በጉራጌ ዞን በመስቃንና ማረቆ ማህበረሰብ መካከል የነበረው የሰላም ችግርና ግጭት ተፈቶ እርቀሰላም በመፈጸሙ ከፍተኛ ደስታ እንደተሰማቸው ነዋሪዎቹ ገልጸዋል።

አካባቢያዊና አገራዊ ችግሮችን ለመፍታትና የዜጎች አንድነትና ወንድማማችነት እሴት ለማጎልበት ቱባ የባህል እሴቶቻችን በአግባቡ መጠቀም እንደሚገባ የጉራጌ ዞን አስተዳደር አስታወቀ።

በሀገሪቱ የተፈጠረው ለውጥ ተከትሎ ግጭት ከተከሰተባቸው አካባቢዎች መካከል የመስቃንና ማረቆ ወረዳዎች ተጠቃሽ ናቸው።

በእነዚህ ወረዳዎች ለሶስት አመታት የዘለቀ ግጭትና ሰላም መደፍረስ ተፈጥሮ ከንብረት ውድመት በተጨማሪ የሰው ህይወት ጠፍቷ፤ በሺዎች የሚቆጠሩ ደግሞ ተፈናቅለዋል።

የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ መሀመድ ጀማል በእርቅ ስነስርዓቱ ተገኝተው እንደተናገሩት በእነዚህ ወረዳዎች በተፈጠረው ግጭት የ80 ሰዎች ህይወት ያለፈ ሲሆን ከ7 ሺህ 6መቶ በላይ አባወራዎችና እማወራዎች ተፈናቅለው ነበር።

ይህ ደግሞ በህብረተሰቡ ማህበራዊ ኑሮ ላይ የፈጠረው ጫና ከፍተኛ እንደነበር የተናገሩት አቶ መሀመድ መንግስት ለልማት ይውል የነበረው ሀብት ለጸጥታ እና ህግ ለማስከበር እንዲያውል አድርጎታል ብለዋል።

በመሆኑም ባለፉት 3 አመታት በእነዚህ ወረዳዎች የልማት ስራዎች በተገቢ ባለመከናወናቸው አርሶአደሮችና ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች ለተለያዩ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ለጸጥታ ችግሮች ተጋላጭ እንዲሆኑ አድርጓቸው ነበር ብለዋል።

የክልሉ መንግስት ከዞኑ አስተዳደር እና ከወረዳዎቹ ነዋሪዎች ጋር በመሆን በወረዳዎቹ ሰላምና ፀጥታ ለማስፈን ከፍተኛ ጥረት ማድረጉን አስተዳዳሪው ገልጸዋል።

አካባቢያዊና አገራዊ ችግሮችን በመፍታት የዜጎች አንድነትና ወንድማማችነት እሴት ለማጎልበት ቱባ የባህል እሴቶቻችን መጠቀም እንደሚገባ የገለፁት አቶ መሀመድ በሀገሪቱ የሚፈጠሩ ግጭቶች በጸጥታው ኃይል ብቻ የሚፈቱ ባለመሆናቸው ባህላዊ እሴቶችን ማጠናከር ይገባል ብለዋል።

በነዚህ ወረዳዎች ባለፉት ሶስት አመታት ግጭቱ በተፈጠረባቸው አካባቢዎች የሚኖሩ የህብረተሰብ ክፍሎች በልማትና በመልካም አስተዳደር ስራዎች ተጠቃሚ ለማድረግ ከክልሉ መንግስት ጋር በቅንጅት ይሰራል ብለዋል።

የማረቆ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ንጉሴ መኪ እና የምስራቅ መስቃን ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ አህመዲን ደድገባ በበኩላቸው ያለፉት ሶስት አመታት የሰው ህይወት ያለፈበት፣ ሰው የተፈናቀለበት እና ከፍተኛ ንብረት የወደመበት ጊዜ እንደነበር ገልጸዋል።

በእነዚህ አመታት በግጭቱ የተጎዱ ወገኖች ህይወት ለመታደግ እና ጸጥታን ለማስከበር ከሚሰሩ ስራዎች ውጪ የልማት ስራዎች በተገቢ ባለመሰራታቸው ህብረተሰቡ ይበልጥ እንዲጎዳ አድርጎታል ብለዋል።

የማረቆ እና የመስቃን ወረዳ ነዋሪዎች በእምነት፣ በሀይማኖት፣ በጋብቻና በሌሎች ማህበራዊ መስተጋብሮች የተሳሰሩ ቢሆኑም ገጭቱ ሀገራዊ ለውጡን ለማደናቀፍና የግል ጥቅማቸው ለማስከበር የሚንቀሳቀሱ ግለሰቦች የፈጠሩት እንደነበር አስረድተዋል።

ነዋሪዎቹ ወደ ቀድሞው ኑሯቸው ለመመለስ መንግስት ህግ የማስከበር ስራ በመስራቱ የሀገር ሽማግሌዎች ግጭቱ በባህላዊ ስርዓት እንዲፈታ የጀመሩት እርቀ ሰላም ውጤታማ እንዲሆን አስችሏል ብለዋል።

በሁለቱ ወረዳዎች የተፈናቀሉ ወገኖች ወደ መኖሪያቸው የተመለሱ ሲሆን ህብረተሰቡን በማስተባበር መኖሪያ ቤቶቻቸው ለመጠገንና ሙሉ በሙሉ ለወደመባቸው ደግሞ በአዲስ እንዲገነባላቸው እየተሰራ ነው ብለዋል አስተዳዳሪዎቹ።

አቶ መርጋ አሰፋ በማረቆ ወረዳ የቆሼ ከተማ ነዋሪ ሲሆኑ አቶ ከድር ሰርሞሎ እና ጃቢር መሀመድ የእንሴኖ ከተማ ነዋሪዎች ናቸው።

እንደነዋሪዎቹ ገለፃ በመካከላቸው የተፈጠረው ግጭት እጅግ አስከፊና ከፍተኛ መሰዋእትነት ያስከፈለ ክስተት ነበር ብለዋል።

የክልሉ፣ የዞኑና የወረዳ የስራ ኃላፊዎች ከሃገር ሽማግሌዎች ጋር ሆነው በመስራታቸው ለውጥ ማምጣት እንደተቻለ አስረድተዋል።

በመስቃንና ማረቆ የህብረተሰብ ክፍሎች መካከል የነበረው ግጭት ተፈቶ እርቀሰላም በመፈጸሙ መደሰታቸውን ገልጸው ተፈናቃዮች ወደ ቀዬአቸው ከተመለሱ ወዲህ የእለት ተእለት እንቅሰቃሴ በነጻነት እያካሄዱ መሆናቸውን ገልፀዋል።

የጥል ግድግዳ ፈርሶ ሰላምና እርቅ ሰፍኖ የተነፋፈቀው ቤተሰብ ተገናኝቶ የሶስት አመት መለያየትና ግጭት በአንድነት ሆነው በእርቅ ደመደሙት ሲል የዘገበው የጉራጌ ዞን የመንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያነው።

= ኢትዮጵያን እናልማ!
= የፈረሰውን እንገንባ!
= ለፈተና እንዘጋጅ!

በተጨማሪም እነዚህ ሊንኮችን በመጫን ወቅታዊና ትኩስ መረጃዎቻችንን እንድትከታተሉ እንጋብዛለን፡፡

Facebook:- https://www.facebook.com/gurage1Zone
Website:- https://gurage.gov.et
Telegram:- https://t.me/comminuca
Youtub: -https://www.youtube.com/channel/UCzrcazGvvIO2tG7bQN36Cx

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *