በየደረጃው በሚገኙ ምክር ቤቶች የተወከሉ ህዝብ ተወካዮች የክትትልና ቁጥጥር ስራቸው በማጠናከር የህዝብ ፍትሀዊ ተጠቃሚነት ሊያረጋግጡ እንደሚገባ የጉራጌ ዞን ምክርቤት ገለፀ።

በዞኑ በ2013 ዓመተ ምህረት በተካሄደው 6ኛ ዙር ሀገራዊና ክልላዊ ምርጫ ለህዝብ ተወካዮችና የክልል ምክርቤቶች ተወክለው የገቡ የህዝብ እንደራሴዎች በየደረጃው ከወከላቸው ህዝብ ውይይት ሲያደርጉ ቆይተው ዛሬ ከህዝብ በተነሱ ጥያቄዎች ከዞኑ አስፈፃሚ አካላት ውይይት አድርገዋል።

በውይይት መድረኩ የተገኙት የጉራጌ ዞን ምክርቤት ዋና አፈ ጉባኤ ክብርት ወይዘሮ አርሺያ አህመድ እንደገለፁት በዞኑ ባለፉ ወቅቶች በየደረጃው የሚገኙ ህዝብ የወከላቸው ተወካዮች በሚያደርጉት ድጋፍ፣ ክትትልና ቁጥጥር እንዲሁም በአስፈፃሚው ጥረት በርካታ ለውጦች መጥተዋል።

አሁንም በ2014 አመተ ምህረት በአዲሱ ምክርቤት ተመርጠው ወደ ተወካዮች ምክርቤት የገቡ ተወካዮች በዚህ አጭር ጊዜ የወከላቸው ህዝብ ለማወያየትና ለማድመጥ መምጣታቸው መንግስትና ተወካዮቹ ሊመሰገኑ ይገባል ብለዋል።

የዞኑ ህዝብ አዳጊ እና በርካታ የልማትና መልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ያሉት መሆኑ አመላክተው በቀጣይም በየደረጃው በሚገኙ ምክር ቤቶች የተወከሉ ህዝብ ተወካዮች የክትትልና ቁጥጥር ስራቸው በማጠናከር የህዝብ ፍትሀዊ ተጠቃሚነት ሊያረጋግጡ እንደሚገባ ገልፀዋል።

የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ መሀመድ ጀማል በበኩላቸው ከዞኑ ጀምሮ በየደረጃው የሚገኙ የህዝብ ተወካዮች በሚያደርጉት ክትትልና ቁጥጥር እንዲሁም በሚሰጧቸው ግብረመልሶች በርካታ ክፍተቶቻችን መሙላት ችለናል ብለዋል።

እንደ አቶ መሀመድ ገለፃ አሁንም የፓርላማና የክልል ተወካዮች በየደረጃው ህዝቡ በማወያየት ያመጧቸው የህዝብ ጥያቄዎች በትክክልም በዞናችን ያሉና አስፈፃሚው በቀጣይ በትኩረት ችግሮቹ ለመፍታት መስራት አለበት።

በዞናችን ባለፉት ወቅቶች በተደረጉ ጥረቶች በርካታ የልማት፣መልካም አስተዳደርና የዴሞክራሲ ግንባታ ስራዎች መሰራታቸው ገልፀው አሁንም ከንፁህ መጠጥ ውሃ ተደራሽነት፣ከመንገድ ልማት፣ከመብራት ተደራሽነትና አገልግሎት አሰጣጥ፣ከተቋማት አገልግሎት አሰጣጥና ከአንድ አንድ ተቋማት ተደራሽነትና በሌሎችም ዘርፎች የሚነሱ ችግሮች መኖራቸው ገልፀው በቀጣይ አስፈፃሚው ህዝቡ በማሳተፍና ከሚመለከታቸው አካላት በቅንጅት ለመፍታት ጥረት ይደረጋል ብለዋል።

አክለውም አስተዳዳሪው ከሰላምና ፀጥታ አንፃር በተደረጉ ጥረቶች በዞናችን አስቸጋሪ የነበሩ ሁኔታዎች መፍታት መቻሉና በቀጣይም ቀሪ የሰላምና ፀጥታ ችግሮችና ህገወጥነቶች ለማረም በትኩረት ይሰራል ብለው ለተወካዮችም አንድ አንድ መታገዝ የሚገባቸውና በየደረጃው መፈታት ያለባቸው ችግሮችም አመላክተዋል።

በዞኑ በተለያዩ ወረዳና ከተሞች ተቀሳቅሰዉ ከህዝቡ ውይይት ሲያደርጉ የቆዩ ተወካዮች እንደገለፁት ባለፉት የለውጥ አመታት በተከናወኑ የልማትና መልካም አስተዳደር እንዲሁም የዴሞክራሲ ግንባታ ስራዎች በርካታ ውጤቶ መኖራቸውና ህዝቡም እውቅና እየሰጠ መሆኑ ተናግረዋል።

ነገር ግን ከህዝቡ አዳጊ ፍላጎትና ያደሩ የልማትና መልካም አስተዳደር ችግሮች አሁንም በዞኑ አሳሳቢ መሆናቸው አመላክተዋል።

እንደ ተወካዮቹ ገለፃ በዞኑ ከንፁህ መጠጥ ውሃ ተደራሽነት፣ ከመንገድ ልማት፣ከመብራት ተደራሽነት ችግር እና መቆራረጥ፣ከከተሞች ልማት፣ ከጤናና ከትምህርት ኮሌጆች ተደራሽነት ሌሎችም የሚነሱ ችግሮች መኖራቸው ገልፀው በቀጣይ አስፈፃሚው ህዝቡ በማሳተፍ መፍታት ይገባል።

በተጨማሪም ከሰላምና ፀጥታ አንፃር የማቆና ምስራቅ መስቃን ችግር መፈታቱ፣ቆሴ አካባቢ ችግር ለመፍታት የተሰራ ስራ እና ሌሎችም በዞናችን አስቸጋሪ የነበሩ ሁኔታዎች ለመፍታት የተሰራ ስራ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ብለዋል።

በሌላ በኩል በአንድ አንድ ወረዳዎች ከአጎራባች ወረዳና ዞኖች ስራ የሚፈልጉ ችግሮች በመኖራቸው እንዲሁም ተፈናቃዮች በተገቢ ከማደራጀት ጋር ተጨማሪ ስራ እንደሚጠይቅ ጠቁመዋል።

ሌሎችም ህዝቡ ከኑሮ ውድነትና ህገ ወጥ ንግድ ቁጥጥር፣ ከአደረጃጀት ጥያቄና፣ከመብራት ዲስትሪክት፣ከከተሞች መሬት ወረራ፣ከማዳበሪያ ዋጋ መወደድ እና ሌሎችም ችግሮች ታቅዶ ደረጃ በደረጃ በቅንጅት መፍታት እንደሚገባ አመላክተዋል።

በመጨረሻም ተወካዮቹ በዞኑ በየደረጃው ያለው አመራር የውይይት መድረኮች እንዲሳኩ ላደረገው ጥረትና አስፈፃሚው ግብረመልሱ ለመውሰድ ለነበረው ዝግጁነት ምስጋናቸው አቅርበዋል።

በመድረኩም የዞኑ አመራሮች፣የጉብሬና ወራቤ ገጠር መንገድ ዲስትሪክት ሀላፊዎች፣የሆሳና መብራት ዲስትሪክት ሀላፊና ሌሎችም የሚመለከታቸው አካላት ተገኝተው ለተነሱ ጥያቄዎች መረጃና ማብራሪያ በመስጠት በቀጣይ ችግሮቹ በሚፈታበት ሁኔታ መግባባት ተፈጥረዋል።

= ኢትዮጵያን እናልማ!
= የፈረሰውን እንገንባ!
= ለፈተና እንዘጋጅ!
በተጨማሪም እነዚህ ሊንኮችን በመጫን ወቅታዊና ትኩስ መረጃዎቻችንን እንድትከታተሉ እንጋብዛለን፡፡

Facebook:- https://www.facebook.com/gurage1Zone
Website:- https://gurage.gov.et
Telegram:- https://t.me/comminuca
Youtub: -https://www.youtube.com/channel/UCzrcazGvvIO2tG7bQN36C

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *