በጉራጌ ዞን ቀቤና ወረዳ በሌንጫ ቀበሌ በፈረጀቴ ጎጥ 42 ቤቶች ላይ ከፍተኛ የእሳት አደጋ መድረሱ የወረዳው የመንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ፅ/ቤት ገለፀ።

በጉራጌ ዞን በቀቤና ወረዳ በሌንጫ ቀበሌ በፈረጀቴ ጎጥ ልዩ ስሙ ሀጅ አጂቦ መንደር ውስጥ በተነሳው የእሳት ቃጠሎ በመንደሩ የነበሩ 42 ቤቶችን ከነሙሉ ንብረታቸው ሙሉ በሙሉ መውደማቸው ተገልፆል።

በአደጋው ሰለባ የሆኑ የመንደሩ ነዋሪዎች እንደገለፁት በተለምዶ ቆንጥር ተብሎ የሚጠራውን እሾህ ለማፅዳት የመንደሩ ህፃናት በለኮሱት እሳት ቃጠሎው መነሳቱንና እሳቱ ከተነሳ በኋላ በነበረው ከፍተኛ ነፋስ ምክንያት ቃጠሎው ሊስፋፋ ችሏል ብለዋል።

በቃጠሎውም ከወደሙት 42 ቤቶች በተጨማሪ የመንደሩ አርሶደአሮች አመት ለፍተው ያከማቹት ብዛት ያለው እህል፣የቤት ቁሳቁስና አልባሳትና የጓሮ አትክልትና ሰብሎች ሙሉ በሙሉ ሲወድሙ ቤት ውስጥ ታስረው የነበሩ ከብቶች ላይም ጉዳት መድረሱን የሌንጫ ቀበሌ ሊቀመንበር አቶ ሚፍታ ደገፋ የገለፁ ሲሆን።

እንደ ሊቀመንበሩ ገለፃ በእሳቱ ጉዳት የደረሰባቸው የተወሰኑ ሰዎች እንዳሉና በአቅራቢያው የህክምና እርዳታ እየተደረገላቸው መሆኑንም ገልፀው በቃጠሎው ከንብረት ውድመት በዘለለ የሰው ህይወት ላይ ጉዳት አለማድረሱን ገልፀዋል።

እሳቱ ያደረሰው ጉዳት እንዳይደርስ በጊዜ ለመቆጣጠር በመንደሩ የውሃ አቅርቦት በበቂ ሁኔታ አለመኖር እንቅፋት እንደሆነባቸው ገልፀው የጉዳቱ ሰለባዎች አሁን ላይ ምንም ነገር እንዳልቀራቸውና ሜዳ እንደወደቁ ገልጸዋል።

በመንደሩ የሚገኘው መስጂድ ተአምር በሚባል መልኩ ከእሳት አደጋው የተረፈ ሲሆን በመንደሩ ከነበሩት ቤቶች የቀረው መስጂዱ መሆኑንም ተገልጿል።

የቀቤና ወረዳ አስተዳደር አመራሮች እና የአከባቢው ነዋሪዎች ቃጠሎውን ለመግታት ባለው አቅም እርብርብ በማድረግ ቃጠሎው ተስፋፍቶ ተጨማሪ ጉዳት እንዳያደርስ ቃጠሎውን መቆጣጠር መቻሉ ተገልፀዋል።

የደረሰው አደጋ ከባድ በመሆኑ የአደጋው ሰለባዎች ቤት ንብረታቸውን አጥተው ሜዳ ላይ በመውደቃቸው የዞንና የወረዳ አስተዳደር ፣የአከባቢው ተወላጆች፣አጋሮችና ሌሎችም የሚመለከታቸው አካላት ሁሉ ተጎጂዎችን ለማቋቋም ሊረባረቡ ይገባል።

በመጨረሻም የዞኑ ህዝብ ወቅቱ ነፋሻማ በመሆኑ ለእሳት አደጋ የሚያጋልጡ ነገሮች በመለየት ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ ይገባል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *