በጉራጌ ዞን ለመንገድ ልማት ስራ የተሰጠው ልዩ ትኩረት አበረታች ነው ሲሉ የማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የመሰረተ ልማት ዘርፍ አስተባባሪ እና የትራንስፖርት እና መንገድ ልማት ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር መሀመድ ኑርዬ ገለጹ።


በህብረተሰቡ፣ በባለሀብቱና በመንግስት ትብብር የተጀመረው የመንገድ ንቅናቄ አጠናክሮ በማስቀጠል በዞኑ ያሉ ቀበሌዎችን እርስ በርስ የማገናኘት ስራ ላይ በትኩረት እንደሚሰራ የጉራጌ ዞን አስተዳደር አስታወቀ።

በጉራጌ ዞን ቸሀ ወረዳ በኦገር ቀበሌ በማህበረሰቡና በመንግስት ትብብር ከ8 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር በላይ የተሰራው 11 ነጥብ 1 ኪሎ ሜትር የጠጠር መንገድ ተመርቆ ለአገልግሎት ክፍት ሆነ።

የማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የመሰረተ ልማት ዘርፍ አስተባባሪ እና የትራንስፖርት እና መንገድ ልማት ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር መሀመድ ኑርዬ እንደተናገሩት መንገድ ከሌለ አጠቃላይ ማህበራዊ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎች በቀላሉ ማከናወን አይቻልም ብለዋል።

የጉራጌ ማህበረሰብ እና መንግስት ለመንገድ ልማት ስራ አስቀድሞ የተረዱና አሁንም አሁንም ልዩ ትኩረት ሰጥቶ በመስራታቸው አበረታች ውጤት እያስመዘገበ እንደሆነ ተናግሯል።

ቢሮውም በተለይ በመንገድ ልማት ዘርፍ የሚደረጉ እንቅሰቃሴዎች አስፈላጊውን እገዛ እንደሚያደርግ ያስታወቀት ዶ/ር መሀመድ ህዝቡ ከመንግስት ጎን ሆኖ እያከናወነ ያለው አኩሪ የልማት ተግባራትን አጠናክሮ እንዲስቀጥል አሳስበዋል።

የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ላጫ ጋሩማ እንደተናገሩት የጉራጌ ማህበረሰብም በመንገድ ልማት ስራ ከጥንት ጀምሮ ልምድ ያለው ሲሆን ዛሬም የአባቶች አርዓያ በመከተል ከመንግስት ጋር በመቀናጀት ይህን እያከናወነ ይገኛል።

በመሆኑም በመንግስ፣ በህብረተሰቡና በባለሀብቱ የተጀመረው ይህ የመንገድ ንቅናቄ አጠናክሮ በማስቀጠል በዞኑ ያሉ ቀበሌዎችን እርስ በርስ የማገናኘት ስራ ላይ በትኩረት እንደሚሰራ አስታውቀዋል።

በአሁን ሰአት ግብርና በከፍተኛ ሁኔታ የኢኮኖሚ ምንጭ ሆኗል ያሉት አቶ ላጫ መንገዱም አርሶ አደሩ ያመረተው ምርት በቀላሉ ወደ ገበያ በማውጣት ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚ እንዲሆን የሚያደርግ በመሆኑ እንክብካቤ ሊደረግለት እንደሚገባ መክረዋል።

የቸሀ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ጥላሁን ሽምንሳ በዘንድሮ አመት የወረዳው ማህበረሰብ በማስተባበር ከ34 ነጥብ 8 ሚሊየን ብር በላይ በማሰባሰብ 34 ኪሎ ሜትር መንገድ ጠጠር ማልበስ መቻሉ አስረድተዋል።

የዚህ አካል የሆነው ይህ የኦገር መንገድ 3 ወረዳዎች ማለትም ጌታ፣ጉመርና እኖር ወረዳዎች የሚያገናኝ ሲሆን የመገሰስ፣ወርኬማ የቀርቃር፣ማጅጉንየ ቀበሌያት ያስተሳስራል ነው ያሉት።

በቀጣይ የክልልና የዞን ድጋፍ ከታከለበት አገና ከተማ እና እኖር ወረዳ የሚያገናኝ ሲሆን መንገዱ በማህበረሰቡ የደርስ የነበረው ችግር ከመቅረፉ በተጨማሪ ልማትን የሚያፋጥንና የመልካም አስተዳደር ችግር የሚቀርፍ መሆኑ አስገንዝበዋል።

የጉራጌ ዞን ትራንስፖርት እና መንገድ ልማት መምሪያ ኃላፊ አቶ ሙራድ ከድር የኢኮኖሚ እና የማህበራዊ ብልጽግና ለማሳካት መንገድ ወሳኝ ነው።በዞኑ በዘንድሮ አመት ለመንገድ ልማት ስራ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ በማህበረሰቡና በባለሀብቱ 2መቶ 35 ሚሊየን ብር በማሰባሰብ ከ2 መቶ 50 ኪሎ ሜትር በላይ የመንገድ ልማት ስራ መሰራቱ አስታውቋል።

በተለይ በመስቀልና በአረፋ እንዲሁም ሰው ሲታመም ይደርስ የነበረው ችግር እጅግ ከባድ እንደነበር አስታውሰው መንገዱ ይህንን የቀረፈ በመሆኑ አስፈላጊውን እንክብካቤ ሊደረግለት እንደሚገባ ገልጸዋል።

የአካባቢው ነዋሪዎች እንደተናገሩት መንገዱ አጎራባች ወረዳዎች እና በርካታ ቀበሌዎች የሚያገናኙ በመሆናቸው የህዝብ ለህዝብ ትስስር እንዲኖርና አብሮነትን የሚያጠናከር መሆኑን አብራርተዋል።

ለዚህ የመንገድ ስራ ከወረዳው መንግስት ጋር በመሆን የገንዘብ እና የጉልበት አስተዋጽኦ አድርገው ዛሬ መመረቁ እጅጉ ደስታኛ መሆናቸው ተናግረዋል።

ከዚህ በፊት ምቹ መንገድ ባለመኖሩ የሰው ህይወት ለመጠፋት ምክንያት ይሆን እንደነበር ገልጸው ዛሬ ግን በኢኮኖሚያዊ በማህበራዊና በሁሉም ዘርፍ ተጠቃሚ የሚያደርግ በመሆኑ ለመንገዱ አስፈላጊውን እንክብካቤ እንደሚያደርጉለት ተናግሯል።

በእለቱም ለመንገድ ስራው አስተዋጽኦ ላደረጉ አካላት እውቅናና ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *