በጉራጌ ዞን በወልቂጤ፣ በቀቤናና በገደባኖ ጉታዘር ወለኔ ወረዳዎች ለሚገኙ ለእግር ኳስ ክለቦች፣ ለአትሌቲክስ ፣ ለወርልድ ቴኳንዶ ክለብ ፣ለብስክሌት፣ ለጠረጴዛ ቴኒስ እና ለፓራሊምክስ ፕሮጀክቶች የደቡብ ክልል ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ የስፖርት ቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ።

የደቡብ ክልል ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ተስፋዬ ብላቱ ለታዳጊ ፕሮጀክቶች የስፖርት ቁሳቁስ ድጋፍ ባደረጉበት ወቅት እንዳሉት መንግስት የተለያዩ የልማት ስራዎች እያከናወነ እንደሆነና የታዳጊ ወጣት ፕሮጀክቶች ላይ በትኩረት እየሰራ እንደሚገኝ አመላክተዋል።

ከታች ጀምሮ የታዳጊ ወጣት ፕሮጀክቶች ላይ ትኩረት ተደርጎ እየተሰራ እንደሆነም ተናግረዉ በክልሉ ተተኪ ስፖርተኞች ለማፍራት በሁሉም አካባቢዎች ሁሉንም የስፖርት አይነቶች ባካተተ መንገድ ፕሮጀክቶች ላይ ስራ እየተሰራ ነዉ ብለዋል።

በክልሉ በስፖርቱ ዘርፍ የሚፈልገዉን ዉጤት እንዲመጣና ለሀገሪቱም ተተኪ ስፖርተኞች ለማፍራት በ11 የተለያዩ የስፖርት አይነቶች ከ2 ሺህ 5 መቶ በላይ ታዳጊ ስፖርተኞች ስልጠና እየወሰዱ እንደሆነም አመላክተዋል።

በክልሉ በስፖርቱ ዘርፍ ትልቅ አቅም እንዳለና ታዳጊ ህጻናት ከስር እየኮተኮቱ በማሳደግና ታዳጊዎች በተገቢዉ ስልጠና አግኝተዉ ከመደበኛ ትምህርታቸዉ ጎን ለጎን በተለያዩ የስፖርት አይነቶች እንደየፍላጎታቸዉ በክለብ ታቅፈዉ በጥሩ አሰልጣኝ እንዲሰለጥኑ በማድረግ በሁሉም የስፖርት ዘርፍ ተተኪ ማፍራት እንደሚገባም አስረድተዋል።

ለታዳጊ ስፖርተኞች የስፖርት ቁሳቁስ የማሟላት ስራ መጀመሩም የተናገሩት አቶ ተስፋዬ ብላቱ በዚህ ዙር ብቻ ለ11 የተለያዩ ፕሮጀክቶች ከ250 በላይ ለሆኑ ታዳጊ ስፖርተኞችና ለአሰልጣኞች የቱታ እንዲሁም ለስልጠና የሚሆናቸዉ የስፖርት ቁሳቁስና ትጥቅ ድጋፍ እያደረጉ እንደሆነም ጠቅሰዋል።

የጉራጌ ዞን ወጣቶችና ስፖርት መምሪያ የስፓርት ትምህርት ስልጠና ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ወይዘሮ ዝናሽ በለጠ እንዳሉት በዞኑ በተለያዩ ወረዳዎችና ከተማ መስተዳደሮች የታዳጊ ፕሮጀክቶች ላይ ጥሩ የሚባል ስራዎች እየተሰሩ እንደነበረም አስረድተዋል።

የታዳጊ ስፖርት ፕሮጀክት ስልጠና በፊት የነበረዉ አሰራር ሳይንሳዊ አይደለም በሚል ከፌዴራል ጀምሮ እስከ ቀበሌ ድረስ በአዲስ መልክ ክልሉ ባዋቀረዉ መሰረት በዞኑ በ7 የስፖርት አይነቶች 13 ፕሮጀክቶች ለማሰልጠን የተሰጣቸዉ መሆኑም ተናግረዋል።

ዞኑ ለስፖርቱ ያለዉን አቅም በማየት የተጀመረዉን ስራ የታዳጊ ፕሮጀክቶች ስፖርት እያስቀጠሉ እንደሆነም አመላክታለች።

በአንድ የታዳጊ ፕሮጀክት 25 ልጆችን በመያዝ ስልጠና የሚሰጥ እንደሆነና ታዳጊዎች ስልጠና ጀምረዉ ለልምምድ የሚሆናቸዉ ቁሳቁስ መዘግየት እንደተግዳሮት ሲታይ መቆየቱን አንስተዋል።

ከፕሮጀክቶች የሚፈለገዉ ዉጤት እንዲመጣ አሰልጠኞች በስልጠና እንዲታገዙ ማድረግ ፣ ክልሉ ድጋፍ ላደገረገዉ የስፖርት ቁሳቁስ አመስግነዉ በፓራሊምክ ስፖርት የተደረገላቸዉ ማሊያና ቁምጣ ለልምምድ ምቹ ባለመሆኑ ሙሉ ቱታ ሊቀየርላቸው እንደሚገባ ተናግረዋል።

ፌዴራል አንደኛ ደረጃ ዳኛ እና አሰልጣኝ ሳቦም ሀዲሙ አክመል እና የታዳጊ የብስክሌት ስፖርት አሰልጣኝ ሰብር ረሻድ እንዳሉት ለታዳጊዎች በተገቢዉ ስልጠና እየሰጡ እንደሆነም አስረድተዋል።

ክልሉ ድጋፍ ያደረገላቸዉ የስፖርት ትጥቅ ከሚያሰሩት የስፖርት አይነት ጋር የሚጣጣም እንዳልሆነም ጠቅሰዉ ለተደረገላቸዉም ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።

አንዳንድ ታዳጊ ስፖርተኞች በሰጡት አስተያየት ድጋፉ የተሟላ ባይሆንም ደስ ብሎናል ለወደፊቱ ስፖርቱን ወደን እንድንሰራና ጠንክረን ሰርተን የሃገራችንን ስም በከፍታ ቦታ ለማስጠራት ያበረታታናል ሲሉ ተናግረዋል ሲል የዘገበዉ የጉራጌ ዞን የመንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ነዉ።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *