በጉራጌ ዞን ቆሴ ከተማና አካበቢዋ በተፈጠረው የሰላምና ፀጥታ ችግር የተጎዱ የከተማዋና አካባቢዋ ነዋሪዎች በልማትና በመልካም አስተዳደር ስራዎች ተጠቃሚ ለማድረግ እንደሚሰራ በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የደቡብ ክልል ሰላምና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ አለማየሁ ባውዴ ገለጹ።

በቆሴ ከተማና አካባቢዋ ተፈጥሮ የነበረው የጸጥታ ችግር በመፍታት የሰላምና አንድነት ኮንፈረንስ በጉራጌ ዞን በእኖር ኤነር ወረዳ በቆሴ ከተማ ተካሄደ።

በሰላምና አንድነት ኮንፈረንስ የተገኙት በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የደቡብ ክልል ሰላምና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ አለማየሁ ባውዴ የጉራጌና የሀዲያ ህዝቦች ከቀዬአቸው ባለፈ በመላው ሀገሪቱ እየተንቀሳቀሱ በሚሰሩባቸው አካባቢዎች ሰላም በማስፈንና ህግ በማስከበር በግንባር ቀደምትነት ይጠቀሳሉ ብለዋል።

እነዚህ የህብረተሰብ ክፍሎች በረጅም ጊዜ ያካበቷቸው አብሮ የመኖር፣ የመቻቻል፣ የመከባበርና የመተሳሰብ እሴቶቻቸውን ለማጥፋት የሚንቀሳወቀሱ ግለሰቦችና ቡድኖች ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ በጋራ የማውገዝ ልምድ እንደነበራቸው ኃላፊው ገልጸዋል።

ይሁን እንጂ በለውጡ ማግስት የእነዚህ የህብረተሰብ ክፍሎች የአብሮነት እሴት በማይመጥን ደረጃ በእኖርኤነር ወረዳ ቆሴ ከተማና አጎራባች ቀበሌዎች መንግስት መዋቅሩን ዘርግቶ ነዋሪዎቹ በማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ አገልግሎቶች ተጠቃሚ እንዳይሆኑ ጥቂት ግለሰቦችና ቡድኖች ችግር እንደፈጠሩ ገልጸዋል።

በተፈጠረው ችግር የመንግስት እና የግል ተቋማት የወደሙ ሲሆን የንግድ ተቋማት እንዲዘጉና መንግስት ግብርና ታክስ እንዳይሰበሰብ ከማድረግ ባሻገር ህዝቡ በለውጡ መንግስት እምነት እንዳይኖረው ሲሰሩ እንደነበር አቶ አለማየሁ አስረድተዋል።

እንደ አቶ አለማየሁ ገለፃ የክልሉ መንግስት የችግሩ አሳሳቢነት በመገንዘብ የህዝብን ሰላም ወደ ነበረበት ለመመለስ በየደረጃው ከሚገኙ አመራሮች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ ወጣቶችና ሌሎች የህብረተሰብ ስከበር ያሳተፈ ውይይት ማድረግ መቻሉን አስገንዝበዋል።

ሰላም ለማስፈንና የህግ የበላይነት ለማስከበር የሚቀመጥ ቅድመ ሁኔታ ሊኖር እንደማይችል የገለጹት ኃላፊው ግጭት የተፈጠረባቸው ቀበሌያት በህጉ መሰረት በአሁን ሰዓት የጉራጌ ዞን አካል ሲሆኑ ተጠሪነታቸው ደግሞ ለእኖርኤነር ወረዳ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በመሆኑም ቀበሌዎቹና ታዳጊ ማዘጋጃ ቤቱ በህዝብና በመንግሥት ተቋቁመው ስራ መጀመር እንዳለባቸው እና ገላጭ ታፔላዎች መለጠፍ፣ የተዘጉ የንግድ ተቋማት መክፈት ፣ የተቋረጠው ገበያ ማስጀመርና የንግዱ ማህበረሰብ ግብር እና ታክስ መክፈል እንዳለባቸው አሳስበዋል።

ለሰላም ጸር የሆኑ ግለሰቦች በህግ እንዲጠየቁ ነዋሪዎቹ ከመንግስት ጋር ተቀናጅተው መስራት ይጠበቅባቸዋል ያሉት ኃላፊው ህብረተሰቡ የሚጠይቃቸው የልማትና የመልካም አስተዳደር ችግሮች በዘላቂነት ለመቅረፍ የክልሉ መንግስት ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልጸዋል።

የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ መሀመድ ጀማል አመጽ ቀስቃሾችና የፀብ ነጋዴዎች ባህሪያቸው እየቀያየሩ አብሮ ተጋምዶ የኖረ ህዝብን በማደናገር ለእንግልት እና ለስቃይ ከመዳረግ አልፎ የከተማው መሬት በህገወጥ መንገድ በመውረር ህገወጥ ግንባታ ሲያስፋፉ እንደነበርና ግብር እና ታክሰ እንዳይከፈል በማስተጓጎል ከተማዋን ሲያዳክሙ መቆየታቸው ገልጸዋል።

እንደ አቶ መሀመድ ገለፃ በቆሴና አካባቢው የሚኖሩ የጉራጌና የሀድያ ህዝቦች በጋብቻ፣በንግድና፣በደስታና ሀዘን የተሳሰሩ በአጠቃላይ ልማታቸውም ጉዳታቸው ለይቶ ማየት የማይቻል የተጋመዱ ህዝቦች ናቸው።

በመሆኑም በቆሴ ከተማና ዙሪያ በሚገኙ ቀበሌዎች የፀብ ነጋዴዎች በፈጠሩት ችግር አላስፈላጊ መስዋዕትነት የሚከፍሉ ወገኖች ለመታደግ ግጭቱ በፍጥነት እንዲቀረፍ ከክልሉ መንግስት፣ ከሀዲያ ዞን አስተዳደር እና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን ሲሰራ እንደነበር አስረድተዋል።

ይህ ከረዥም ጊዜ ጥረት በኋላ ችግሩ በመፍታት የሰላምና የአንድነት ኮንፈረንስ ማድረግ የተቻለ ሲሆን ኮንፈረንሱ የአካባቢው ሰላም ከማረጋገጥ ባለፈ የጉራጌ እና የሀድያ ህዝቦች የቆየውን የአብሮነትና የመቻቻል እሴቶች የሚያጠናክር እንደሆነም ተናግረዋል።

አቶ መሀመድ አክለውም አሁን መንግስት ከምንም ጊዜ በተለየ ሁኔታ የዜጎች ሰላምና ደህንነት ለመጠበቅ ቅድሚያ ሰጥቶ የሚሰራበት ወቅት በመሆኑ የጉራጌ ዞን መንግስት ከሀዲያ ዞን መንግስት ጋር በመሆን በህገወጦች ላይ ህጋዊ እርምጃ እንደሚወስድ አረጋግጠዋል።

የሀዲያ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ማቲዎስ ሎምቢሶ እንደገለፁት በቆሴ ከተማና አካባቢዎች በሚፈጠሩ ግጭቶች የሚጎዱት ነዋሪዎች ራሳቸው በመሆናቸው የአካባቢያቸውን ሰላም ሊጠብቁ እና ፀብ በቃ በማለት ወደ ልማታቸውና ወደ ቀደመው ፍቅራቸው ሊመለሱ ይገባል።

ሰላም ከራስ፣ ከቤተሰብ፣ ከአካባቢ ይቀዳል ያሉት ዋና አስተዳዳሪው የሀድያና የጉራጌ ዞን ህዝቦች በማንም ሴራና የፀብ ድግስ ሳይሸበሩ የቀድሞ አንድነታቸው አጥናክረው የአካባቢያቸው ሰላም እስኪረጋገጥ በጋራ መቆም ይገባቸዋል ብለዋል።

አክለውም አቶ ማቲዎስ በቀጣይ ጊዜያት በልማት የተጎዳው የቆሴ ከተማ ሊክስ የሚችል ሰራ መስራት እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

በመረጃ ምንጭነት ገጻችን ምርጫዎ ስላደረጉ እናመሰግናለን!!

= ኢትዮጵያን እናልማ!
= የፈረሰውን እንገንባ!
= ለፈተና እንዘጋጅ!

በተጨማሪም እነዚህ ሊንኮችን በመጫን ወቅታዊና ትኩስ መረጃዎቻችንን እንድትከታተሉ እንጋብዛለን፡፡
Facebook:-
https://www.facebook.com/gurage1Zone
Website:- https://gurage.gov.et
Telegram:- https://t.me/comminuca
Youtub: -https://www.youtube.com/channel/UCzrcazGvvIO2tG7bQN36Cx

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *