በመንግስት ተቋማት ፣ በባለሀብት ፣ በወጣቶችና በማህበረሰቡ ንቁ ተሳትፎ 267 አዲስ ቤቶችን የመገንባትና 247 ቤቶች የማደስ ስራ መሰራቱም የጉራጌ ዞን ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ መምሪያ አስታወቀ።
የደቡብ ክልል ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ኦንጋይ ኦዳ በርክብክቡ ተገኝተዉ ንግግር ባደረጉበት ወቅት እንዳሉት የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሴክተር ባለፉት የለዉጥ ዓመታት የማህበራዊ ጥበቃ ፖሊሲን መነሻ ባደረገ መልኩ መደበኛና መደበኛ ባልሆነ መንገድ ድህነትን ፣ የዜጎችን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ስጋትና ተጋላጭነትን እና መገለልን ለመቀነስ የሚያስችል እርምጃ በመዉሰድ ለሁሉም ተደራሽ ለማድረግ መጠነ ሰፊ ተግባራትን ሲያከናዉን ቆይቷል።
በዞኖችና በልዩ ወረዳ መዋቅሮች በማህበራዊ ድጋፍ በኩል ተጋላጭ ለሆኑ አረጋዉያን እና አካል ጉዳተኞች መኖሪያ ቤቶች በመጠገን ፣አዲስ ቤቶችን በመገንባት እንዲሁም የተለያዩ የአልባሳት ፣የትምህርት ቤት ዩኒፎርምና የትምህርት መረጃ ቁሳቁስ ድጋፍ ለተቸገሩ ህጻናት ድጋፍ ተደርጓል ብለዋል።
የክልሉ ሰራተኛና ማህበራዊ ቢሮ በ2013 ዓመተ ምህረት በክረምት ወቅት በወልቂጤ ከተማ የአንድ አረጋዉያን ቤት ያስገነባ ሲሆን በዚህም ለግንባታና ለቤት ዉስጥ ቁሳቁስ ለማሟላት 2 መቶ 50 ሺህ ብር ወጪ ማድጋቸውን አብራርተዋል።
የጉራጌ ዞን ረዳት የመንግስት ተጠሪ አቶ አለማየሁ ገብረመስቀል እንዳሉት የደቡብ ክልል ሰራተኛ ቢሮ አጠቃላይ የማኔጅመንት አባላት በወልቂጤ ከተማ አቅመ ደካማ አረጋውያንን መሰረት በማድረግ ደረጃዉን የጠበቀ ቤት በመስራታቸዉና በማስረከባቸው ልባዊ ምስጋና አቅርበዋል።
በጉራጌ ዞን በክረምት በጎ ፍቃድ አገልግሎት በርካታ ስራዎች ተሰርተዋል ያሉት አቶ አለማየሁ በክልሉ ሶስት ቢሮዎች ማለትም የደቡብ ክልል ሰራተኛ ቢሮ በወልቂጤ ከተማ ፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ቡታጅራ ላይ እንዲሁም የዲዛይንና ቁጥጥር ቢሮ በእምድብር ከተማ አዲስ የአረጋዉያን ቤት መስራት መቻላቸዉም ጠቁመዋል።
በጉራጌ ማህበረሰብ ዘንድ መረዳዳትና መደጋጋፍ ቆየት ያለ ባህል መሆኑንና አሁንም ተደጋግፎ የአንዱን ጉድለት አንዱ እየሞላ አብሮ የሚያድግ ማህበረሰብ እንደሆነም አስታዉቀዋል።
የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ስራ በክረምት ብቻ ሳይሆን በበጋ ወራትም የበለጠ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ተናግረዋል።
በርክክቡ የተገኙት የወልቂጤ ከተማ ከንቲባ አቶ እንዳለ ገብረመስቀል በበኩላቸዉ በከተማዉ በክረምት በጎ ፍቃድ ተግባር ረዳት የሌላቸዉ እናት ወይዘሮ አሽረቃ አብድላ ያማረና የተዋበ ቤት የክልሉ ሰራተኛና ማህበራዊ ቢሮ ሰርቶ በማስረከቡ ከፍተኛ ምስጋና አቅርበዋል።
የክልሉ ሰራተኛና ማህበራዊ ቢሮ ከአንድ ወር በላይ ወልቂጤ ከተማ ላይ በመቀመጥ በአረንጓዴ ልማት ስራ ፣ በጽዳትና ዉበት ስራ እንዲሁም ረጂ የሌላቸዉ አረጋዉያን በከተማዉ ቤት ለቤት በመዞር የተለያዩ ቁሳቁሶችን ድጋፍ ሲያደርግ የነበረበት ሁኔታዎች መኖራቸዉም ተናግረዋል
በእለቱ የተገኙት የጉራጌ ዞን ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳዮች መምሪያ ኃላፊ ወይዘሮ አመተረዉፍ ሁሴን እንዳሉት በዞኑ ከ90 ሺህ በላይ የሚሆኑ አረጋዉያን የሚገኙ ሲሆን ከነዚህም ዉስጥ ለተለያዩ ለኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ችግር የተጋለጡ 35 ሺህ የሚጠጉ እንደሆነም አመላክተዋል።
እነዚህ ወገኖች ሁሉ አቀፍ ማህበራዊ ጥበቃ እንዲያገኙ በትኩረት እየተሰራ እንደሆነም ጠቁመዉ አረጋዉያንም የጤና መድህን ተጠቃሚ እንዲሆኑ ተደርጎዋል ብለዋል።
ጧሪና ደጋፊ ለሌላቸዉ አረጋዉያን በ2013 ዓመተ ምህረት በክረምት በጎ ፍቃድ አገልግሎት በመንግስት ተቋማት ፣ በባለሀብት ፣ በወጣቶችና በማህበረሰቡ ተሳትፎ 267 አዲስ ቤቶችን የመገንባትና 247 ቤቶች የማደስ ስራ መሰራቱም ያስታወሱት ኃላፊዋ የተለያዩ አልባሳትና የቤት ቁሳቁሶችን መደገፍ እንደተቻለም አመላክተዋል።
አዲስ ቤት የተሰራላቸዉ አረጋዊ ወይዘሮ አሽረቃ አብድላ እንዳሉት ቤቱ ቀደም ሲል በላያቸዉ ላይ ሊፈርስ የደረሰ እንደነበረ እንዲሁም ብርድና ዝናብ ይመታቸዉ እንደነበረም አስታዉሰዉ የክልሉ ሰራተኛና ማህበራዊ ቢሮ ያረጀው ቤታቸው አፍርሶ በአዲስ መልክ በጥሩ ሁኔታ ሰርቶ የቁልፍ ርክክብ በማድረጉ እጅግ ደስተኛ እንደሆኑ ተናግረዋል።
በዚህ በስራው ለተሳተፉ አካላት በሙሉ ከፍተኛ ምስጋናም አቅርበዋል ሲል የዘገበዉ የጉራጌ ዞን የመንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ነዉ።
በተጨማሪም እነዚህ ሊንኮችን በመጫን ወቅታዊና ትኩስ መረጃዎቻችንን እንድትከታተሉ እንጋብዛለን፡፡
Facebook:- https://www.facebook.com/gurage1Zone
Website:- https://gurage.gov.et
Telegram:- https://t.me/comminuca
Youtub: -https://www.youtube.com/channel/UCzrcazGvvIO2tG7bQN36Cx