በጉራጌ ዞን በ2014 ዓ.ም በስምንተኛ እና በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መግቢያ ፈተና ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገቡ ተማሪዎች እውቅናና ሽልማት ተበረከተላቸው።

የተማሪዎች ውጤትና ስነምግባር በማሻሻል ብቁ ተወዳዳሪና በራሱ የሚተማመን ትውልድ ለመፍጠር ባለድርሻ አካላት ተቀናጅተው መስራት እንደሚጠበቅባቸው ተገለጸ።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አረጋ በእውቅናና ሽልማት መርሃግብር ላይ ባስተላለፉት መልዕክት በ2014 የትምህርት ዘመን በሀገር አቀፍ ፈተና ከፍተኛ ውጤት ላስመዘገቡ ተማሪዎች የተዘጋጀው መርሀግብር የቀጣይ ራዕያቸውን ለማሳካት መነሳሳትን ይፈጥርላቸዋል ብለዋል።

ዞኑ ለማሳደግ የተማረ፣ ብቁና ተወዳዳሪ የሰው ሀይል እንደሚያስፈልግ የገለጹት አምባሳደር ምስጋኑ አሁናዊ የዞኑ የትምህርት ጥራት ጉድለት አሳሳቢ በመሆኑ መምህራን፣ አመራሮች፣ ባለሀብቶች፣ ወላጆችና አጋር ድርጅቶች ተቀናጅተው መስራት እንደሚጠበቅባቸው አስረድተዋል።

አያይዘውም ሚኒስቴር ዴኤታው መምህራን ከፖለቲካ፣ ከዘርና ከሀይማኖት ነጻ ሆነው ትውልድ በእውቀት የመገንባት ኃላፊነታቸው መወጣት አለባቸው ብለዋል።

የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ላጫ ጋሩማ እንደገለፁት የዞኑ ማህበረሰብ የትምህርት ተቋማት በመገንባት ረገድ እያደረገ ያለው ተሳትፎ ከፍተኛ ቢሆንም ትምህርት ቤቶቹ በቁሳቁስ አለመሟላታቸው የትምህርት ጥራት ላይ የሚፈለገውን ውጤት ማስመዝገብ አለመቻሉን ገልጸዋል።

በዞኑ ለሀገር አቀፍ ፈተና ከተቀመጡ 12 ሺህ 964 ተማሪዎች 50 እና ከ50 በመቶ በላይ ውጤት ያስመዘገቡ ተማሪዎች ቁጥር 560 ብቻ በመሆኑ የተማሪዎች ውጤትና ስነምግባር ለማሻሻል በትኩረት መስራት እንደሚገባ አቶ ላጫ አስገንዝበዋል።

የቅድመ መደበኛ ትምህርት መጠናከር ለትምህርት ጥራት መሻሻል ያለው ፋይዳ ከፍተኛ በመሆኑ በሁሉም ቀበሌዎች የተገነቡ የቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤቶች ማጠናከር ይገባል ብለዋል።

አያይዘውም አቶ ላጫ ህጻናት በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው እንዲማሩ ጉራጊኛ ቋንቋ በስርዓተ ትምህርት አካቶ ማስተማር እንደሚገባ ገልጸዋል።

የጉራጌ ዞን ትምህርት መምሪያ ኃላፊ አቶ አስከብር ወልዴ የ2014 ሀገር አቀፍ ፈተና ለመፈተን ከተቀመጡ ተማሪዎች 4 ነጥብ 8 የሚሆኑት የከፍተኛ የትምህርት ተቋማት መግቢያ ውጤት ያስመዘገቡ ቢሆንም በዞኑ ሁለት ወረዳዎች አንድም ተማሪ ያላሳለፉ በመሆናቸው ትኩረት ሊሰጡ ይገባል ብለዋል።

በዞኑ የሚስተዋለው የትምህርት ስብራት ለመጠገን ብቃት ያላቸው መምህራን መቅጠር የማይተካ ሚና እንዳለው የተናገሩት ኃላፊው መምሪያው ፈተና በማዘጋጀት ብቁ የሆኑ መምህራን እየቀጠረ እንደሚገኝ አስረድተዋል።

የመርሀግብሩ ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያየት በትምህርት ዘርፍ የሚስተዋለው የትምህርት ስብራት ለመጠገን ያላሳለሰ ጥረት እንደሚያደርጉ ገልጸዋል።

ባለፉት አመታት በትምህርት ሽፋን ላይ የተሰራው ስራ ወደ ውጤት በመለወጥ በትምህርት ቤቶች ተቀራራቢ ውጤት እንዲመዘገብ መስራት ይገባል ብለዋል።

የመምህራን እጥረት በትምህርት ጥራት ላይ የሚያሳድረው ተጽዕኖ ከፍተኛ በመሆኑ በዞኑ የመምህራን ማሰልጠኛ ኮሌጅ መገንባት ያስፈልጋል ብለዋል።

በእውቅናና ሽልማት መርሀግብሩ በ2014 በተፈጥሮ ሳይንስ ከ500 በላይ በማህበራዊ ሳይንስ ደግሞ ከ400 በላይ ውጤት ያስመዘገቡ 40 ተማሪዎች እና በ8ኛ ክፍል ከ90 በመቶ በላይ ውጤት ያስመዘገቡ ተማሪዎች እውቅናና ሽልማት ተበርክቶላአዋል።

በ2014 አገር አቀፍ ፈተና የላቀ ውጤት ያስመዘገቡ ተማሪዎች ለእያንዳንዳቸው ላፕቶ ኮምፒውተር ፣ 13 ሺህ ብርና ሰርተፊኬት ተበርክቶላቸዋል።

ለሽልማቱ የወልቂጤ ዩኒቨርስቲ 800 ሺህ ብር፣ ምስጋኑ የበጎ አድራጎት ፋወረንዴሽን 540 ሺህ ብር እና የጉራጌ ልማትና ባህል ማህበር 120 ሺህ ብር ግምት ያላቸው የላፕቶፕ ኮምፒውተር፣ ዘመናዊ ተንቀሳቃሽ ስልክ፣ ቦርሳ አበርክተዋል።

በተጨማሪ ንብ ኢንተርናሽናል ባንክ በጉራጌ ዞን በ2014 ዓ/ም የትምህርት ዘመን በአገር አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ውጤት ላስመዘገቡ አርባ ተማሪዎች አራት መቶ ሺህ ብር በመመደብ ለእያንዳንዳቸው አስር ሺህ ብር ድጋፍ አድርጓል፡፡

ባንኩ ከዞኑ ጋር ተቀራርቦ የሚሰራ ሲሆን በተለያዩ ጊዜያት ለባንኩ ለሚቀርቡ የድጋፍ ጥያቄዎች አዎንታዊ ምላሽ እየሰጠ ሲሆን በየዓመቱ የሚካሄደውን የጉራጌ ባህልና ልማት አረንጓዴ ዘመቻ ድጋፍ እያደረገ ጥገኛል፡፡

ንብ ባንክ የደንበኞች ፍላጎትና ምርጫ ሊያሳደጉ የሚችሉ የተለያዩ ንብ ማር፣ንብ ማህበራዊ ፣ንብ ልገሳ እና ንብ የስራ ፈጣሪዎች የቁጠባ ሂሳብ አይነቶች ለደንበኞች ማቅረቡ ተጠቁሟል።

ተማሪዎች በብዛት ያሳለፉ ትምህርት ቤቶችና ትምህርት ጽህፈት ቤቶች የኮምፒውተርና የስማርት ቴሌቪዥን ሽልማት ተበርክቶላቸዋል ሲል የዘገበው የጉራጌ ዞን የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ዘግቧል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *