ 4መቶ 30 ሺህ ብር በአጠቃላይ ስምንት መቶ 30 ሺህ ብር የጨረሱ ሙሉ የቤት ቁሳቁስ የተሟላላቸው ቤቶች የቁልፍ እርክክብ ማድረግ መቻሉ አብራርተዋል።

በእለቱም በእንሴኖ ከተማ አስተዳደር የ1 አቅመ ደካማ ቤተሰብ ቤት በአዲስ ለመስራት ቤቱን የማፍረስ ስራ የተሰራ ሲሆን በበጋና በክረምት ወራት የሚሰሩ የበጎ አድራጎት ስራዎች ሌሎችም በማስተባበር ተጠናክሮ ይቀጥላል ነው ያሉት።

የአረቅጥ ከተማ ከንቲባ አቶ መንግስቱ ሹሜ ይህን የበጎ አድራጎት ተግባር በፈጣሪም ዘንድ ተወዳጅነት ያለው ስራ መሆኑን ጠቅሰው በከተማው መሰል አይነት ችግር ያለባቸው የ2 ሰዎች ቤት የተጀመሩ ሲሆን በአጭር ጊዜ ተሰርቶ አቅም ለሌላቸው ሰዎች እንደሚሰጥ አስገንዘበዋል።

የማረቆ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ንጉሴ መኬ በበኩላቸው በወረዳው በበጋ ወራት የበጎ ፍቃድ ተግባር ከሚመለከታቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር 6 ቤቶች ተሰርተው መጠናቃቸው አስታውቀው ይህንን ላደረጉ አካላትም ምስጋናቸው አቅርበዋል።

የጉራጌ ዞን ቀይ መስቀል ጽ/ቤት ስራ አስከያጅ አቶ ሙሴ በቀለ እንዳሉት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመቀናጀት የግንባታው ስራ በበላይነት በመከታተልና አስፈላጊ ቁሳቁሶችም ድጋፍ እንደሚያደርጉ ተናግሯል።

ወይዘሮ ሰውዳት አህመድ የአረቅጥ ከተማ ነዋሪ ሲሆኑ ወይዘሮ አበራሽ ጦሚሶ የቆሼ ከተማ ነዋሪ ናቸው። መኖሪያ ቤታቸው በበጋ ወራት የበጎ ፍቃድ አገልግሎት በአዲስ መልክ ተገንብቶ ቁልፍ ተረክበዋል።

ተጠቃሚዎቹ እንደተናገሩት ቤተሰብ የታመመባቸውና ልጆቻቸው በሞት ያጡ በመሆናቸው በአካባቢው ማህበረሠሰብ ድጋፍ እንደሚኖሩ አስታውቀዋል ።
ከዚህ በፊት ክረምት በዝናብ በጋ በጸሀይና በውርጭ ሲደርስበቸው የነበረ መከራ ከባድ እንደነበር አስታውሰው በዛሬው እለት ግን ይህን ችግራቸው ተቀርፎ ቤታቸው ተሰርቶ ቁልፍ በመረከባቸው ከፍተኛ ደስታ እንደተሰማቸው ገልጸዋል።

በመድረኩም የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ላጫ ጋሩማ ጨምሮ የዞኑ አመራሮች፣የወረዳዎችና የከተማ አስተዳደር ኃላፊዎች፣የበጎ አድራጊ ወጣቶች ሚመለከታቸው አካላት እየተሳተፊ ሆነዋል ሲል የዘገበው የጉራጌ ዞን የመንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ነው።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *