በጉራጌ ዞን መስቃን ወረዳ በማህበር ተደራጅተው በአንድ ቀን ጫጩት ማሳደግና ፍየል ማሞከት ስራ የተሰማሩ የህብረተሰብ ክፍሎች ውጤታማ መሆናቸውን ገለፁ፡፡

ማህበራቱ ከሌማት ትሩፋት ጋር በማስተሳሰር ይበልጥ ስኬታማ እንዲሆኑ የተጠናከረ ድጋፍ እያደረገ መሆኑንም የወረዳው ግብርና ጽ/ቤት አስታወቀ፡፡

ወ/ሮ መካ ሙዘይን በመስቃን ወረዳ ተቦን ቀበሌ በሴቶች የተመሰረተው የአንድነት ዶሮ ህብረት ስራ ማህበር ሰብሳቢ ናቸው፡፡

ሴቶቹ ነገን የተሻለ ህይወት ለመኖር በማለም መንግስት ያመቻቸላቸውን ምቹ ሁኔታ በመጠቀም የሀሳብ አንድነት በመፍጠር በቡድን ደረጃ የነበረውን የአንድ ቀን ጫጩት ማሳደግ ስራ ወደ አንድነት የዶሮ ህብረት ስራ ማህበር አሸጋግረዋል፡፡

56 አባላት ያሉት የህብረት ስራ ማህበሩ አሁን ላይ ከ6 ሺ በላይ የአንድ ቀን ጫጩት በማስገባት እያሳደጉ መሆኑን የተናገሩት ሰብሳቢዋ ይህን ደረጃ ለመድረሳቸው የመንግስት እገዛ ከፍተኛ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

ሌላኛው በወረዳው ዊጣ ቀበሌ ነዋሪ የሆነችው ወ/ሮ አለምነሽ ፍሰሃ ልጆቿን ለማሳደግ በንግድ ስራ ትንቀሳቀስ እንደነበረና በወቅቱ እስከ ጠረፍ በመጓዝ የተለያዩ ችግሮች ይፈራረቁባት እንደነበር አስታውቃለች፡፡

አሁን ላይ ከሌሎች ሴቶች ጋር በመሆን ዥማር የአንድ ቀን ጫጩት ማሳደጊያ ማህበር መስርተው እየሰሩ መሆናቸውን ገልፀው ዛሬ ላይ ችግሮች ሁሉ ተቀርፈው ውጤታማ መሆንዋን ገልፃለች፡፡

ቡድኑ በኮከብ የዶሮ እርባታ ህብረት ስራ ማህበር ታቅፏል ያለችው ሰብሳቢዋ አባላቱም የተሻለ ህይወት እየኖሩ መሆናቸውን ገልፃ ቀጣይ ማህበሩ ወደ ዩኒየን ለማሳደግ ማቀዳቸውን ተናግራለች፡፡

አቶ መሀመድ ሰይድ ደግሞ በዊጣ ቀበሌ የየምቦሪ ፍየል ማሞከት ማህበር አባል ሲሆን በዘርፉም መንግስት የተለያየ ድጋፍ አድርጎላቸው ስራ መጀመራቸውን ተናግሮ ማህበሩም ውጤታማ ነው ብለዋል፡፡

በወረዳው ግብርና ልማት ጽ/ቤት የዶሮ ሀብት ባለሙያ የሆኑት አቶ ሙሉጌታ ነጋሽ ለተደራጁ ማህበራት ሙያዊ ድጋፍ እንደሚያደርጉ ገልፀዋል፡፡

የመስቃን ወረዳ ግብርና ልማት ጽ/ቤት የእንስሳትና አሳ ሀብት ዘርፍ ሀላፊ አቶ አወል ከድር የጋራ ፍላጎት ያላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች በ188 ቡድን ተደራጅተው በወተት ከብት እርባታ፣ በአንድ ቀን ጫጩት ማሳደግና በበግና ፍየል ማሞከት ስራ ተሰማርተዋል ብለዋል፡፡

ማህበራቱ ይበልጥ ስኬታማ እንዲሆኑ በሀገር አቀፍ ደረጃ ከተቀረፀው የሌማት ትሩፋት ፕሮጀክት ጋር የማስተሳሰር ስራ እየተሰራ መሆኑን የተናገሩት ሀላፊው በዚህም ዘርፉን በመንደር እንዲታቀፍ ተደርገዋል።

ዘገባው የወልቂጤ ኤፍ ኤም ነው

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *