በየደረጃው በሚገኙ የህዝብ ምክር ቤቶች የጸደቀውን በጀት በአግባቡ በማስተዳደር ለታለመለት አላማ እንዲውል በትኩረት እየሰራ መሆኑን የጉራጌ ዞን ፋይናንስ መምሪያ አስታወቀ።

መምሪያው የ2016 አመተ ምረት የተግባር አፈጻጸም ግምገማና የ2017 በጀት አመት እቅድ ላይ ያተኮረ ውይይት በወልቂጤ ከተማ አካሂዷል።

የጉራጌ ዞን ፋይናንስ መምሪያ ኃላፊ አቶ አብዶ ሀሰን በመድረኩ ላይ እንዳሉት መንግስት ለፋይናንስ ሴክተር በሰጠው ስልጣንና ኃላፊነት መሰረት በየደረጃው በሚገኙ የህዝብ ምክር ቤቶች የጸደቀውን በጀት በአግባቡ በማስተዳደር ለታለመለት አላማ እንዲውል በትኩረት እየሰራ ነው።

የፋይናንስ ስርዓቱ ጤናማ በሆነ መልኩ እንዲመራ የሚያስችሉ የውስጥ የኦዲትና ቁጥጥር ስርዓት የማጠናከር ስራ መሰራቱን ገልጸዋል።

በ2016 በጀት አመት ለዞኑ ከተመደበው 4 ቢሊዮን 57 ሚሊዮን 190 ሺህ 528 ብር ውስጥ ለደመወዝ 60 ነጥብ 84 ከመቶ፣ ለስራ ማስኬጃ 21 ነጥብ 74 ከመቶ እንዲሁም ለካፒታል 17 ነጥብ 42 ከመቶ በጀት በመመደብ ስራ ላይ ማዋል መቻሉን የመምሪያው ኃላፊ አብራርተዋል።

እንደ አቶ አብዶ ገለጻ ነባሩ ጉራጌ ዞን በአዲሱ አደረጃጀት መሰረት ወደ አራት የተለያዩ መዋቅሮች መከፋፈሉን ተከትሎ የበጀት፣ የእዳ፣ የተሽከርካሪና ሌሎች ንብረቶች ያለምንም 3ኛ ወገን ጣልቃ ገብነት ተስማምቶ ክፍፍሉ እንዲካሄድ የተመራበት መንገድ አበረታች ነው።

አክለውም ባለበጀት ተቋማት ኦዲት የማድረግ ሽፋን ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ ቢመጣም በኦዲት የተገኘውን ግኝት ተከታትሎ ከማስመለስ አንጻር ክፍተት የሚስተዋል በመሆኑ በቀጣይ ክፍተቱ ለመሙላት በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ ኃላፊው ገልጸዋል።

በቀጣይ ያገለገሉ ንብረቶች በአግባቡ በማስወገድ ለገቢ አሰባሰብ ስራ ልዩ ድጋፍ በማድረግ እና አላስፈላጊ ወጪዎችን በመቀነስ ገንዘብ የሚገኝባቸው አማራጮች ላይ በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ አቶ አብዶ አስገንዝበዋል።

የጉራጌ ዞን ፋይናንስ መምሪያ የመንግስት ፋይናንስ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ሳሊም ሸምሱ የአፈፃፀም ሪፓርት ባቀረቡበት ወቅት እንደገለጹት ለዞኑ የሚመደበውን በጀት በቀመር መመሪያ መሰረት በፍትሃዊነት በማከፋፈል የማስተዳደር ስራ እየተሰራ ይገኛል።

በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ለዞኑ ከተመደበው በጀት 87 ነጥብ 09 ከመቶ ለወረዳዎችና ከተማ አስተዳደሮች፣ 12 ነጥብ 46 ከመቶ ለዞን ማዕከል እንዲሁም ዜሮ ነጥብ 45 ከመቶ ለዞን መጠባበቂያ በመመደብ ስራ ላይ ማዋል መቻሉን አብራርተዋል።

በዞኑ ተቋማት ለአገልግሎት በማይመች ሁኔታ ተከማችተው የነበሩ አገልግሎት የማይሰጡ ንብረቶች የፋይናንስ ደንብና መመሪያ መሰረት በማስወገድ ከ4 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ በመሰብሰብ አርዓያነት ያለው ተግባር መከናወኑን አቶ ሳሊም ተናግረዋል።

በጉራጌ ዞን ፋይናንስ መምሪያ የበጀት ሲቪክ ትብብር ዘርፍ ኃላፊ አቶ ቴዎድሮስ አለሙ በበኩላቸው የተራድኦ ድርጅቶች በሌሉባቸው አካባቢዎች ገብተው ህብረተሰቡን ተጠቃሚ እንዲያደርጉ የሚመለከታቸው ባለርሻ አካላቶች መልካም ግንኙነት በመፍጠርና መፃፃፍ ይኖርባቸዋል ብለዋል።

በትራድኦ የሚገኙ በጀቶችን ለታመላቸው ዓላማ በማዋል ህብረተሰቡ ተጠቃሚ እንዲሆን የፋይናንስ ሴክትር በትኩረት መስራት አለበት እያሉት አቶ ቴድሮስ አለሙ በምክር ቤት ያልፀደቀ በጀቶች መጠቀምም እንደማይገባ ተናግረዋል። የተራዶ በጀት በወቅቱ ስራ ላይ በማዋልና ሂሳቡን ኦዲት በማድረግ ማወራረድ ይገባልም ብለዋል።

የውይይቱ ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያየት በህዝብ ምክር ቤቶቾ የጸደቀውን በጀት ለህብረተሰቡ ልማት ለማዋል እንዲቻል ዞኑ የሚያመነጨውን ሀብት ለመሰብሰብ በሚደረገው ጥረት ሁሉም ባለድርሻ አካላት የድርሻውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።

በመንግስት የሚመደበው በጀት በአግባቡ ስራ ላይ እንዲውል የቁጥጥርና የኦዲት ስራ ውጤታማ በሆነ መልኩ ለማከናወን የሚያስችል የክህሎት ስልጠና ለዘርፉ ባለሙያዎች ሊሰጥ ይገባል ሲሉ ጠቁመዋል።

የጉራጌ ዞን ፋይናንስ መምሪያ ኃላፊ ከወረዳና ከተማ አስተዳደር የፋይናንስ ጽ/ቤት ኃላፊዎች ጋር የ2017 በጀት ዓመት ዕቅድ ላይ የግብ ስምምነት የተፈራረሙ ሲሆን በተገባደደው በጀት አመት የተሻለ አፈጻጸም ያሳዩ ወረዳዎች የዋንጫና የሰርተፊኬት ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *