በዞኑ የ2016 ዓ.ም ክልላዊ የ8ኛ ክፍልና ዞናዊ የ6ኛ ክፍል የእርከን ማጠቃለያ ፈተናዎች ፍጹም ሰላማዊና ከኩረጃ ነጻ በሆነ መልኩ ለመስጠት ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን ድርሻ መወጣት እንዳለባቸው የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ላጫ ጋሩማ አሳሰቡ።


በዞኑ የ2016 ዓ.ም ክልላዊ የ8ኛ ክፍልና ዞናዊ የ6ኛ ክፍል የእርከን ማጠቃለያ ፈተናዎች ፍጹም ሰላማዊና ከኩረጃ ነጻ በሆነ መልኩ ለመስጠት ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን ድርሻ መወጣት እንዳለባቸው የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ላጫ ጋሩማ አሳሰቡ።

የጉራጌ ዞን ትምህርት መምሪያ በ2016 ዓ.ም ክልላዊ የ8ኛ ክፍልና ዞናዊ የ6ኛ ክፍል የእርከን ማጠቃለያ ፈተናዎች አስተዳደር የምክክርና የኦረንቴሽን መድረክ በእምድብር ከተማ አካሄደ።

በዞኑ የሚሰጡ ፈተናዎች ውጤታማ በሆነ መልኩ ለመስጠት አስፈላጊውን የቅድመ ዝግጅት ስራዎች ማጠናቀቁን መምሪያ ገለጸ።

የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ላጫ ጋሩማ በምክክርና በኦረንቴሽን መድረኩ ተገኝተው እንዳሉት የ8ኛ ክፍል ክልልና የ6ኛ ክፍል ዞን አቀፍ ፈተና ፍጹም ሰላማዊ በሆነ መልኩ ለመስጠት ይሰራል።

በትምህርት ጥራት ላይ ያጋጠመው ችግር ለመፍታትና የትምህርት ስርአቱ ለማሻሻል የፈተና አስተዳደር ስርአቱ ማሻሻል ይገባል ያሉት አቶ ላጫ ለዚህም አምና በዞኑ ከኩረጃ ነጻ ፈተና በመሰጠቱ በ8ኛ ክፍል ከተፈተኑ ተማሪዎች 10 በመቶ ብቻ ማለፉን ገልጸዋል።

ፈተናው ከኩረጃ ነጻ በሆነ መልኩ ለመስጠትና ፍጹም ሰላማዊ በሆነ መልኩ በሰላም እንዲጠናቀቅ ለማስቻል ሁሉም ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ አሳስበዋል።

የጉራጌ ዞን ትምህርት መምሪያ ኃላፊ አቶ መብራቴ ወልደማርያም በበኩላቸው የ2016 ዓ.ም የ8ኛ ክፍል ክልልና የ6ኛ ክፍል ዞን አቀፍ የእርከን የፈተና ለመስጠት ቅድመ ዝግጅት መጠናቀቁን ተናግረዋል።

በዞኑ በ326 ትምህርት ቤቶች የ8ኛ ክፍል ክልል አቀፍ ፈተና 24 ሺህ 623 ተማሪዎችና የ6 ክፍል ዞን አቀፍ ፈተና በ377 ትምህርት ቤቶች 19 ሺህ 230 ተማሪዎች ፈተናው ለመስጠት ዝግጅት መደረጉን ገልጸዋል።

ፈተናው ውጤታማ በሆነ መልኩ ለመስጠት ከዚህ ቀደም በርካታ ስራዎች ሲሰራ መቆየቱን አንስተው የ8ኛ ክፍል ተማሪዎች በኦንላይና የ6ኛ ክፍል ተማሪዎች በዞኑ የመመዝገብ ስራ ተሰርቷል ብለዋል።

ኩረጃ በሀገር ደረጃ በትምህርት ስርአቱ ላይ ትልቅ ጫና ፈጥሮ መቆየቱ አንስተው በዞኑ በባለፉት ሁለት አመታት በተሰራው ስራ ከኩረጃ ነጻ ፈተና መስጠት መቻሉን ጠቁመው ይህም የትምህርት ማህበረሰብና አመራሩ የኩረጃ ጉዳት በተገቢው በመገንዘቡ ነው ብለዋል።

በየደረጃው ያሉ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ተማሪዎች የፈተና ደንብ በማክበር ፈተናው በተገቢው እንዲፈተኑ ማድረግ እንዳለባቸው የገለጹት አቶ መብራቴ ተማሪዎችም የፈተናው ህግና ስርአት በማክበር ፈተናው በተገቢው እንዲወስዱ አስገንዝበዋል።

ከመድረኩ ተሳታፊዎች መካከል የጉራጌ ዞን ፖሊስ አዛዥ ዋና ኢንስፔክተር ገና ደገሙና አቶ ሽኩረታ አብድርከሪም የእኖር ወረዳ ትምህርት ጽህፈት ኃላፊ በጋራ በሰጡት አስተያየት ፈተናው በሰላም እንዲጠናቀቅ አስፈላጊውን የቅድመ ዝግጅት ስራዎች መሰራቱን ተናግረዋል።

ፈተናው በሰላም ተጀምሮ እንዲጠናቀቅ የጸጥታ መዋቅር ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመቀናጀት ስራዎች እንደሚሰራ ገልጸዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *