በዞኑ የጥምቀት በዓል በሰላም እንዲከበር አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት መደረጉ የጉራጌ ዞን ሰላምና ጸጥታ መምሪያ አስታወቀ።


ቀጣይ የሚከበረው የጥምቀት በዓል አከባበር በተመለከተ ከወልቂጤ ጊዜያዊ ኮማንድ ፖስትና ሚመለከታቸው አካላት ጋር በወልቂጤ ከተማ ውይይት ተደርጓል።

የጉራጌ ዞን ሰላምና ጸጥታ መምሪያ ኃላፊ አቶ የህያ ሱልጣን እንዳሉት የጥምቀት በዓል ከጥንት ጀምሮ ማህበረሰቡ የጋራ እሴት አድርጎ ሙስሊም ክርስቲያኑ በመከባበርና በመቻቻል የሚያከብረው የአደባባይ በዓል ነው።

ዘንድሮም በዓሉ በሰላማዊ ሁኔታ እንዲከበር ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመነጋገር አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት መደረጉ የተናገሩት አቶ የህያ በዞኑ በ379 የጥምቀት ባህር የሚከበርባቸው አካባቢዎች ፈጣን የመረጃ ቅብብሎሽ እንዲደረግ አሳስበዋል።

በዓሉ ሲከበር አስፈላጊ ያልሆኑ ጥቅሶች፣ባነሮች፣ትሸርቶች፣ምንም አይነት የእርችት ሆነ የጦር መሳረያ ተኩስ ማድረግ የተከለከለ መሆኑን አስታውቀዋለሰ።

አቶ የህያ አክለውም በዓልን ምክንያት በማድረግ በከተሞች አካባቢ የአላስፈላጊ ጩኸትና ሌሎች ጸረ ሰላም ድርጊቶች መፈጸም እንደማይቻልም አክለዋል።

የጥምቀት በዓል በሰላም እንዲከበር የስጋት ቀጠናዎችን በመለየት ከአጎራባች ዞኖችና ልዩ ወረዳ በመነጋገር እንዲሁም ከጊዜያዊ ኮማንድ ፖስት ጋር በጋራ እየተሰራበት እንደሆነ አስታውቀዋል።

የወልቂጤ ከተማ ጊዜያዊ ኮማንድ ፖስት ሰብሳቢ ምክትል ኮሚሽነር ቦጋለ ቃሎሬ እንደተናገሩት የግል ፍላጎት ያላቸው አካላት በዓሉ በሰላም እንዳይከበር እንዲሁም በየ አካባቢው ትንኮሳ ለማድረግ የሚጥሩ አካላት ስለሚኖሩ ትንኮሳዎችን መመከትና አጥፊዎችን በቁጥጥር ስር እንዲውሉ መስራት ያስፈልጋል ብለዋል።

ኮማንደር አክለውም ለዚህም የጸጥታ አካሉ የበለጠ በማጠናከር ከወጣቶች፣ከሀይማኖት አባቶች፣ከትራፊክ እና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በሆን ተቀናጅቶ መስራት እንደሚገባ መክረዋል።

በተለይ በወልቂጤ ከተማ እና አጎራባች አካባቢዎች በዓሉ የሚያከብሩ ምእመናን ያለምንም የጸጥታ ስጋት እንዲያከብሩ የጸጥታ አካሉ በኃላፊነት እንዲሰራ ትዛዝ አስተላልፏል።

የወልቂጤ ከተማ ጊዜያዊ ኮማንድ ፖስት ምክትል ሰብሳቢ ኮማንደር ታምራት ታንቱ በበኩላቸው የጥምቀት በዓል በዩኒስኮ የተመዘገበ የአደባባይ በዓል ሲሆን በርካታ ጎብኞች ይታደሙበታል።

ወልቂጤ ከተማ አሁን ያለችበት ነባራዊ ሁኔታ በመረዳት ህዝቡ ከመንግስት ጋር በቅንጅት በመስራት ከዉጪና ከውስጥ የሚመጡ ትንኮሳዎችን መከታተልና አሳልፎ መስጠት አለበት ነው ያሉት።

ለዚህ ደግሞ ኮማንድ ፖስቱ አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት ማድረጉ ገልጸዋል።

በውይይቱ የተገኙ አካላት እንዳሉት በየ አካባቢው የስጋት ቀጠናዎችን የመለየትና ከሚመለከታቸው አካላት እንዲሆን ከሌሎች የእምነት ተቋሟት ጋር ውይይት ተደርጓል።

ችግሮች እንዳይፈጠሩ አስፈላጊውን ቁጥጥር ለማድረግ ፈጣን የሆነ የመረጃ ልውውጥ ማድረግና ቅንጅታዊ አሰራርን በማጠናከር በዓሉ በሰላም እንደከበር የበኩላቸውን እንደሚወጡ ገልጸዋል።

ብሄርን ተኮር ያደረጉና የራሳቸው ፍላጎት ሊያራምዱ የሚፈልጉ በዓሉ በሰላም እንዳይከበር የሚፈልጉ ጽንፈኛ ሀይሎች ያሉ በመሆኑ ክትትል ማድረግ ከሁሉም ይጠበቃል ብለዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *