በጉራጌ ዞን በአዲሱ ስርዓተ ትምህርት ላይ ለመምህራን ለሱፐርቫይዘሮችና ለትምህርት ባለሙያዎች ሲሰጥ የነበረው ስልጠና ተጠናቀቀ።

ጥቅምት 01/2015

በጉራጌ ዞን በአዲሱ ስርዓተ ትምህርት ላይ ለመምህራን ለሱፐርቫይዘሮችና ለትምህርት ባለሙያዎች ሲሰጥ የነበረው ስልጠና ተጠናቀቀ።

አዲሱ ፍኖተ ካርታ ዘመኑን የሚመጥን የሰው ሀይል ለማፍራት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት መምህራን ገለጹ።

ይህን የገለጹት መምህራን፣ ሱፐርቫይዘሮችና የትምህርት ባለሞያዎች በአዲሱ የትምህርት ፍኖተ ካርታ ስልጠና በተሳተፉበት ወቅት ነው።

በስልጠናው ከ9ሺህ በላይ የሚሆኑ መምህራን፣ ሱፐርቫይዘሮችና የትምህርት ባለሙያዎች ተሳትፈዋል።
በዞኑ ትምህርት መምሪያ የመምህራን እና ትምህርት አመራር ልማት ቡድን መሪ አቶ ባቂ በሰማ ባለፈው የትምህርት ዘመን በ13 ትምህርት ቤቶች በሙከራ ደረጃ ሲተገበር የነበረው አዲሱ ስርዓተ ትምህርት በ2015 የትምህርት ዘመን በመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ወደ ሙሉ ትግበራ ተገብቷል ብለዋል።

ስርዓተ ትምህርቱ የታለመለትን አላማ ለማሳካት መምህራን ከአዲሱ ስርዓተ ትምህርት ጋር ማስተዋወቅ ይገባል ያሉት አቶ ባቂ በዞኑ በ14 ማዕከላት 9ሺህ 492 መምህራን፣ ሱፐርቫይዘሮችና የትምህርት ባለሙያዎች በአዲሱ ስርዓተ ትምህርት ትግበራ ስልጠና ላይ እንዲሳተፉ ተደርጓል ብለዋል።

እንደ ቡድን መሪው ገለጻ አዲሱ ፍኖተ ካርታ ቀደምሲል በሀገሪቱ ሲተገበር በነበረው ስርዓተ ትምህርት ላይ ይስተዋሉ የነበሩ ችግሮች የሚፈታና መምህራን የአዲሱ ፍኖተ ካርታ ምንነት በመረዳት ለተማሪዎች ዘመኑን የዋጀ እውቀት ለማስጨበጥእንደሁ የሚያስችል መሆኑን አስረድተዋል ።

በዞኑ ትምህርት መምሪያ የስርዓተ ትምህርት ባለሙያ ወይዘሮ ገነት ደምስስ መምህራኑ ከ1 እስከ 6 እና ከ7 እስከ 8ኛ ክፍል ባሉ ሁለት እርከኖች እንደሚያስተምሩ ገልጸዋል።

ስልጠናው መምህራን በቂ ግንዛቤና እውቀት ይዘው የአዲሱን ስርዓተ ትምህርት ይዘቶች በተሟላ መልኩ ለማስረጽ የሚያግዝ ሲሆን መምህራንን ከመጻህፍት ጋር በማስተዋወቅ በኩል ትልቅ ሚና እንደሚጫወት ባለሞያዋ አስታውቀዋል ።

በዞኑ የሚስተዋለው ግብዓት የመጽሐፍት አቅርቦት እጥረት ለመቅረፍ ከ1ኛ እስከ 8ኛ ክፍሎች የመማሪያና ማስተማሪያ መጽሃፍት በሶፍት ኮፒ ለሁሉም ትምህርት ቤቶች ተደራሽ ማድረግ ተችሏል።
ይሁን እንጂ ትምህርት ቤቶች መጽሀፍቱ በወረቀት አባዝቶ የማሰራጨት አቅም ባይኖራቸውም ባለሀብቶችን በማስተባበር መጽሐፍቱ ለማሳተም የተጀመሩ ጥረቶች ማጠናከር እንዳለባቸው ገልጸዋል።

የመማሪያና ማስተማሪያ መጽሀፍት ህትመት በአጭር ጊዜ ተጠናቆ ለተማሪዎች በፍጥነት ተደራሽ ለማድረግ የክልሉ መንግስት መስራት አለበት ብለዋል።

እንደ አዲስ በተካተቱ የትምህርት አይነቶች ላይ የሚታየውን የመምህራን እጥረት ለማቃለል የአጭር፣ የመካከለኛና የረጅም ጊዜ ስልጠናዎች መስጠት እንደሚገባም ጠቁመዋል።

በጉራጌ ዞን ቸሀ ወረዳ ሲሰለጥኑ ያነጋገርናቸው መምህር ዘመላክ ታገሰ፣ ተኸልቁ አለሙ እና መምህርት ደስታ ደገሙ ፍኖተ ካርታው ዘመኑን የሚመጥን የሰው ሀይል ለማፍራት ያስችላል ብለዋል።

ጥራት ያለው ትምህርት የሀገር መጻዒ እድል ለመወሰንና ሀገር በቀል እውቀቶችን ለማጎልበት የሚያስችል በመሆኑ መምህራን፣ ተማሪዎች፣ ወላጆች፣ መንግስት፣ ባለሀብቶች እና ረጂ ድርጅቶች የሚያደርጉት ተሳትፎ ማጠናከር ይጠበቅባቸዋል ብለዋል ሲል የዘገበው የጉራጌ ዞን የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ነው።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *