በጉራጌ ዞን በተለያዩ ወረዳዎችና ከተማ አስተዳደሮች 1443ኛ የኢድ አልፈጥር በዓል በድምቀት ተከበረ።

ህዝበ ሙስሊሙ 1443ኛው የኢድ አልፈጥር በዓል ሲያከብር የተቸገሩን በመርዳትና የአካባቢውን ሰላም በመጠበቅ መሆን እንዳለበት የጉራጌ ዞን አስተዳደር ገለጸ።

የደቡብ ክልል እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ፕረለዝዳንት ሃጅ አብድልከሪም መህ በድረዲን በኢድ አልፈጥር በዓል ላይ ተገኝተው ባስተላለፉት መልዕክት ህዝበ ሙስሊሙ አንድነቱን በማጠናከር የሀገሪቱ ሰላም ለማደፍረስ የሚንቀሳቀሱ አካላት መከላከል ይጠበቅብናል ብለዋል።

በቅርቡ በጎንደር ግጭት በመቀስቀስ ለእምነት ተቋማት መቃጠልና ለሰው መሞት ምክንያት በሆኑ አካላት አስፈላጊውን እርምጃ እንዲወሰድባቸው የፌደራልና የአማራ ክልል መንግስታት መስራት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።

ጥፋትን በጥፋት በማረም ሰላም ማረጋገጥ እንደማይቻል የተናገሩት ፕሬዝዳንቱ በመካከላችን ያሉ ልዩነቶች በማጥበብ በአጥፊዎች ላይ ሰላማዊ በሆነ መንገድ በመታገል እርምጃ እንዲወሰድባቸው መስራት እንደሚገባ አስረድተዋል።

አክለውም ሼህ አብድልከሪም ሙስሊሙን ማህበረሰብ የሚወክል ጠንካራ እስላማዊ መጅሊስ እንዲመሰረት መንግስት አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደርግ ጠይቀዋል።

የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ መሀመድ ጀማል የዘንድሮ የኢድ አልፈጥር በዓል የሚከበረው በሀገሪቱ በርካታ ዜጎች በኢኮኖሚ ምክንያት የወገኖቻቸውን ድጋፍ በሚሹበት እና ሰላም አጥተው በስጋት ውስጥ በሚገኙበት ወቅት በመሆኑ ህዝበ ሙስሊሙ በዓሉ ሲያከብር በመረዳዳት፣ በመደጋገፍና ለሀገሪቱ ሰላም ለጸሎትና ዱዓ በማድረግ መሆን አለበት ብለዋል።

ህዝበ ሙስሊሙ በታላቁ የረመዳን ወቅት ሲከውናቸው የነበሩ የጸሎት፣ የእዝነትና የይቅር ባይነትና የመደጋገፍ ባህሉን አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚጠበቅበት አስገነዘቡ።

ኢትዮጵያውያን ለዘመናት የገነቡት የአብሮነት፣ የመቻቻልና የመረዳዳት እሴት ተጠብቆ እንዲቆይ በመደረጉ የእምነት ተቋማት በጋራ በመገንባት ማህበራዊ ችግሮቻቸው ተከባብረው እንዲፈቱ አድርጓቸዋል።

በመሆኑም ህዝበ ሙስሊሙ ይህን እሴት ተጠብቆ እንዲቆይ እና ለሰላምና አንድነት የበኩሉን ሚና እንዲጫወት ይጠበቅበታል ብለዋል።

እንደ አቶ መሀመድ ገለፃ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሀገራችን ሰላምና ብልጽግና ለማደናቀፍ የእምነት ካባ ደርበው ከውጭ ጠላቶቻችን ጋር አብረው የሚንቀሳቀሱ አካላት እኩይ ተግባር ለመመከት በአንድነት መቆም ይጠበቅብናል ብለዋል።

በሀገሪቱ በአንዳንድ አካባቢዎች በእምነት ተቋማት የደረሰው ውድመትና በንጹሃንን ላይ የተፈጸመው ግድያ እንዳሳዘናቸው የገለጹት የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ የእስልምናና የክርስትና እምነት ተከታዮች፣ የሀይማኖት አባቶች፣ የሀገር ከሽማግሌዎችና ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች ድርጊቱን ሊያወግዙ ይገባል ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል።

የእምነቱ ተከታዮች በበኩላቸው የዘንድሮ የኢድ አልፈጥር በዓል ሰላማዊ ሆኖ መጠናቀቁ በዓሉ ይበልጥ እንዲደምቅ አድርጎታል ብለዋል።

በሀገሪቱ የወገናቸውን ድጋፍ የሚሹ ወገኖች በመኖራቸው በሀይማኖት፣ በዘርና በብሄር ሳንለያይ የምንደጋገፍበትና የምንረዳዳበት እሴታችን ማጠናከር ይጠበቅብናል ብለዋል።

በተጨማሪም እነዚህ ሊንኮችን በመጫን ወቅታዊና ትኩስ መረጃዎቻችንን እንድትከታተሉ እንጋብዛለን፡፡
Facebook:- https://www.facebook.com/gurage1Zone
Website:- https://gurage.gov.et
Telegram:- https://t.me/comminuca
Youtub: -https://www.youtube.com/channel/UCzrcazGvvIO2tG7bQN

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *