በጉራጌ ዞን በቡኢ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት የቀድሞ ተማሪዎች ህብረት የተገነባው የትምህርት ቤቱ የማስፋፊያ ግንባታ ለትምህርት ጥራት መረጋገጥ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት የደቡብ ክልል ትምህርት ቢሮ አስታወቀ።

መሰከረም 21/2015 ዓ .ም

በጉራጌ ዞን በቡኢ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት የቀድሞ ተማሪዎች ህብረት የተገነባው የትምህርት ቤቱ የማስፋፊያ ግንባታ ለትምህርት ጥራት መረጋገጥ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት የደቡብ ክልል ትምህርት ቢሮ አስታወቀ።

በቡኢ ከተማ አስተዳድር በቀድሞ ተማሪዎችና በአካባቢዉ ማህበረሰብ የተገነቡ የቡኢ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እና በእዣ ወረዳ የቦዠባር ቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የማስፋፊያ ግንባታ የደቡብ ክልል ትምህርት ቢሮ ኃላፊ፣ የዞን ትምህርት መምሪያ ኃላፊ ፣ የከተማዉ ከንቲባ፣ የትምህርት ቢሮ ሀላፊዎችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት በተገኙበት ተጎብኝተዋል።

በጉብኝቱ የተገኙት የደቡብ ክልል ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ዲላሞ ኦቴሬ የቡኢ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የቀድሞ የተማሪዎች ህብረት በትምህርት ቤቱ ያስገነባው የመማሪያ ብሎኮች በክልሉ አሉ ከሚባሉ ትምህርት ቤቶች መካከል እንዲጠቀስ አድርገውታል ።

የቀድሞ ተማሪዎች ህብረት ለትምህርት ቤት ግንባታ ከተጠቀምንበት ትልቅ አቅም እንደሆነም ተናግረዉ የቡኢ ከተማ መስተዳድር የቀድሞ ተማሪዎች ህብረት 60 የመማሪያ ክፍሎች መገንባት ችለዋል ብለዋል።

ለሶስቱም ሳይንሶች ዘመናዊ የሆነ ትልቅ ላብራቶሪዎች ፣ ደረጃዉን የጠበቀ ቤተ መጽሀፍት ፣ ለአስራ አራቱም የትምህርተ አይነት ለእያንዳንዱ የአስተዳድር ህንጻ ተገንብቷል ብለዉ ይህም ለትምህርት ጥራት የሚኖረዉ ፋይዳ ከፍተኛ ነዉ ብለዋል።

ክፍሎቹ ደረጃቸዉን የጠበቁ እንደሆኑም ተናግረዉ የትምህርት ቤቱ ግንባታ ለሀገራችን ትልቅ ተሞክሮ የሚወሰድበት እንደሆነም አስረድተዋል።

የጉራጌ ዞን ትምህርት መምሪያ ኃላፊ አቶ አስከብር ወልዴ እንዳሉት በዞኑ የትምህርት ስራ ከተጀመረበት 1934 ዓ. ም ጀምሮ 628 የአንደኛ ደረጃ ፣89 ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ይገኛሉ።

አብዛኛዉ ትምህርት ቤቶች በህብረተሰብና በባለሀብት ፣ በመንግስና በረጂ ድርጅቶች የተገነቡ ሲሆን በዚህ አመት የተማሪዎች ጥምርታ ለማስተካከል የትምህርት ቤቶች የግንባታ ጥራት ለማሻሻል በረጂ ድርጅቶች ፣በባለሀብቶች እንዲሁም በህብረተሰቡ አማካኝነት በርካታ ትምህርት ቤቶች እየተገነቡ እንደሆነም አስታዉቀዋል።

ከነዚህም መካከል የቡኢ ከተማ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የማስፋፊያ ግንባታ በአይነቱ ለየት የሚል እጅግ በጣም ሰፊ የግንባታ ሂደት የታየበት እንደሆነም ተናግረዋል።

በቀድሞ ተማሪዎች ህብረት እየተገነባ ያለዉ ትምህርት ቤት ግንባታ የትምህርት ጥራት የሚያስጠብቅ ፣በርካታ ቁሳቁሶችም የተሟሉለትም እንደሆነም አንስተዉ በዞኑ መሰል ግንባታዎችም መኖራቸዉም ጠቅሰዉ እነዚህም ትምህርት ቤቶች በአካባቢ ባለሀብቶች ፣የቀድሞ ተማሪዎች ህብረት እንዲሁም ሌሎችም በማስተባበር በርካታ ትምህርት ቤቶች እየተገነቡ እንደሆነም ጠቁመዋል።

የትምህርት ጥራት ለማስጠበቅ ተማሪዎች ከታችኛ ደረጃ በተገቢዉ መማር እንዳለባቸዉ የተናገሩት አቶ አስከብር እነዚህ ተማሪዎች ለማስተማር የትምህርት ቤቶች ግንባታ ወሳኝነት እንዳለዉ አብራርተዉ ከዚህ በፊት የቅድመ አንደኛ ትምህርህ ቤት ግንባታቸዉ ትኩረት እየተሰጣቸዉ እንዳልነበረም ተናግረዋል።

ይህንን ለመቀየር በክረምት ወቅት ንቅናቄ በመፍጠር በዞኑ ከ306 በላይ መማሪያ ክፍሎች የቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ግንባታ መከናወኑም አብራርተዋል።

የቡኢ ከተማ አስተዳድር ከንቲባ አቶ የሽልጌታ በላይነህ እንዳሉት በከተማዉ ዙሪያ የሚገኙ ቀበሌዎች የሚመጡ የአርሶአደር ልጆች በስፋት ተመራጭ አድርገዉ ከተማ ላይ መጥተዉ ይማራሉ።

ባለፉት አመታት የተማሪ የመቀበል አቅማቸዉ እጅግ በጣም ዝቅተኛ እንደነበረ አስታዉሰዉ የተለያዩ ኮሚቴዎች በማደራጀት የትምህርት ጥራት ለማረጋገጥ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ዉጪ እንዳይሆኑ እየተሰራ እንደሆነም አብራርተዋል።

በከተማዉ በቀድሞ ተማሪዎች ህብረት ወደ መጠናቀቅ ምዕራፍ ላይ የደረሰዉ ደረጃዉን የጠበቀ ግንባታ ከፍተኛ የሆነ ሀብት በማሰባሰብ የትምህርት ጥራት በማሻሻልና የትምህርት ተደራሽነት አተኩረዉ እየሰሩ እንደሆነም ጠቁመዋል።

የተማሪዎች የፈራቃ ጊዜ በማስቀረታቸዉ በትምህርት ጥራት ላይ የራሱ የሆነ በጎ ተጽኖ እንደሚኖረዉም ተናግረዉ ከሰአት ቷኋላ መምህራኖች ያስተምሩበት የነበረዉ ጊዜያቸዉ ለተማሪዎች የማጠናከሪያ ትምህርት በመስጠት ተማሪዎች የበለጠ ዉጤታማ እንደሚያደርጋቸዉም ጠቁመዋል።

በዶ/ር ዲላሙ የተመራው ቡድን በእዣ ወረዳ ባሉ ትምህርት ቤቶቾም የተሰሩ ስራዎችን ጎብኝቷል።

በጉብኝቱ ተሳታፊ ከነበሩት የእዣ ወረዳ ትምህርት ጽህፈት ቤት ኃላፊ ተጠምቀ በርጋ በበኩላቸዉ በወረዳቸው ከንቅናቄ መድረክ በኋላ ነዋሪዎች ፣ተወላጆችና በማስተባበር የቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ግንባታ በስታንዳርዱ መሰረት በማድረግ በ3 ቀበሌዎች አራት አራት ክፍል ያላቸዉ ብሎኮች መገንባታቸዉም አስረድተዋል።

በቦዠባር ፣ አገና 01 ቀበሌ እንዲሁም ሳቡላ ቀበሌ ላይ የቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መገንባታቸዉ አስታዉሰዉ በተጨማሪም በዳርቻ ቀበሌ ፣ዝግባ ቦቶ ፣አጓሽተረህ፣ሻመነ ቀበሌዎች ላይ ሁለት ክፍል የነበራቸዉ ወደ አራት ክፍል እንዲሆኑ የማስፋፊያ ግንባታ ማከናወናቸዉም አብራርተዋል ሲል የጉራጌ ዞን መንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ዘግቦታል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *