በዞኑ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ በሁሉም አካባቢዎች በተጠናከረ መልኩ በመስራት የአርሶ አደሩ ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ እንደሚገባ የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ላጫ ጋሩማ አሳሰቡ።

በጉራጌ ዞን የ2016 ዓ.ም ዞናዊ የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ስራ በጉመር ወረዳ ተጀመረ።

የዘንድሮ የተጀመረው የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ስራ አጠናክረው እንደሚሰሩ በወረዳው አግኝተን ያነጋገርናቸው አርሶ አደሮች ተናገሩ።

የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ላጫ ጋሩማ የዘንድሮ የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ስራ በይፋ ባስጀመሩበት ወቅት እንዳሉት መሬት በተገቢው ባለመጠበቅና ተንከባክቦ ባለመያዝ ምክንያት ለአየር መዛባት፣ የአፈር ለምነት እንዲቀንስ፣ ሰብል እንዳይለማና ምርት እንዲቀንስ ያደርጋል።

በመሆኑም አርሶ አደሩ ለትውልዱ የሚያስተላልፈው ብቸኛ ሀብቱ መሬት በመሆኑ በተገቢው በመጠበቅና እንክብካቤ በማድረግ ለትውልዱ ማስተላለፍ እንዳለባቸው ተናግረዋል።

ለዚህም አርሶ አደሩ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ በተጠናከረ መልኩ መስራት እንዳለባቸው ያነሱት አቶ ላጫ ጠረጴዛማ እርከን በስፋት በመስራት ሰብሎችን በማልማት ምርትና ምርታማነታቸውን ለማረጋገጥ በትኩረት መስራት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

የጉራጌ ዞን ምክትል አስተዳዳሪና የግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ አበራ ወንድሙ በበኩላቸው የዞኑ አርሶ አደሮች የአፈርና ጥበቃ ስራ ከተጀመረ ወዲህ የዳበረ ልምድ ያአላቸው በመሆኑ በዘርፉ በስፋት እየተሰራ ይገኛል።

በዞኑ በ270 ንዑስ ተፋሰስ ከ67 ሺህ በላይ ሄክታር መሬት የሚለማ ሲሆን በዚህም 385 ሺህ በላይ የህብረተሰብ ክፍሎች የሚሳተፉ መሆኑን ተናግረዋል።

በዞኑ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ ከተጀመረ ወዲህ ከዚህ በፊት በጎርፍ ተሸርሽሮ የሚሄደውን አፈር በማስቀረት የአፈር ለምነት እንዲጨምር፣ የውሃ አቅም እንዲጨምር ብሎም በመኸር ወቅት በጠረጴዛማ እርከን የተለያዩ ሰብሎች እያለሙ በመሆኑ አርሶ አደሩ ያለው ጠቀሜታ በመረዳታቸው በስፋት እየሰሩ መሆኑን አንስተዋል።

የዞኑ አርሶ አደሮች በተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ስራ ያለውን ልምድ ይበልጥ በመጠቀም የተጀመረው የአፍርና ውሃ ጥበቃ ስራ አጠናክሮ መስራት ይገባል ያሉት አቶ አበራ ለዚህም መምሪያው አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልጸዋል።

በዞኑ እየተሰሩ ያሉ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ በቀጣይ በስነ ህይወታዊ ስራዎችን አጠናክሮ መስራት ላይ ሁሉም የበኩሉን ድርሻ መወጣት እንዳለበት ተናግረዋል።

የጉመር ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ፈይሰል ሀሰን በወረዳው የተጀመረው የተፋሰስ ልማት ስራ አጠናክሮ ከመስራት ጎን ለጎን በሌሎችም የግብርናና የልማት ስራዎች ላይ በትኩረት እንዲሰሩ አመላክተዋል።

የወረዳው ምክትል አስተዳዳሪና ግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ ደገሙ አለሙ በወረዳው በ52 ንዑስ ተፋሰሶች 5ሺህ 5መቶ 50 ሄክታር መሬት በአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ እንደሚለማ ገልጸዋል።

የወረዳው አርሶአደሮች የተለያዩ አደረጃጀቶችን በመጠቀም ከዚህ በፊት በርካታ የተራቆቱና ከምርት ርቀው የነበሩ መሬቶች በተፋሰስ ልማት ስራ በማልማት መሬቱ ወደ ምርት መቀየር መቻሉን ጠቅሰው በዛሬው እለት የተጀመረው ስራ የበለጠ አጠናክረው እንዲሰሩም አመላክተዋል።

አቶ ሙከረም ኑረዲን፣ አቶ ጀማል ረሻድና ወይዘሮ ላዲያ ኤብዶ በወረዳው የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ስራ ሲያከናውኑ ያገኘናቸው አርሶ አደሮች ናቸው።
አርሶ አደሮቹ በጋራ በሰጡት አስተያየት የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ስራ መስራት ከጀመሩ ወዲህ ከዚህ ቀደም በጎርፍ ተሸርሸሮ ይሄድ የነበረውን ለም መሬታቸውን በማስቀረት የተለያዩ ችግኞች፣ ሰብሎችና መኖ በመትከል ውጤታማ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ከዚህ በፊት ጠረጴዛማ እርከን በስፋት በመስራታቸው ምርትና ምርታማነታቸው እንዳሳደገላቸው ያነሱት አርሶ አደሮቹ በዚህም ያላቸውን ልምድና አደረጃጀት በመጠቀም የተጀመረው ስራ በጓሮአቸውም ይበልጥ እንደሚሰሩ ገልጸዋል።

በተያያዘም በወረዳው በበጋ መስኖ ስንዴ፣ በአትክልትና ፍራፍሬ የተሰሩ ስራዎች ጎብኝቷል ሲል የዘገበው የጉራጌ ዞን የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ነው።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *